ከዓለም አካባቢ
◼ ሁለት ሺህ ስድስት “በጣም ሞቃት በመሆናቸው ከተመዘገቡት ዓመታት ስድስተኛው እንደሚሆን ይታሰባል።” በጣም ሞቃት የሆኑት አሥር ዓመታት ያጋጠሙት ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ ነው።—የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት
◼ የቤይጂንግ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ የእብድ ውሻ በሽታን መስፋፋት ለመግታት ሲባል አንድ ቤተሰብ “አንድ ውሻ” ብቻ እንዲኖረው የሚያዝዝ ሕግ አውጥቷል። በ2004 ቻይና ውስጥ በእብድ ውሻ በሽታ ምክንያት 2,660 ሰዎች ሞተዋል።—ሺንህዋ ኦንላይን፣ ቻይና
◼ በሆቴል ውስጥ የሚያርፉ እንግዶች በክፍሎቹ ውስጥ የሚገኙትን የበር እጀታዎች፣ ማብሪያና ማጥፊያዎች፣ ስልኮችና ቴሌቪዥንን ከርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችለውን መሣሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) የሚነኩ ከሆነ “50 በመቶ ጉንፋን የመያዝ አጋጣሚ ይኖራቸዋል።”—ማክሊንስ፣ ካናዳ
በአማዞን የሚገኙ ነፍሳትን መቁጠር
ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ የሥነ እንስሳት ተመራማሪዎች በአማዞን ደን ውስጥ እስካሁን ድረስ በግምት 60,000 የሚሆኑ የነፍሳት ዝርያዎች እንዳገኙ ገልጸዋል። ፎልያ ኦንላይን እንደገለጸው ወደፊት 180,000 የሚያህሉ የነፍሳት ዝርያዎች እንደሚገኙ ይገመታል። በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ 20 ተመራማሪዎች ይገኛሉ። እነዚህ ተመራማሪዎች በየዓመቱ በአማካይ 2.7 የነፍሳት ዝርያዎችን እንደሚያገኙ በቅርብ የወጡ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ አያያዝ እያንዳንዱ የተመራማሪዎች ቡድን በአማካይ ለ35 ዓመታት ቢሠራ ነፍሳቱን የማግኘቱን ሂደት ለማጠናቀቅ 90 ትውልድ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም 3,300 ዓመታት ገደማ ይፈጃል ማለት ነው!
የኃይል እጥረት
“ከምድር ሕዝብ ውስጥ ሩብ ያህሉ ማለትም 1.6 ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ ሲሆን 2.4 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ምግብ ለማብሰልና ሙቀት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ኃይል በዋነኝነት የሚያገኙት ከከሰል፣ ከኩበት ወይም ከእንጨት ነው” በማለት አወር ፕላኔት የተሰኘው በተባበሩት መንግሥታት አካባቢያዊ ፕሮግራም የተዘጋጀ መጽሔት ይናገራል። “ከእነዚህ ባሕላዊ የኃይል ምንጮች የሚወጣው ጭስ ደግሞ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ተኩል የሚያህሉ ሴቶችንና ሕፃናትን ለሞት ይዳርጋቸዋል።”
በኢንተርኔት አማካኝነት የሚመሠረቱ ግንኙነቶች ለሥቃይ ሊዳርጉህ ይችላሉ
በኢንተርኔት አማካኝነት ከሌሎች ጋር ግንኙነት መመሥረት የሚቻልባቸው ድረ ገጾች፣ አንድን ግለሰብ ከማያውቃቸው በርካታ ሰዎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉት ሲሆን ይህም ግለሰቡ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነ እንዲሰማው እንደሚያደርግ ሪፖርት ተደርጓል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድረ ገጾች “ለውሸታሞች” እንዲሁም ለዘረኞች፣ በሰው ጉዳይ ጣልቃ ለሚገቡና በጭፍን ጥላቻ ለታወሩ ሰዎች “ገነት” እንደሆኑ ፎልያ ኦንላይን ገልጿል። የአንዳንዶቹ ድረ ገጾች ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ስለ ማንነታቸው የሐሰት መረጃ ያቀርባሉ። ሌሎች ደግሞ በጣም ወፍራም የሆኑ ሰዎችን፣ አጫጭሮችን፣ ኪንኪ ጸጉር ያላቸውንና ሌሎችንም እንዲሸማቀቁ በማድረግ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ያስከትሉባቸዋል። ኢቬሊዜ ፎርቲም የተባሉት ብራዚላዊት የሥነ አእምሮ ተመራማሪ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ “በእንዲህ ዓይነት ችግር የሚሠቃዩ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ከሚያጋጥማቸው ነገር ይበልጥ የሚያሳስባቸው [በድረ ገጾቹ] ላይ የሚከናወነው ነገር ነው” ብለዋል።
ስለ ከዋክብት ለማጥናት የሚረዳ ጥንታዊ መሣሪያ
በ1901 ሰፍነግ ፍለጋ ባሕር ውስጥ የሚገቡ ዋናተኞች አንዲኪቲራ በምትባለው የግሪክ ደሴት አቅራቢያ በሰጠመች ጥንታዊት የሮም መርከብ ውስጥ አንድ የዛገ የእጅ መሣሪያ አገኙ። በአሁኑ ወቅት ይህ ዕቃ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን ለሥነ ከዋክብት ጥናት ያገለግል የነበረ የተራቀቀ የስሌት መሣሪያ መሆኑ ታውቋል። በቅርቡ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል በሚያሳይ ራጅ በመጠቀም ይህን “የአንዲኪቲራ መሣሪያ” ያጠኑት የሳይንስ ሊቃውንት፣ ጥንት ከእንጨት በተሠራ ማህደር ውስጥ የሚቀመጡ ቢያንስ 30 የሚያህሉ ከነሐስ የተሠሩ ተሽከርካሪ ጥርሶች እንደነበሩት ደርሰውበታል። መሣሪያው የፀሐይንና የጨረቃን አቀማመጥ በትክክል ሊያሳይ የሚችልና የጨረቃና የፀሐይ ግርዶሾችን አስቀድሞ ለመተንበይ የሚያስችል ነው። ኔቸር የተሰኘው መጽሔት መሣሪያው “ከሙያ አንጻር ሲታይ፣ ከዚያ ወዲህ ቢያንስ ለአንድ ሺህ ዓመታት እንደተሠራ ከሚታወቅ ከማንኛውም መሣሪያ ይበልጥ የተራቀቀ” እንደሆነ ገልጿል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
AP Photo/Thanassis Stavrakis