ግንቦት
ሰኞ፣ ግንቦት 1
በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ።—ዕብ. 12:3
ይሖዋ ልጁን እንድናውቀው ለመርዳት ሲል በፍቅር ተነሳስቶ በቃሉ ውስጥ አራቱን ወንጌሎች አካትቶልናል። ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጽ ታሪካዊ ዘገባ ይዘዋል። እነዚህ ዘገባዎች ኢየሱስ ምን እንደተናገረ፣ ምን እንዳደረገና ምን እንደተሰማው ይነግሩናል። እነዚህ አራት መጻሕፍት የኢየሱስን ምሳሌ ‘በጥሞና እንድናስብ’ ይረዱናል። በሌላ አባባል ወንጌሎች ኢየሱስ የተወውን ፈለግ ይዘዋል ሊባል ይችላል። ስለዚህ የወንጌል ዘገባዎችን በመመርመር ኢየሱስን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ይህም የእሱን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል ይረዳናል። ከወንጌሎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ዘገባዎቹን ከማንበብ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ልናጠናቸውና በጥልቀት ልናሰላስልባቸው ይገባል። (ከኢያሱ 1:8 የግርጌ ማስታወሻ ጋር አወዳድር።) የወንጌል ዘገባዎች ሕያው እንዲሆኑላችሁ አድርጉ። ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ በመሣል፣ የተከናወነውን ነገር ለማየትና ለመስማት እንዲሁም እናንተ በቦታው ብትኖሩ ኖሮ ምን ይሰማችሁ እንደነበር ለማሰብ ሞክሩ። የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው ጽሑፎች በመጠቀም ምርምር አድርጉ። w21.04 4-5 አን. 11-13
ማክሰኞ፣ ግንቦት 2
በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል . . . ነው።—1 ቆሮ. 1:23
ይሖዋ፣ መሲሑ ‘በ30 የብር ሰቅል’ አልፎ እንደሚሰጥ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከዘመናት በፊት በቃሉ ውስጥ አስነግሮ ነበር። (ዘካ. 11:12, 13) ኢየሱስን የሚከዳው ከቅርብ ወዳጆቹ አንዱ እንደሚሆንም ተገልጿል። (መዝ. 41:9) በተጨማሪም ነቢዩ ዘካርያስ “እረኛውን ምታ፤ መንጋውም ይበተን” በማለት ጽፎ ነበር። (ዘካ. 13:7) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በእነዚህ ክስተቶች ከመሰናከል ይልቅ ትንቢቶቹ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው እምነታቸው ሊጠናከር ይገባ ነበር። በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በዘመናችን አንዳንድ የታወቁ የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን ትተው በመውጣት ከሃዲዎች ሆነዋል፤ ከዚያም ሌሎችን ከእውነት ለማራቅ ሞክረዋል። እነዚህ ሰዎች በዜና ማሰራጫዎችና በኢንተርኔት አማካኝነት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አሉታዊ ዘገባ፣ ከፊል እውነትነት ያለው ወሬ ይባስ ብሎም ዓይን ያወጣ ውሸት አሰራጭተዋል። ያም ሆኖ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዚህ አይሰናከሉም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ነገሮች እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ እንደተናገረ ያውቃሉ።—ማቴ. 24:24፤ 2 ጴጥ. 2:18-22፤ w21.05 11 አን. 12፤ 12-13 አን. 18-19
ረቡዕ፣ ግንቦት 3
የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።—ምሳሌ 4:18
ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛው እውቀት በጊዜ ሂደት እየጨመረ እንደሚሄድ ይናገራሉ። (ቆላ. 1:9, 10) ይሖዋ እውነትን የሚገልጠው ቀስ በቀስ ነው፤ እኛም የእውነት ብርሃን እየደመቀ እስኪሄድ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች መሆን አለብን። አመራር የሚሰጡን ወንድሞች አንድን እውነት በተመለከተ ያለን ግንዛቤ መስተካከል እንዳለበት ሲገነዘቡ አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች ማስተካከያ የሚያደርጉት ተከታዮቻቸውን ለማስደሰት ወይም ወደ ዓለም ይበልጥ ለመቅረብ ሲሉ ነው፤ የይሖዋ ድርጅት ግን ማስተካከያዎችን የሚያደርገው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብና ኢየሱስ የተወውን የአምልኮ ሥርዓት በጥብቅ ለመከተል ሲል ነው። (ያዕ. 4:4) ማስተካከያዎችን ለማድረግ የሚያነሳሳን ዘመን አመጣሽ አስተሳሰቦችን ለመደገፍ ወይም ብዙኃኑን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን ግንዛቤ ከበፊቱ ይበልጥ እየጠራ መሄዱ ነው። እውነትን እንወዳለን!—1 ተሰ. 2:3, 4፤ w21.10 22 አን. 12
ሐሙስ፣ ግንቦት 4
የሚያስጨንቃችሁን . . . ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ።—1 ጴጥ. 5:7
የብቸኝነት ስሜት ቢሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ እያደረገልህ ባለው ድጋፍ ላይ አተኩር። (መዝ. 55:22) እንዲህ ማድረግህ ስለ ሁኔታህ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳሃል። ይሖዋ ብቸኝነት የሚሰማቸውን የእምነት አጋሮችህን እየረዳቸው ያለው እንዴት እንደሆነም አስብ። (1 ጴጥ. 5:9, 10) ሂሮሺ ለበርካታ ዓመታት እውነት ውስጥ ቢኖርም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዳቸውም ወደ እውነት አልመጡም፤ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ውስጥ ሁሉም ሰው . . . ይሖዋን ለማገልገል አቅሙ የፈቀደውን እያደረገ ነው፤ እውነት ውስጥ ቤተሰብ የሌለን ይህን ስናይ እንጽናናለን።” በተጨማሪም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይኑርህ። ይህም የሚሰማህን ስሜት ለይሖዋ በግልጽ መንገርን ይጨምራል። የአምላክን ቃል አዘውትረህ ማንበብህ ጠቃሚ ነው፤ እንዲሁም ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅር ጎላ አድርገው በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ አሰላስል። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ መዝሙር 27:10 እና ኢሳይያስ 41:10 ያሉ የሚያጽናኑ ጥቅሶችን በቃላቸው ይይዛሉ። ሌሎች ደግሞ ለስብሰባ ሲዘጋጁ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ በድምፅ የተቀረጸውን ንባብ ያዳምጣሉ፤ እንዲህ ማድረጋቸው የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ተናግረዋል። w21.06 9-10 አን. 5-8
ዓርብ፣ ግንቦት 5
ድንገት የሚከሰት የሚያሸብር ነገር . . . አያስፈራህም።—ምሳሌ 3:25
የምትወዱትን ሰው በሞት በማጣታችሁ ምክንያት በሐዘን ተውጣችኋል? ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በማንበብ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ። የቤተሰባችሁ አባል ከጉባኤ በመወገዱ ምክንያት ልባችሁ በሐዘን ተሰብሯል? አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ ምንጊዜም ጠቃሚ እንደሆነ ያላችሁን እምነት ለማጠናከር የግል ጥናት አድርጉ። ያጋጠማችሁ ችግር ምንም ይሁን ምን አጋጣሚውን እምነታችሁን ለመገንባት ተጠቀሙበት። ልባችሁን በይሖዋ ፊት አፍስሱ። ራሳችሁን አታግልሉ፤ ከዚህ ይልቅ ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ተቀራረቡ። (ምሳሌ 18:1) ለመጽናት በሚረዷችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ፤ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የምትካፈሉት እያለቀሳችሁ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችሁን አታቁሙ። (መዝ. 126:5, 6) አዘውትራችሁ በስብሰባዎች ላይ ተገኙ፤ በአገልግሎት ተካፈሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ። በተጨማሪም ይሖዋ ባዘጋጀላችሁ በረከቶች ላይ ምንጊዜም ትኩረት አድርጉ። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ስታስተውሉ በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይጠናከራል። w21.11 23 አን. 11፤ 24 አን. 17
ቅዳሜ፣ ግንቦት 6
በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም።—ማቴ. 18:14
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ‘ትናንሾች’ የሆኑት እንዴት ነው? እስቲ አስበው፦ ዓለም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለማን ነው? ሀብት፣ ዝና እና ሥልጣን ላላቸው ሰዎች ነው። በአንጻሩ ግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ትልቅ ቦታ የማይሰጣቸውና ከቁጥር የማይገቡ ስለሆኑ በዓለም ዘንድ እንደ ‘ትናንሾች’ ይቆጠራሉ። (1 ቆሮ. 1:26-29) ይሖዋ ለእነሱ ያለው አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ኢየሱስ ‘እነዚህ ትናንሾች’ በማለት ስለጠራቸው ሰዎች ለመናገር የተነሳሳው ለምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” በማለት ስለጠየቁት ነው። (ማቴ. 18:1) በዘመኑ የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ለሥልጣን እና ለደረጃ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። አንድ ምሁር እንዳሉት “ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ክብር፣ መልካም ስም፣ ታዋቂነት፣ ውዳሴና አክብሮት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን እንኳ ይሰጡ ነበር።” ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ ባሕል ውስጥ በስፋት የሚታየውን የፉክክር መንፈስ ከልባቸው ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያውቅ ነበር። w21.06 20 አን. 2፤ 21 አን. 6, 8፤ 22 አን. 9
እሁድ፣ ግንቦት 7
ዘይትና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ በቀና ምክር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ወዳጅነትም እንዲሁ ነው።—ምሳሌ 27:9
ሐዋርያው ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በተሰሎንቄ ያሉ ወንድሞች ምክር ባስፈለጋቸው ወቅት ጳውሎስ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለም። ሆኖም ጳውሎስ ለእነሱ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ በቅድሚያ ለእምነት ሥራቸው፣ ከፍቅር ለመነጨ ድካማቸውና ለጽናታቸው አመስግኗቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቷል፤ ሕይወታቸው አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና ስደትን እየተጋፈጡ እንዳሉ ተናግሯል። (1 ተሰ. 1:3፤ 2 ተሰ. 1:4) እንዲያውም ለሌሎች ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ እንደሆኑ ገልጾላቸዋል። (1 ተሰ. 1:8, 9) እነዚህ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ከልቡ ስላመሰገናቸው ተደስተው መሆን አለበት። ጳውሎስ እነዚህን ወንድሞቹን በጣም እንደሚወዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ ውጤታማ ምክር መስጠት የቻለው ለዚህ ነው።—1 ተሰ. 4:1, 3-5, 11፤ 2 ተሰ. 3:11, 12፤ w22.02 15 አን. 6
ሰኞ፣ ግንቦት 8
እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።—ራእይ 21:4
ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት መሪዎች በመጠቀም ‘ይሖዋ ጨካኝ ነው’ እንዲሁም ‘በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው እሱ ነው’ የሚል ትምህርት ያስፋፋል። እንዲያውም አንዳንዶች፣ ሕፃናት ሲሞቱ ‘አምላክ ተጨማሪ መላእክት ስለሚያስፈልጉት ወደ ሰማይ ወስዷቸዋል’ ብለው ያስተምራሉ። ይህ በአምላክ ላይ የተሰነዘረ ስድብ ነው። እኛ ግን ይሖዋ አፍቃሪ አባት እንደሆነ እናውቃለን። በመሆኑም በከባድ በሽታ ብንያዝ ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ብናጣ በፍጹም አምላክን አንወቅስም። እንዲያውም አንድ ቀን አምላክ ነገሮችን እንደሚያስተካክል እምነት አለን። ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ መሆኑን ሰሚ ጆሮ ላለው ሁሉ እንናገራለን። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ እሱን ለሚነቅፈው አካል ግሩም ምላሽ እንዲሰጥ ያስችለዋል። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ ሩኅሩኅ አምላክ ነው። በስደት፣ በሕመም ወይም በአለፍጽምናችን የተነሳ ስንሠቃይ በሚመለከትበት ጊዜ በጣም ያዝናል። (መዝ. 22:23, 24) ይሖዋ ሥቃያችን ይሰማዋል፤ ከሥቃያችን ሊገላግለን ይፈልጋል፤ ደግሞም ይገላግለናል።—ከዘፀአት 3:7, 8 እና ከኢሳይያስ 63:9 ጋር አወዳድር፤ w21.07 9-10 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ግንቦት 9
የክብርና የግርማ ዘውድ . . . ደፋህለት።—መዝ. 8:5
በቅርቡ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ከሁሉ የላቀውን ክብር፣ ማለትም ይሖዋን ለዘላለም የመውደድና የማምለክ መብት ያገኛሉ! አዳምና ሔዋን ከአምላክ ቤተሰብ ለመውጣት በመወሰናቸው ምክንያት የመጡትን ችግሮች በሙሉ ኢየሱስ ያስተካክላቸዋል። ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ጤናማ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 23:42, 43) በምድር ላይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ወደ ፍጽምና ሲደርሱ ሁሉም ዳዊት የተናገረለትን ‘ክብርና ግርማ’ ይላበሳሉ። ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባል ከሆንክ ግሩም ተስፋ ተዘርግቶልሃል። (ራእይ 7:9) አምላክ ይወድሃል፤ የቤተሰቡ አባል እንድትሆንም ይፈልጋል። እንግዲያው እሱን ለማስደሰት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። አምላክ በሰጠህ ተስፋዎች ላይ በየዕለቱ አሰላስል። የምንወደውን ሰማያዊ አባታችንን የማምለክና እሱን ለዘላለም የማወደስ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው! w21.08 7 አን. 18-19
ረቡዕ፣ ግንቦት 10
ካልታከትን [እናጭዳለን]።—ገላ. 6:9
ነቢዩ ኤርምያስ የሰዎችን ግድየለሽነትና ተቃውሞ ተቋቁሞ ለአሥርተ ዓመታት ሰብኳል። በተቃዋሚዎቹ “ስድብና ፌዝ” በጣም ከማዘኑ የተነሳ ሥራውን ለማቆም እስከማሰብ ደርሶ ነበር። (ኤር. 20:8, 9) ሆኖም ኤርምያስ ተስፋ አልቆረጠም! የተሰማውን አሉታዊ ስሜት ለማሸነፍና በአገልግሎቱ ደስታ ለማግኘት የረዳው ምንድን ነው? በሁለት ወሳኝ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ነው። አንደኛ፣ ኤርምያስ የሚናገረው መልእክት “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” የሚሰጥ ነበር። (ኤር. 29:11) ሁለተኛ፣ ኤርምያስ የይሖዋን ስም የመሸከም መብት አግኝቶ ነበር። (ኤር. 15:16) እኛም በጨለማ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የተስፋ መልእክት የምንናገር ከመሆኑም ሌላ ምሥክሮቹ በመሆን የይሖዋን ስም የመሸከም መብት አግኝተናል። በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ የሰዎች ምላሽ ምንም ይሁን ምን ደስተኛ መሆን እንችላለን። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችሁ እናንተ በፈለጋችሁት ፍጥነት እድገት ባያደርግ ልታዝኑ ወይም ተስፋ ልትቆርጡ አይገባም። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ትዕግሥት ይጠይቃል።—ያዕ. 5:7, 8፤ w21.10 27 አን. 12-13
ሐሙስ፣ ግንቦት 11
ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን አንስተን እንጣል።—ዕብ. 12:1
በይሖዋ አገልግሎት የቱንም ያህል ረጅም ጊዜ ብንቆይ ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን ለመቀጠል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ካልተጠነቀቅን እምነታችን ሊዳከም ይችላል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የምናምንባቸው ነገሮች በማስረጃ የተደገፉ ቢሆኑም በዓይን አይታዩም። የማናየውን ነገር ደግሞ በቀላሉ ልንረሳው እንችላለን። ጳውሎስ እምነት ማጣትን “በቀላሉ ተብትቦ [የሚይዘን] ኃጢአት” ብሎ የጠራው ለዚህ ነው። ታዲያ በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን? (2 ተሰ. 1:3) በመጀመሪያ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው፤ እንዲህ ያለውን ልመናም አዘውትረህ አቅርብ። ለምን? ምክንያቱም እምነት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ካላገኘን በፈጣሪያችን ላይ እምነት መገንባትና ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን መቀጠል አንችልም። ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን አዘውትረን ከለመንነው ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13) እንዲያውም “እምነት ጨምርልን” ብለን በቀጥታ መጸለይ እንችላለን። (ሉቃስ 17:5) በተጨማሪም የአምላክን ቃል የምታጠናበት ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ።—መዝ. 1:2, 3፤ w21.08 18-19 አን. 16-18
ዓርብ፣ ግንቦት 12
ሽበት . . . የውበት ዘውድ ነው።—ምሳሌ 16:31
አረጋውያን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ማከናወን ይችላሉ። በአንድ ወቅት የነበራቸውን ያህል ጉልበት ባይኖራቸውም እንኳ በረጅም ዘመናት ያካበቱት ብዙ ልምድ አላቸው። ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች በእነሱ መጠቀሙን ሊቀጥል ይችላል። ዕድሜያቸው ከገፋም በኋላ ይሖዋን በትጋት ማገልገላቸውን የቀጠሉ ታማኝ ሰዎችን ግሩም ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ የይሖዋ ነቢይና የእስራኤል ብሔር መሪ ሆኖ ማገልገል በጀመረበት ወቅት ዕድሜው 80 ዓመት ገደማ ነበር። ዳንኤል ካረጀም በኋላ፣ ምናልባትም ዕድሜው 90 ዓመት ካለፈም በኋላ ጭምር ይሖዋ እሱን ቃል አቀባዩ አድርጎ መጠቀሙን ቀጥሏል። ሐዋርያው ዮሐንስም የራእይ መጽሐፍን በመንፈስ መሪነት የጻፈው በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ሳይሆን አይቀርም። “ጻድቅና ለአምላክ ያደረ ሰው” ስለነበረው ስለ ስምዖን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ በጣም ጥቂት ነው። ሆኖም ይሖዋ ይህን ሰው በደንብ ያውቀው ነበር፤ በተጨማሪም ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት እንዲሁም ስለ እሱና ስለ እናቱ ትንቢት የመናገር መብት ሰጥቶታል።—ሉቃስ 2:22, 25-35፤ w21.09 3-4 አን. 5-7
ቅዳሜ፣ ግንቦት 13
ይሖዋ ሆይ፣ ልቤ አይኩራራም፤ . . . እጅግ ታላላቅ ነገሮችን . . . አልመኝም።—መዝ. 131:1
ወላጆች አንዱን ልጃቸውን ከሌላው ጋር ላለማወዳደር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ልጃቸውን ከአቅሙ በላይ ሊጠብቁበት አይገባም። እንዲህ ማድረግ ልጃቸውን ተስፋ ሊያስቆርጠው ይችላል። (ኤፌ. 6:4) ሳቺኮ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ በሁሉም ፈተናዎቼ መቶ ከመቶ እንዳመጣ ትፈልግ ነበር፤ ይህን ማድረግ ደግሞ አልቻልኩም። ትምህርት ከጨረስኩ ብዙ ዓመት አልፎኛል፤ አሁንም ግን ለይሖዋ ምርጤን ብሰጥም እንኳ ‘እሱ ይደሰትብኝ ይሆን?’ የሚለውን እጠራጠራለሁ።” ንጉሥ ዳዊት “እጅግ ታላላቅ ነገሮችን” ወይም ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮችን እንደማይመኝ ተናግሯል። ትሑትና ልኩን የሚያውቅ መሆኑ ‘እንዲረጋጋ’ እና ሰላም እንዲያገኝ አድርጎታል። (መዝ. 131:2) ወላጆች ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ወላጆች ትሑት መሆናቸው ከራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸውም ከልክ በላይ እንዳይጠብቁ ያደርጋቸዋል። ወላጆች፣ ልጃቸው ጥንካሬውንና ድክመቱን እንዲያውቅ እንዲሁም ሊደርስባቸው የሚችሉ ግቦች እንዲያወጣ በመርዳት ለራሱ ጥሩ ግምት እንዲኖረው ሊረዱት ይችላሉ። w21.07 21 አን. 5-6
እሁድ፣ ግንቦት 14
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
ይሖዋ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት እንደሰጠን ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም እሱን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ መምረጥ እንችላለን። አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ባይሆኑላቸውም እንኳ ይሖዋን ለማገልገል መርጠዋል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል። ሌሎች ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸው እነሱን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርጉም ካደጉ በኋላ እውነትን ለመተው መርጠዋል። ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋን ማገልገል እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው ውሳኔ ነው። (ኢያሱ 24:15) እንግዲያው ልጃቸው እውነትን በመተዉ ያዘኑ ወላጆች ሁኔታው የእነሱ ጥፋት እንደሆነ ሊሰማቸው አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወላጆች እውነትን ይተዉ፣ ሌላው ቀርቶ ቤተሰባቸውንም ጥለው ይሄዱ ይሆናል። (መዝ. 27:10) ይህ ሁኔታ ወላጆቻቸውን እንደ ምሳሌ ሲመለከቱ የኖሩትን ልጆች ቅስማቸውን ሊሰብረው ይችላል። ወጣቶች፣ አባታችሁ ወይም እናታችሁ ተወግደው ከሆነ ይሖዋ ሥቃያችሁን በሚገባ እንደሚረዳው አትጠራጠሩ። ይሖዋ ይወዳችኋል፤ እንዲሁም የምታሳዩትን ታማኝነት ያደንቃል። በተጨማሪም ለወላጆቻችሁ ውሳኔ እናንተ ተጠያቂ እንዳልሆናችሁ አስታውሱ። w21.09 27 አን. 5-7
ሰኞ፣ ግንቦት 15
ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል።—ዕብ. 12:6
አንድ የተወገደ ክርስቲያን መንጋው ላይ ሊጋባ የሚችል ተላላፊ በሽታ ከያዘው በግ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ሰው በመንፈሳዊ ታሟል። (ያዕ. 5:14) እንደ አንዳንድ በሽታዎች ሁሉ መንፈሳዊ ሕመምም ወደ ሌሎች ሊተላለፍ ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ፣ በመንፈሳዊ የታመመ ሰው ከጉባኤው እንዲገለል ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ ተግሣጽ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት የመንጋው አባላት ያለውን ፍቅር ያሳያል፤ እንዲሁም ኃጢአተኛው ልቡ እንዲነካና ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል። ግለሰቡ፣ በተወገደበት ወቅትም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላል። እዚያም በመንፈሳዊ መመገብና እምነቱን ማጠናከር ይችላል። በተጨማሪም ለግሉ የሚጠቀምባቸውን ጽሑፎች መውሰድና JW ብሮድካስቲንግ መመልከት ይችላል። ሽማግሌዎች ግለሰቡ የሚያደርገውን ለውጥ ሲያዩ እንደገና በመንፈሳዊ ጤናማ መሆንና ወደ ጉባኤው መመለስ እንዲችል አልፎ አልፎ በግሉ ምክርና መመሪያ ሊሰጡት ይችላሉ። w21.10 10 አን. 9, 11
ማክሰኞ፣ ግንቦት 16
“ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ” የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም።—ማቴ. 7:21
በዛሬው ጊዜ እኛ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉትን የአምልኮ ሥርዓት እንከተላለን። ለምሳሌ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የሚያካትተው የድርጅታችን መዋቅር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሐዋርያት ያቋቋሙትን ሥርዓት የሚከተል ነው። (ፊልጵ. 1:1፤ ቲቶ 1:5) ስለ ፆታ ግንኙነት፣ ስለ ጋብቻና ስለ ደም ቅድስና ያለን አመለካከት እንዲሁም ጉባኤውን ንስሐ ከማይገቡ ኃጢአተኞች ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይከተሉት በነበረው አሠራር ላይ የተመሠረተ ነው። (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮ. 5:11-13፤ 6:9, 10፤ ዕብ. 13:4) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው “አንድ እምነት” እንዳለ በቀጥታ ይናገራል። (ኤፌ. 4:4-6) ከይሖዋ ሕዝቦች አንዱ መሆን እንዲሁም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን ማወቅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንግዲያው ያገኘነውን እውነት ምንጊዜም አጥብቀን እንያዝ። w21.10 22-23 አን. 15-17
ረቡዕ፣ ግንቦት 17
ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።—2 ዜና 20:17
ንጉሥ ኢዮሳፍጥ አንድ ከባድ ችግር አጋጠመው። አሞናውያን፣ ሞዓባውያንና በሴይር ተራራማ ክልል የሚኖሩ ሰዎች ግዙፍ ሠራዊት አስከትለው ሊወጉት በመጡበት ወቅት የእሱ፣ የቤተሰቡና የሕዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ ወደቀ። (2 ዜና 20:1, 2) ታዲያ ኢዮሳፍጥ ምን አደረገ? እንዲረዳውና ብርታት እንዲሰጠው ይሖዋን ለመነ። በ2 ዜና መዋዕል 20:5-12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢዮሳፍጥ ያቀረበው ትሕትና የሚንጸባረቅበት ጸሎት ይህ ንጉሥ አፍቃሪ በሆነው ሰማያዊ አባቱ ምን ያህል እንደሚታመን የሚያሳይ ነው። ይሖዋ ያሃዚኤል በተባለ ሌዋዊ አማካኝነት ኢዮሳፍጥን በማነጋገር በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ነገረው። ኢዮሳፍጥ በአምላኩ ሙሉ በሙሉ በመታመን የታዘዘውን አደረገ። እሱና ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን ለመግጠም ሲወጡ ከፊት ያሰለፈው ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወታደሮች ሳይሆን ምንም መሣሪያ ያልታጠቁትን ዘማሪዎች ነው። ይሖዋ ኢዮሳፍጥን አላሳፈረውም፤ ጠላቶቹን ድል አድርጎለታል።—2 ዜና 20:18-23፤ w21.11 15-16 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ግንቦት 18
ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም፤ ምሕረቱ ፈጽሞ አያልቅምና።—ሰቆ. 3:22
ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚያስፈልገንን ድጋፍ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (2 ቆሮ. 4:7-9) የይሖዋ ታማኝ ፍቅር እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም መዝሙራዊው “የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን፣ ደግሞም ታማኝ ፍቅሩን የሚጠባበቁትን በትኩረት ይመለከታል” ብሏል። (መዝ. 33:18-22) ይሖዋን ማገልገል ከመጀመራችን በፊት አምላክ ለሁሉም ሰዎች ከሚያሳየው ፍቅር እንጠቀም ነበር። እሱን ማምለክ ከጀመርን ወዲህ ግን ታማኝ ፍቅሩንም አሳይቶናል። ይህ ፍቅር ይሖዋ በክንዶቹ እቅፍ አድርጎ ጥበቃ እንዲያደርግልን ያነሳሳዋል። ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን አይለይም፤ እንዲሁም የሰጠንን አስደናቂ ተስፋዎች ይፈጽምልናል። ይሖዋ ለዘላለም የእሱ ወዳጆች እንድንሆን ይፈልጋል! (መዝ. 46:1, 2, 7) በመሆኑም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። w21.11 7 አን. 17-18
ዓርብ፣ ግንቦት 19
እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 3:13
አብዛኞቻችን በሥራ ባልደረባቸው፣ አብሯቸው በሚማር ልጅ፣ በዘመዳቸው ወይም በቤተሰባቸው አባል ላይ ቂም ይዘው የቆዩ ሰዎችን እናውቃለን፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ቂም የያዙት ለዓመታት ነው! የዮሴፍ አሥር ወንድሞች በእሱ ላይ ቂም ይዘው እንደነበረ እናስታውሳለን፤ ይህም ውሎ አድሮ፣ ጥላቻ የሚንጸባረቅበት ድርጊት ወደመፈጸም መርቷቸዋል። (ዘፍ. 37:2-8, 25-28) ዮሴፍ ግን እንደ ሥራቸው አላደረገባቸውም! ሥልጣን ባገኘበት ወቅት ወንድሞቹን መበቀል ይችል ነበር፤ እሱ ግን ምሕረት አሳይቷቸዋል። ዮሴፍ ቂም አልያዘም። ከዚህ ይልቅ፣ ከጊዜ በኋላ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ከተመዘገበው ምክር ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። (ዘፍ. 50:19-21) አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል፣ ቂም ከመያዝ ወይም ከመበቀል ይልቅ ይቅር ይላሉ። ኢየሱስም ቢሆን የበደሉንን ይቅር እንድንል አበረታቶናል። (ማቴ. 6:9, 12) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ” በማለት ለክርስቲያኖች ምክር ሰጥቷል።—ሮም 12:19፤ w21.12 11 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ግንቦት 20
የሚፈሩትን ሰዎች ፍላጎት ያረካል፤ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል።—መዝ. 145:19
ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ምሽት ላይ ኢየሱስ ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሄደ። በዚያም የልቡን አውጥቶ ወደ ይሖዋ ጸለየ። (ሉቃስ 22:39-44) ኢየሱስ “በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃ” ያቀረበው በዚህ ከባድ ወቅት ነው። (ዕብ. 5:7) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የጸለየው ስለ የትኛው ጉዳይ ነው? ይሖዋ በታማኝነት ለመጽናት እና የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችለው ጥንካሬ እንዲሰጠው ጸልዮአል። ይሖዋም የልጁን የጭንቅ ጸሎት ሰምቶ እሱን ለማበረታታት መልአኩን ልኮለታል። ኢየሱስ ከባድ ኃላፊነት ጫንቃው ላይ እንደወደቀም ያውቅ ነበር፤ ይህም የአባቱን ስም ከነቀፋ ነፃ ማድረግ ነው። ይሖዋ ኢየሱስ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ልመና ሰምቷል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስን በዋነኝነት ያሳሰበው ለአባቱ እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆኑ እና ስሙን ማስቀደሱ ነበር። እኛም በዋነኝነት የሚያሳስበን ይህ ከሆነ ይሖዋ እርዳታ ለማግኘት የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማናል።—መዝ. 145:18፤ w22.01 18 አን. 15-17
እሁድ፣ ግንቦት 21
ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያጠመቃችኋቸው፣ . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20
ብዙዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ በመሆናችን ይሰናከሉብናል። ምርጫ ሲካሄድ ድምፅ እንድንሰጥ ይጠብቁብናል። ይሁንና ሰብዓዊ መሪ እንዲገዛን መምረጥ የይሖዋን አገዛዝ አንቀበልም ማለት ይሆንብናል። (1 ሳሙ. 8:4-7) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን መገንባት እንዲሁም ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን መፈጸም እንዳለብን ይሰማቸዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት በማድረጋችን ይሰናከሉብናል። እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? (ማቴ. 7:21-23) በዋነኝነት ትኩረት ልናደርግ የሚገባው ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ በማከናወን ላይ ነው። በዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረታችን እንዲከፋፈል ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ሰዎችን እንወዳለን፤ ችግሮቻቸውም ያሳስቡናል። ያም ቢሆን ሰዎችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እነሱን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማርና ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት እንደሆነ እናውቃለን። w21.05 7 አን. 19-20
ሰኞ፣ ግንቦት 22
በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]።—2 ጢሞ. 3:1
በዛሬው ጊዜ ያሉት የብዙዎቹ ብሔራት ገዢዎች አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ሥልጣናቸውን ማስረከብ አይፈልጉም። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ገዢዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ገዢዎችም በኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ እየተቃወሙ ነው። (ሥራ 4:25-28) ታዲያ ይሖዋ ምን አድርጓል? መዝሙር 2:10-12 መልሱን ይሰጠናል፤ እንዲህ ይላል፦ “እንግዲህ እናንተ ነገሥታት አስተውሉ፤ እናንተ የምድር ፈራጆች እርማት ተቀበሉ። ይሖዋን በፍርሃት አገልግሉ፤ ለእሱ በመንቀጥቀጥም ሐሴት አድርጉ። ልጁን አክብሩ፤ አለዚያ አምላክ ይቆጣል፤ ከመንገዱም ትጠፋላችሁ፤ ቁጣው ፈጥኖ ይነድዳልና። እሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።” እነዚህ ተቃዋሚዎች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ይሖዋ በደግነት ጊዜ ሰጥቷቸዋል። አሁንም ቢሆን አመለካከታቸውን ለውጠው የይሖዋን መንግሥት መቀበል ይችላሉ። ይሁንና የቀራቸው ጊዜ አጭር ነው። (ኢሳ. 61:2) ሰዎች እውነትን አውቀው ትክክለኛ ውሳኔ ማድረጋቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጣዳፊ ነው። w21.09 15-16 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ግንቦት 23
ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።—1 ጢሞ. 6:8
ጳውሎስ ያለን ነገር ምንም ይሁን ምን በዚያ ረክተን ልንኖር እንደሚገባ መግለጹ ነበር። (ፊልጵ. 4:12) ከሁሉ የላቀው ውድ ንብረታችን ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና እንጂ ያሉን ቁሳዊ ነገሮች አይደሉም። (ዕን. 3:17, 18) እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመታት ካሳለፉ በኋላ ሙሴ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላክህ ይሖዋ የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና። . . . በእነዚህ 40 ዓመታት አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለነበር ምንም የጎደለብህ ነገር የለም።” (ዘዳ. 2:7) በእነዚያ 40 ዓመታት ይሖዋ ለእስራኤላውያን መና ሰጥቷቸዋል። ከግብፅ ሲወጡ ለብሰውት የነበረው ልብስ እንኳ አላለቀባቸውም። (ዘዳ. 8:3, 4) ይሖዋ ባለን ነገር ረክተን ስንኖር ደስ ይለዋል፤ ምንም ያህል ትንሽ ቢመስልም እንኳ እሱ የሚሰጠንን ነገር እንድናደንቅ፣ ከእሱ እንዳገኘነው በረከት አድርገን እንድንመለከተው እንዲሁም ለስጦታው እንድናመሰግነው ይፈልጋል። w22.01 5 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ግንቦት 24
በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።—ምሳሌ 3:5
ባሎች ቤተሰባችሁን የመንከባከብ ኃላፊነት ስላለባችሁ ቤተሰባችሁን ከጉዳት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ተግታችሁ ትሠራላችሁ። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ ችግሩን በራሳችሁ መፍታት እንደምትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም በራሳችሁ ብርታት አትመኩ። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳችሁ በግላችሁ ጸልዩ። በተጨማሪም ከሚስታችሁ ጋር ሆናችሁ አጥብቃችሁ ጸልዩ። መጽሐፍ ቅዱስን እና ድርጅቱ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በማጥናት ከይሖዋ መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ያገኛችሁትን ምክር በሥራ ላይ አውሉ። እርግጥ ባደረጋችሁት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሌሎች አይስማሙ ይሆናል። የቤተሰባችሁን ደህንነት ማስጠበቅ የምትችሉት ገንዘብና ቁሳዊ ነገር ሲኖራችሁ እንደሆነ ይነግሯችሁ ይሆናል። ሆኖም የንጉሥ ኢዮሳፍጥን ምሳሌ አስታውሱ። (2 ዜና 20:1-30) ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ታምኗል፤ እምነቱንም በተግባር አሳይቷል። ይሖዋ ያንን ታማኝ ሰው አልተወውም፤ እናንተንም ቢሆን አይተዋችሁም።—መዝ. 37:28፤ ዕብ. 13:5፤ w21.11 15 አን. 6፤ 16 አን. 8
ሐሙስ፣ ግንቦት 25
[አምላክ] ፈጽሞ ፍትሕን [አያጓድልም።]—ዘዳ. 32:4
አምላክ በመልኩ ስለፈጠረን ሁሉም ሰው ፍትሕ ሲያገኝ ማየት እንፈልጋለን። (ዘፍ. 1:26) ሆኖም ፍጹም ባለመሆናችን፣ ስለ አንድ ጉዳይ በደንብ እንደምናውቅ በሚሰማን ጊዜም እንኳ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናስ ይሖዋ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት ለማሳየት በመወሰኑ ምን ያህል እንደተበሳጨ አስታውሱ። (ዮናስ 3:10 እስከ 4:1) ውጤቱን ግን አስቡት። ንስሐ የገቡ ከ120,000 የሚበልጡ የነነዌ ሰዎች ሕይወታቸው ተረፈ! መጨረሻውንም አመለካከቱን ማስተካከል ያስፈለገው ዮናስ እንጂ ይሖዋ አይደለም። ይሖዋ ውሳኔ ያደረገበትን ምክንያት ለሰዎች የማብራራት ግዴታ የለበትም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹ ስላደረጋቸው ወይም ሊያደርጋቸው ስላሰባቸው ውሳኔዎች ያሳሰባቸውን ነገር እንዲገልጹ ፈቅዶላቸዋል። (ዘፍ. 18:25፤ ዮናስ 4:2, 3) ውሳኔውን ያደረገበትን ምክንያት ያብራራበት ጊዜም አለ። (ዮናስ 4:10, 11) ያም ቢሆን ይሖዋ ውሳኔ ከማድረጉ በፊትም ሆነ በኋላ የእኛን ይሁንታ ማግኘት አያስፈልገውም።—ኢሳ. 40:13, 14፤ 55:9፤ w22.02 3-4 አን. 5-6
ዓርብ፣ ግንቦት 26
ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ ይሁን፤ አመራር የሚሰጥም እንደ አገልጋይ ይሁን።—ሉቃስ 22:26
‘ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ’ አድርገን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን “እንደ ታናሽ” እንደምንቆጥር በተግባር እናሳያለን። (ፊልጵ. 2:3) ይህን አመለካከት ይበልጥ ባዳበርን መጠን ሌሎችን ላለማሰናከል ይበልጥ ጥንቃቄ እናደርጋለን። ሁሉም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሆነ መንገድ ከእኛ ይበልጣሉ። ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ የምናተኩር ከሆነ ይህን ማስተዋል አይከብደንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር ልብ ልንለው ይገባል፦ “ለመሆኑ አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው? ደግሞስ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለ? ከተቀበልክ ደግሞ እንዳልተቀበልክ ሆነህ የምትኩራራው ለምንድን ነው?” (1 ቆሮ. 4:7) ወደ ራሳችን ትኩረት የመሳብ ወይም ከሌሎች እንደምንበልጥ አድርገን የማሰብ ዝንባሌ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ግሩም ንግግር የማቅረብ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ የተዋጣላቸው እህቶች ለዚህ ችሎታቸው ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ እንዲወደስ ማድረግ ይኖርባቸዋል። w21.06 22 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ ግንቦት 27
ዘርህን ዝራ፤ . . . እጅህ ሥራ አይፍታ።—መክ. 11:6
በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት ሲካፈሉ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጥቷል። አንዳንድ አስፋፊዎች የሚኖሩት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው አፓርታማዎች ወይም በአጥር የተከለሉ መኖሪያ ሰፈሮች በሚበዙበት አካባቢ ነው። እነዚህ ሰፈሮች ወይም አፓርታማዎች ዘበኛ የሚኖራቸው ሲሆን በዚያ ከሚኖር ሰው ፈቃድ ያላገኘ ማንኛውም ግለሰብ ወደ ውስጥ መግባት አይችልም። ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ ሰዎቹን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፤ ወይም ደግሞ የሚያገለግሉት ብዙ ሰው በማይኖርበት ክልል ነው። እነዚህ አስፋፊዎች አንድ ቤት እንኳ ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ በቦታው ሲደርሱ ደግሞ ቤት ውስጥ ሰው ላያገኙ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካጋጠሙን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። በሌላ ጊዜ ሰዎችን ለማግኘት ሞክሩ። ሰዎች በአብዛኛው ቤታቸው በሚገኙበት ሰዓት ላይ ከሰበክን ብዙ ሰዎችን ልናገኝ እንችላለን። መቼም ሁሉም ሰው የሆነ ሰዓት ላይ ቤቱ መመለሱ አይቀርም! በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከሰዓት በኋላ ወይም ምሽት ላይ ሲያገለግሉ ብዙ ሰዎችን ቤታቸው ያገኛሉ። በተጨማሪም ሰዎቹ በዚህ ሰዓት ሰፊ ጊዜ ስለሚኖራቸው ለመወያየት ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። w21.05 15 አን. 5, 7
እሁድ፣ ግንቦት 28
የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።—ማር. 7:7
በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ልደት እና ገና ያሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በዓላት አብረዋቸው አለማክበራቸው ብዙዎችን ያበሳጫቸዋል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በብሔራዊ ክብረ በዓላት ላይ አለመገኘታቸው ወይም ከአምላክ ቃል ጋር በሚጋጩ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አለመካፈላቸው ያስቆጣቸዋል። በእነዚህ ምክንያቶች የሚሰናከሉ ሰዎች አምላክን በትክክለኛ መንገድ እያመለኩ እንዳለ ከልባቸው ያምኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ግልጽ ትምህርት ይልቅ የዓለምን ወጎች ከመረጡ አምላክን ማስደሰት አይችሉም። (ማር. 7:8, 9) እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? ለይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥልቅ ፍቅር ማዳበር ይኖርብናል። (መዝ. 119:97, 113, 163-165) ይሖዋን የምንወደው ከሆነ እሱን ከሚያሳዝኑ ልማዶች በሙሉ እንርቃለን። ከይሖዋ አስበልጠን የምንወደው ምንም ነገር አይኖርም። w21.05 6 አን. 15-16
ሰኞ፣ ግንቦት 29
በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜትህን ጠብቅ፣ መከራን በጽናት ተቋቋም፣ የወንጌላዊነትን ሥራ አከናውን።—2 ጢሞ. 4:5
የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው? አዘውትረን በማጥናት፣ ሳናሰልስ በመጸለይና ይሖዋ በሰጠን ሥራ በመጠመድ ጠንካራ እምነት ይዘን መቀጠል ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 4:4) ጠንካራ እምነት ካለን አሉታዊ ዘገባዎችን ስንሰማ አንደናገጥም። (ኢሳ. 28:16) ለይሖዋ፣ ለቃሉ እንዲሁም ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እውነትን በተዉ ሰዎች እንዳንሰናከል ይረዳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙዎች በኢየሱስ ተሰናክለው እሱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። በሌላ በኩል ግን ሌሎች ብዙ ሰዎች ተቀብለውታል። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ አንድ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል እንዲሁም “ብዙ ካህናት” ይገኙበታል። (ሥራ 6:7፤ ማቴ. 27:57-60፤ ማር. 15:43) በዛሬው ጊዜም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አልተሰናከሉም። ለምን? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን እውነቶች ስለሚያውቁና ስለሚወዷቸው ነው። የአምላክ ቃል “ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ሊያደናቅፋቸው የሚችል ምንም ነገር የለም” ይላል።—መዝ. 119:165፤ w21.05 13 አን. 20-21
ማክሰኞ፣ ግንቦት 30
ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው።—2 ቆሮ. 12:9
ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ሊያከናውን የቻለው በአምላክ ብርታት እንጂ በራሱ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ስደት፣ እስርና ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙትም አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ኃይል ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሰጥቶታል። የጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ የሆነው ወጣቱ ጢሞቴዎስም አገልግሎቱን ለመፈጸም በይሖዋ ኃይል መታመን አስፈልጎታል። ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ ባደረጋቸው ረጅም ሚስዮናዊ ጉዞዎች ላይ አብሮት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጢሞቴዎስ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዞ ጉባኤዎችን እንዲያበረታታ ጳውሎስ ልኮት ነበር። (1 ቆሮ. 4:17) ጢሞቴዎስ እነዚህን ተልእኮዎች ለመፈጸም ብቃት እንደሌለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጳውሎስ “ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም” የሚል ምክር የሰጠው ለዚህ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞ. 4:12) በዚያ ላይ ደግሞ ጢሞቴዎስም በዚህ ወቅት ሥጋውን የሚወጋ እሾህ ይኸውም ‘በተደጋጋሚ የሚነሳ ሕመም’ ነበረበት። (1 ጢሞ. 5:23) ሆኖም ጢሞቴዎስ፣ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምሥራቹን ለመስበክና ወንድሞቹን ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብርታት እንደሚሰጠው እርግጠኛ ነበር።—2 ጢሞ. 1:7፤ w21.05 21-22 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ግንቦት 31
በጎችህን በደንብ ተንከባከብ።—ምሳሌ 27:23
በያዕቆብ 1:19 ላይ የሚገኘው መመሪያ ምክር ለሚሰጡም እንደሚሠራ የታወቀ ነው። ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” አንድ ሽማግሌ ስለ ወንድም ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ ይሰማው ይሆናል፤ ግን በእርግጥ ያውቃል? ምሳሌ 18:13 እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል፦ “እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።” እንግዲያው ግለሰቡ ራሱ ስላለበት ሁኔታ እንዲናገር ማድረግ ከሁሉ የተሻለ ነው። በመሆኑም አንድ ሽማግሌ ከመናገሩ በፊት ማዳመጥ ይኖርበታል። “እንዴት ነህ?” “ልንረዳህ የምንችለው ነገር አለ?” ብሎ መጠየቅ ይችላል። ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ እነሱን በተሻለ መንገድ መርዳትና ማበረታታት ይችላሉ። ውጤታማ ምክር መስጠት፣ እንዲሁ የተወሰኑ ጥቅሶችን ማንበብ ወይም አንዳንድ ሐሳቦችን ማካፈል ብቻ አይደለም። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንደምናስብላቸው፣ ስሜታቸውን እንደምንረዳና ልንረዳቸው እንደምንፈልግ ሊሰማቸው ይገባል። w22.02 17 አን. 14-15