ሕዝቅኤል
39 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ በጎግ ላይ ትንቢት ተናገር፤+ እንዲህም በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የመሼቅና የቱባል+ ዋና አለቃ* የሆንከው ጎግ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ተነስቻለሁ። 2 እመልስሃለሁ፤ ደግሞም እነዳሃለሁ፤ ራቅ ካለውም የሰሜን ምድር አምጥቼ+ ወደ እስራኤል ተራሮች እወስድሃለሁ። 3 በግራ እጅህ ያለውን ደጋንህንም ሆነ በቀኝ እጅህ የያዝካቸውን ፍላጻዎችህን አስጥልሃለሁ። 4 አንተና ወታደሮችህ ሁሉ እንዲሁም ከአንተ ጋር የሚሆኑት ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ።+ ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉና ለዱር አራዊት መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ።”’+
5 “‘አውላላ ሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤+ እኔ ራሴ ተናግሬአለሁና’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
6 “‘በማጎግና ያለስጋት በደሴቶች በሚኖሩት ላይም እሳት እሰዳለሁ፤+ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። 7 ቅዱስ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜ እንዲረክስ አልፈቅድም፤ ብሔራትም እኔ ይሖዋ፣ የእስራኤል ቅዱስ+ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’+
8 “‘አዎ፣ በትንቢት የተነገረው ነገር ይመጣል፤ ደግሞም ይፈጸማል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘ያ ያልኩት ቀን ይህ ነው። 9 በእስራኤል ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ወጥተው፣ የጦር መሣሪያዎቹን ይኸውም ትናንሾቹንና* ትላልቆቹን ጋሻዎች፣ ደጋኖቹን፣ ፍላጻዎቹን፣ የጦር ቆመጦቹንና* ጦሮቹን እሳት ያነዱባቸዋል። ለሰባት ዓመታትም እሳት ለማንደድ ይጠቀሙባቸዋል።+ 10 የጦር መሣሪያዎቹን እሳት ለማንደድ ስለሚጠቀሙባቸው ከሜዳ እንጨት መልቀም ወይም ከጫካ ማገዶ መሰብሰብ አያስፈልጋቸውም።’
“‘የበዘበዟቸውን ይበዘብዛሉ፤ የመዘበሯቸውንም ይመዘብራሉ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
11 “‘በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር፣ ከባሕሩ በስተ ምሥራቅ በሚጓዙት ሰዎች ሸለቆ ለጎግ+ የመቃብር ቦታ እሰጠዋለሁ፤ በዚያ የሚያልፉትንም ሰዎች መንገድ ይዘጋል። ጎግንና ስፍር ቁጥር የሌለውን ሠራዊቱን ሁሉ በዚያ ይቀብራሉ፤ ሸለቆውንም የሃሞን ጎግ ሸለቆ*+ ብለው ይጠሩታል። 12 የእስራኤል ቤት ሰዎች እነሱን ቀብረው ምድሪቱን ለማንጻት ሰባት ወር ይፈጅባቸዋል።+ 13 የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እነሱን ይቀብራል፤ ይህም ራሴን በማስከብርበት ቀን ዝና ያስገኝላቸዋል’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
14 “‘ምድሪቱ ትነጻ ዘንድ፣ ሰዎች በየጊዜው በምድሪቱ ላይ እንዲያልፉና በምድሪቱ ላይ የቀሩትን አስከሬኖች እንዲቀብሩ ይመደባሉ። ለሰባት ወራትም ፍለጋቸውን ይቀጥላሉ። 15 በምድሪቱ ላይ የሚያልፉት ሰዎች የሰው አፅም ሲያዩ በአጠገቡ ምልክት ያደርጋሉ። ከዚያም እንዲቀብሩ የተመደቡት አፅሙን በሃሞን ጎግ ሸለቆ+ ይቀብሩታል። 16 በዚያም ሃሞና* ተብላ የምትጠራ ከተማ ትኖራለች። እነሱም ምድሪቱን ያነጻሉ።’+
17 “አንተም፣ የሰው ልጅ ሆይ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለተለያዩ ወፎችና ለዱር አራዊት ሁሉ እንዲህ በል፦ “አንድ ላይ ተሰብስባችሁ ኑ። ለእናንተ በማዘጋጀው መሥዋዕቴ ዙሪያ ተሰብሰቡ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚዘጋጅ ታላቅ መሥዋዕት ነው።+ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ።+ 18 የኃያላንን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም አለቆች ደም ትጠጣላችሁ፤ እነሱ አውራ በጎች፣ ጠቦቶች፣ አውራ ፍየሎችና ወይፈኖች ሲሆኑ ሁሉም የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው። 19 እናንተም እኔ ከማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት፣ እስክትጠግቡ ድረስ ስብ ትሰለቅጣላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ።”’
20 “‘በማዕዴም ፈረሶችንና ሠረገለኞችን እንዲሁም ኃያላን ሰዎችንና ሁሉንም ዓይነት ተዋጊዎች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
21 “‘በብሔራት መካከል ክብሬን እገልጣለሁ፤ ብሔራት ሁሉ የወሰድኩትን የፍርድ እርምጃና በእነሱ መካከል የገለጥኩትን ኃይል* ያያሉ።+ 22 ከዚያ ቀን አንስቶ የእስራኤል ቤት ሰዎች እኔ አምላካቸው ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። 23 ብሔራትም የእስራኤል ቤት ሰዎች በግዞት የተወሰዱት በገዛ ራሳቸው በደል ይኸውም ለእኔ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው እንደሆነ ያውቃሉ።+ ስለዚህ ፊቴን ከእነሱ ሰወርኩ፤+ ለጠላቶቻቸውም አሳልፌ ሰጠኋቸው፤+ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። 24 እንደ ርኩሰታቸውና እንደ በደላቸው መጠን አደረግኩባቸው፤ ፊቴንም ከእነሱ ሰወርኩ።’
25 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በምርኮ የተወሰዱትን የያዕቆብ ወገኖች እመልሳለሁ፤+ ለእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤+ የስሜንም ቅድስና አስከብራለሁ።*+ 26 ለእኔ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ውርደት ከደረሰባቸው+ በኋላ የሚያስፈራቸው ሳይኖር በምድራቸው ላይ ያለስጋት ይኖራሉ።+ 27 ከሕዝቦች መካከል መልሼ ሳመጣቸውና ከጠላቶቻቸው አገሮች ስሰበስባቸው፣+ በብዙ ብሔራት ፊት፣ በመካከላቸው ራሴን እቀድሳለሁ።’+
28 “‘በብሔራት መካከል በግዞት እንዲኖሩ ሳደርግና ከዚያም አንዳቸውንም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው መልሼ ሳመጣቸው፣ እኔ አምላካቸው ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 29 ከእንግዲህ ፊቴን ከእስራኤል ቤት ሰዎች አልሰውርም፤+ በእነሱ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁና’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”