መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው? ክፍል ሦስት
በርማ፣ 1824—የንጉሡ መኮንኖች የአዶኒራምና የአንጀድሰንን የሚስዮናዊ ቤት ያመሰቃቅሉት ጀመር፤ ዋጋ ያወጣል ብለው ያሰቡትንም ነገር ሁሉ ወሰዱ። ይሁን እንጂ ከሁሉ የበለጠውን ውድ ሃብት ማለትም አን በምሥጢር በቤቷ ቀብራው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አላገኙትም። ተርጓሚው አዶኒራም በስለላ ወንጀል ተከሶ የወባ ትንኝ በሞላበት የእስር ቤት ክፍል ውስጥ በሠንሰለት ታስሯል። የትርጉም ቅጂውን ደግሞ እርጥበት ሊያበላሸው ሆነ። ከመበላሸት የሚተርፈው እንዴት ይሆን? አን በትራስ ውስጥ ሰፍታ ለባሏ ወደ እስር ቤት ላከችለት። ትራሱ ምንም ሳይሆን በደህና ሁኔታ ተጠብቆ ቆየ። በውስጡ ያለውም መዝገብ በበርማ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ለመሆን በቅቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ ባለፉት የታሪክ ዘመናት በሙሉ ብዙ ተመሳሳይ አስገራሚ ገጠመኞችን አሳልፏል። ካሁን ቀደም በወጡት እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካበቃበት ጊዜ አንስቶ እስከ 1600 መጀመሪያ ድረስ ያለውን የትርጉም ሥራና የሥርጭት ታሪክ ዳስሰናል። ከዚያ ወዲህስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ነገሮች ገጥመውታል? ለሁሉም ሕዝቦች መዳረስ ችሎ ይሆን? በዚህ ረገድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምን ሚና ተጫውቷል?
ሚስዮናውያንና የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት
በ1600ዎቹና በ1700ዎቹ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ረገድ በበርካታ አገሮች ከፍተኛ እንቅስቃሴ ታይቷል። በዚህ ወቅት በተለይ በእንግሊዝ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። እንዲያውም በዚህች አገር ውስጥ ከንጉሡ አንስቶ እርፍ ጨብጦ እስከሚያርሰው ተራ ገበሬ ድረስ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮችና ትምህርቶች ያልተነካ ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳደረው ተጽዕኖ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። እንግሊዝ በወቅቱ የባሕር ላይ ንግድ የምታካሂድና ታላቅ ቅኝ ገዥ ስለነበረች አንዳንድ የእንግሊዝ ተወላጆች በጉዟቸው ወቅት መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ይዘው ይዘዋወሩ ነበር። ይህም ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመቻ እንዲካሄድ መሠረት ጥሏል።
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 1700ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በእንግሊዝ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ርቀው በሚገኙት የብሪታንያ ግዛቶች ውስጥ ስላሉት የአገሬው ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያስቡ አነሳስቷቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ያሳስባቸው ነበር ማለት አይደለም። ብዙ ቀሳውስት ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚል እምነት ስለነበራቸው አምላክ የተወሰኑ ሰዎች እንዲጠፉ ይፈልጋል ብለው ያስቡ ነበር። ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት የነበረው ዊልያም ካሪ ወደ ሕንድ ለሚያደርገው ጉዞ ድጋፍ ለማሰባሰብ በግለት ተሞልቶ ሲናገር በመሃል አንዱ ድምጹን ከፍ አድርጎ “አርፈህ ተቀመጥ ባክህ፤ አምላክ አረመኔዎችን መለወጥ ከፈለገ የአንተ እርዳታ ሳያስፈልገው ያደርገዋል!” በማለት ዘልፎታል። የሆነ ሆኖ ካሪ በ1793 ወደ ሕንድ ተጓዘ። በጣም የሚያስገርመው ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ 35 የሕንድ ቋንቋዎች ተርጉሟል።
ሚስዮናውያኑ ዋነኛው መሣሪያቸው በአካባቢው ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሶችን ማን ሊያዘጋጅ ይችል ይሆን? ሜሪ ጆንስ በተባለች አንዲት የዌልስ ነዋሪ በሆነች የ16 ዓመት ልጃገረድ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ዙሪያ እንዲሠራጭ ምክንያት የሆነ አንድ እንቅስቃሴ ድንገት ተፋፋመ። በ1800 ሜሪ፣ በዌልስ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ቄስ ለመግዛት ስትል በባዶ እግሯ 40 ኪሎ ሜትር ተጉዛ ትሄዳለች። ሜሪ ለስድስት ዓመታት ገንዘብ ስታጠራቅም ቆይታለች፤ እዚያ ስትደርስ ግን መጽሐፍ ቅዱሶቹ በሙሉ ተሸጠው እንዳለቁ ስታውቅ ወሽመጧ ቁርጥ አለ፤ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። በዚህ ነገር ልባቸው የተነካው ቄስ ለሜሪ ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል አንዱን ሰጧት።
ከዚያ በኋላ ቄሱ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ስለሚፈልጉ ሌሎች ብዙ ሰዎችም በማሰብ ችግሩን በለንደን ከሚገኙ ሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ተመካከሩበት። ከዚህ የተነሣ በ1804 የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ተቋቋመ። ማኅበሩ አንግቦ የተነሣው ዓላማ ግልጽ ነበር:- ሰዎች በገዛ ቋንቋቸው በቀላል ወጪ ሊያገኙት የሚችሉት “ማስታወሻ ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ የሌለው” የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማዘጋጀት ነው። የማኅበሩ መሥራቾች በኅዳጎች ላይ የሚሰጠውን ሐሳብ በማስቀረት የመሠረተ ትምህርት ውዝግቦችን ማስወገድ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ አዋልዶችን፣ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ገብቶ መጠመቅን እና የሥላሴ መሠረተ ትምህርትን በሚመለከት በተደጋጋሚ የሐሳብ ልዩነት ታይቶበታል።
ይህ በጋለ ስሜት የተወጠነው ጅምር በፍጥነት እያደገ ሄዶ በ1813 መሰል ማኅበራት በጀርመን፣ በኔዘርላንድ፣ በዴንማርክ እና በሩሲያ ተቋቋሙ። ከጊዜ በኋላ በሌሎች አገራትም ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ተመሥርተዋል። የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ሥራቸውን ሲወጥኑ አብዛኛው የምድር ክፍል የሚጠቀመው በጥቂት ዋና ዋና ቋንቋዎች ብቻ ነው ብለው አስበው ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ይኖራሉ ብለው በሕልማቸውም በውናቸውም አላሰቡትም ነበር! በቀጥታ ከዕብራይስጥና ከግሪክኛ ወደ አገሬው ቋንቋ እንዳይተረጉሙ እነዚህን ቋንቋዎች የሚያውቁት ተርጓሚዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ እጅግ ጥቂት ነበር። በመሆኑም የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ስፖንሰር ያደረጋቸው ትርጉሞችን የሠሩት ተርጓሚዎች ብዙውን ጊዜ ለትርጉም ሥራቸው መሠረት ያደረጉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን ኪንግ ጄምስ ቨርሽንን ነበር።
አንድ ተርጓሚ የገጠመው ፈተና
አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በዕለት ተዕለት ገጠመኞች ላይ የተመሠረቱ ትረካዎችንና ምሳሌዎችን የያዘ ነው። ስውር መልእክት ባላቸው የፍልስፍና ቃላት ከመጻፍ ይልቅ በዚህ ሁኔታ መጻፉ ለትርጉም ሥራው ይበልጥ ቀላል እንዲሆን አድርጎታል። ይሁን እንጂ ሚስዮናውያኑ በመጀመሪያዎቹ ሙከራዎቻቸው ወቅት አንዳንድ ግራ የሚያጋቡ ወይም የሚያስቁ የትርጉም ስህተቶችን ሊሠሩ እንደሚችሉ የታወቀ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ትርጉም በሕንድ ውስጥ በተወሰነ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች አምላክ ሰማያዊ ቀለም ያለው አካል ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓል። “በሰማይ የምትኖር አባታችን” በሚለው መግለጫ ውስጥ ‘በሰማይ የሚኖር’ ለማለት የተጠቀመበት ቃል “ሰማያዊ” ማለትም ቃል በቃል የሰማይ ዓይነት ቀለም ያለው የሚል ነበር!
አንድ ተርጓሚ ሊገጥሙት የሚችሉትን መሰናክሎች በሚመለከት አዶኒራም ጀድሰን በ1819 እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘ለእኛ ፍጹም ባዕድ የሆነ የሐሳብ ሥርዓት ያለውን እንዲሁም ከዚህ በፊት አጋጥሞን ከሚያውቅ ከማንኛውም ቋንቋ ጋር ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የሌላቸው ፊደላትና ቃላት ያሉትን፣ በሌላኛው የምድር ክፍል የሚኖሩ ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ አላንዳች መዝገበ ቃላት ወይም አስተርጓሚ እርዳታ፣ ስለ ቋንቋው በቀሰምናት ጥቂት እውቀት ብቻ በአገሬው አስተማሪነት ለመማር ስንነሳ ምን ያህል ከባድ ሥራ መጀመራችን እንደነበረ ግልጽ ነው!’ እንደ ጀድሰን ያሉት ተርጓሚዎች የሠሩት ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው እንዲሠራጭ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል።—በገጽ 12 ላይ የሚገኘውን ቻርት ተመልከት
አን ጀድሰን አስቸጋሪ በሆነው የትርጉም ሥራ ባሏን ረድታዋለች። ይሁን እንጂ እነዚህ ባልና ሚስት የገጠማቸው ፈተና የትምህርት ችሎታን የሚፈታተን ብቻ አልነበረም። የንጉሡ መኮንኖች አዶኒራምን እየጎተቱ ወደ እስር ቤት ሲወስዱት አን ነፍሰ ጡር ነበረች። አን ባሏን ከእስር ለማስፈታት ለ21 ወራት ጨካኝ ከሆኑት መኮንኖች ጋር በድፍረት ስትሟገት ቆይታለች። ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ከሕመሟ ጋር ተዳምሮ ጤንነቷን አቃውሶት ነበር። አዶኒራም ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ደፋሯ አንና ትንሿ ልጃቸው በትኩሳት በሽታ ሞቱ። የአዶኒራም ልብ በሐዘን ጦር ተወጋ። ያም ሆኖ ግን አምላክ ብርታት እንደሚሰጠው ተማምኖ በትርጉም ሥራው በመግፋት በ1835 በበርማ ቋንቋ ያዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አጠናቀቀ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሌሎች መሰሪ ደባዎች ቀስ በቀስ ብቅ ማለት ጀምረው ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ
በ1800ዎቹ ታላላቅ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውዝግቦች የታዩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የተካሄዱ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የሩሲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በዛርና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ሥራውን ቢጀምርም ከጊዜ በኋላ ማኅበሩ እንዲፈርስና እንዲታገድ አድርገዋል። (ከመታገዱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የማኅበሩ ተቃዋሚዎች በሺህ የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን አቃጥለዋል።) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በግለት የጀመሩትን መጽሐፍ ቅዱስን ለሁሉም የማዳረስ ግብ የኦርቶዶክስ ቀሳውስት ለማዳፈን በቅንዓት መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን የኦርቶዶክስ መሪዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያኒቱንም ሆነ የመንግሥትን ሥልጣን አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት ይወተውቱ ነበር። ሆኖም ብቅ ያለው አብዮታዊ የፖለቲካ ንቅናቄ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለሥልጣን ሥጋት እንደሚፈጥር መጽሐፍ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ሰዎች ተገዥ እንዲሆኑላቸው የሚጠቀሙበት መሣሪያ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለቱም ወገን ጥቃት ደርሶበታል!
በቀጣዮቹ ዓመታትም መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ “ምሁራዊ” ጥቃት ተሰንዝሮበታል። በ1831 ቻርልስ ዳርዊን ወደ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ያደረሰውን ምርምር ለማድረግ አንድ የቡድን ዘመቻ በመምራት የባሕር ጉዞውን ተያያዘው። በ1848 ማርክስና ኤንግልስ ክርስትናን የጭቆና መሣሪያ አድርጎ የሚገልጸውን ኮሙኒስት ማኒፌስቶ አወጡ። በዚሁ ወቅት የተነሡት የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛነትና ኢየሱስን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ባለ ታሪኮች ታሪካዊ እውነተኛነት በሚመለከት ጥያቄዎች ማንሣት ጀመሩ! ይሁን እንጂ አንዳንድ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ያጣጣሉት ጽንሰ ሐሳቦች የተሳሳቱና መሠረተ ቢስ መሆናቸውን በመገንዘብ የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት በምሁራዊ መንገድ ለማረጋገጥ ቆርጠው ተነሡ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ፣ ተሰጥኦውም የነበረው ጀርመናዊው የቋንቋ ሰው ኮንስታንቲን ቮን ቲሸንዶርፍ ነበር።
አዳዲስ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት ለማረጋገጥ አስችለዋል
ቲሸንዶርፍ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ከጥርጣሬ ነፃ ለማድረግ በማሰብ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተጉዟል። ዳርዊን ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ የተባለውን መጽሐፍ ባሳተመበት ዓመት ማለትም በ1859 ቲሸንዶርፍ በሲና ተራራ ሥር በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ በወቅቱ በጥንታዊነቱ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተሟላ ቅጂ አገኘ። ይህ ቅጂ ኮዴክስ ሳይናይቲከስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ጄሮም የላቲን ቩልጌት ትርጉሙን ከማጠናቀቁ ከ50 ዓመታት በፊት እንደተዘጋጀ ይታመናል። ኮዴክሱን ከገዳም ማውጣቱ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ገና አከራካሪ ቢሆንም ቲሸንዶርፍ አሳትሞ ለምሁራን እንዲደርስ አድርጓል።a
ሳይናይቲከስ በመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ከተዘጋጁት ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል አንዱ በመሆኑ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መሠረታዊ ለውጥ እንዳልተደረገባቸው ከማረጋገጡም በላይ ምሁራኑ ከጊዜ በኋላ በተዘጋጁት ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ የተጨመሩትን ስህተቶች ለማግኘት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል የሳይናይቲከስ ቅጂ በ1 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “እርሱ በሥጋ ተገለጠ” ይላል። በወቅቱ ይታወቁ የነበሩት አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ጽሑፎች ግን “እርሱ” ለማለት በገባው የግሪክኛ ቃል ላይ ጥቂት ለውጥ በማድረግ “እርሱ” በሚለው ፋንታ “አምላክ” የሚል ትርጉም ያለው አሕጽሮታዊ ቃል እንዲገባ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የሳይናቲከስ ቅጂ የተዘጋጀው “አምላክ” ብለው ያስነበቡት ማንኛቸውም የግሪክኛ ቅጂዎች ከመዘጋጀታቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ነው። በዚህ መንገድ ከጊዜ በኋላ ጽሑፉን ለመበረዝ ጥረት ተደርጎ እንደነበር አመልክቷል፤ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ሐሳብ የተጨመረው የሥላሴን ትምህርት ለመደገፍ ሲባል ነው።
ቲሸንዶርፍ ይህን ጽሑፍ ካገኘበት ጊዜ ወዲህ ብዙ ጥንታዊ ጽሑፎች ብቅ ብቅ ብለዋል። ዛሬ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑ በድምሩ 6,000 ጥንታዊ ቅጂዎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑ ደግሞ ከ13,000 በላይ ቅጂዎች ይገኛሉ። እነዚህን ቅጂዎች በማነጻጸር የተደረገው ጥናት ሙሉ እምነት ሊጣልበት የሚችል በመጀመሪያው ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ለማግኘት አስችሏል። ምሁሩ ኤፍ ኤፍ ብሩስ እንደገለጹት “በተለያየ ዓረፍተ ነገር መቀመጡ . . . ታሪካዊ እውነታዎችን ወይም የክርስትናን እምነትና ልማድ በሚመለከት ጉልህ የሆነ ጥያቄ አያስነሣም።” መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ተጨማሪ ቋንቋዎች መተርጎሙን በቀጠለ መጠን የተገኘው ይህ ተጨማሪ እውቀት ሰዎችን ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው?
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና መጽሐፍ ቅዱስ
በ1881 ጥቂት ቁጥር ያላቸው ነገር ግን ልባዊ ፍላጎት የነበራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ከጊዜ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በመባል የታወቀውን ማኅበር መሠረቱ። በመጀመሪያ የቲሸንዶርፍን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጨምሮ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ያዘጋጁአቸውን መጽሐፍ ቅዱሶች ያሠራጩ ነበር። ይሁን እንጂ በ1890 የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የመጀመሪያ እትሞችን ስፖንሰር እያደረጉ ማሳተሙን ተያያዙት። በ1926 ማኅበሩ መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ማተሚያዎች ማተም ጀመረ። ይሁን እንጂ የተሻሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የማግኘቱ አስፈላጊነት ጉልህ ሆኖ እየታየ መጥቶ ነበር። ቀደም ባሉት መቶ ዘመናት በአዳዲስ ግኝቶችና በምሁራን ምርምር የተደረሰበት እውቀት ለመረዳት የማይከብድና በተመጣጣኝ ዋጋ በሰዎች እጅ ሊገባ የሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ያስችል ይሆን? የማኅበሩ አባላት ይህንን ግብ በመያዝ በ1946 አዲስ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ለማዘጋጀት ዕቅድ አወጡ።
በብዙ ቋንቋዎች የሚገኝ አንድ ትርጉም
የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የተባለውን የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ተሞክሮ ካላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተውጣጣ አንድ የትርጉም ኮሚቴ ተዋቀረ። ሥራው የተጀመረው በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ሲሆን ከ1950 እስከ 1960 ባሉት ዓመታት በስድስት ጥራዝ ወጥቷል። ከ1963 ወዲህ በተጨማሪ 27 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን አሁንም በሌሎች ቋንቋዎች የትርጉም ሥራው በመካሄድ ላይ ነው። በሌሎች ቋንቋዎችም የሚዘጋጀው ትርጉም ዓላማው ከእንግሊዝኛው የተለየ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ትርጉሙ ትክክለኛ ማለትም በተቻለ መጠን ከመጀመሪያው ሐሳብ ጋር አንድ ዓይነት ሊሆን ይገባል። ከአንድ የተወሰነ የመሠረተ ትምህርት ግንዛቤ ጋር እንዲጣጣም ሲባል ትርጉሙ ሊጣመም አይገባም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ትርጉሙ ወጥነት ሊኖረው ይገባል፤ የሐሳቡ አገባብ እስከፈቀደ ድረስ ለእያንዳንዱ ወሳኝ ቃል የሚሰጠው ትርጉም ተመሳሳይ መሆን አለበት። እንዲህ ያለው አቀራረብ አንባቢው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ ቃላቱን እንዴት እንደተጠቀሙባቸው እንዲያስተውል ይረዳዋል። በሦስተኛ ደረጃ መልእክቱም ሳይሰወር በተቻለ መጠን ትርጉሙ ቃል በቃል ሊቀመጥ ይገባል። ትርጉሙ ቃል በቃል መቀመጡ አንባቢዎቹ የመጀመሪያዎቹን ቋንቋዎች ለዛ በትንሹም ቢሆን እንዲያጣጥሙ የሚያስችል ሲሆን ከዚያ ጋር የተያያዘውን ሐሳብ እንዲያስተውሉም ያስችላቸዋል። እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ ማንኛውም ሰው አንብቦ ሊረዳው የሚችል መሆን ይገባዋል።
የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የእንግሊዝኛ ቅጂ ቃል በቃል የተተረጎመ መሆኑ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም አመቺ እንዲሆን አድርጎታል። ለዚሁ ሲባል በአሁኑ ወቅት የማኅበሩ የትርጉም ቡድኖች ሥራውን የሚያፋጥኑና ይበልጥ ትክክለኛ እንዲሆን የሚያግዙ ዘመናዊ የኮምፒዩተር ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ይህ አሠራር ተርጓሚዎቹ ለእያንዳንዱ ወሳኝ ቃል የቋንቋቸውን ተመሳሳይ ቃል እንዲያሰባስቡ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተሠራበት ለእያንዳንዱ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃል የተሰጠውን የእንግሊዝኛ ፍቺ እንዲያጠኑ ያስችላቸዋል።
በቀጥታ ከዕብራይስጡና ከግሪክኛው ከመተርጎም ይልቅ ከእንግሊዝኛው መተርጎም ጠቃሚ ጎኖች አሉት። የትርጉሙን ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ በሁሉም ቋንቋዎች በመግለጫዎች አጠቃቀም ረገድ ተመሳሳይነት እንዲኖር ያስችላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ከአንድ ጥንታዊ ቋንቋ ዛሬ ወዳሉ የተለያዩ ቋንቋዎች ከመተርጎም ይልቅ ከአንድ ዘመናዊ ቋንቋ ወደሌላው በትክክል ትርጉሙን ማስተላለፍ ይበልጥ ቀላል ስለሆነ ነው። ደግሞም ተርጓሚዎቹም ቢሆኑ ማማከር የሚያስፈልጋቸው ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረን ቋንቋ ተናጋሪዎች ሳይሆን የዘመናዊውን ቋንቋ ተናጋሪዎች ይሆናል ማለት ነው።
ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን ምሥራች
መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ዙሪያ በስፋት በመሠራጨት ረገድ አቻ የለሽ መጽሐፍ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ቆራጥ ወንዶችና ሴቶች በሚመለከት ገና ብዙ ማለት ይቻላል። ላለፉት መቶ ዘመናት ቢያንስ ቢያንስ አራት ቢልዮን መጽሐፍ ቅዱሶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የምድር ነዋሪ በሚናገራቸው ከሁለት ሺህ በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል!
መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ በእኛ ዘመን የአምላክ መንግሥት በምድር ሁሉ እንደሚታወጅ ይገልጻል። ይህንኑ ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንዲቻል ይሖዋ አምላክ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰው እንዲዳረስ በማድረጉ ሥራ እጁን እንዳስገባ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 13:47, 48፤ 24:14) ጥንት የነበሩ ደፋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችና አዘጋጂዎች በሥነ ምግባር ጨለማ ውስጥ በወደቀው ዓለም ብቸኛ የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነውን የአምላክ ቃል ለእኛ ለማስተላለፍ ሲሉ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል፤ እነርሱ የተዉት ምሳሌ የእነርሱን ዓይነት ጠንካራ እምነት ኖሮህ ይህን ቃል እንድታነበው፣ የሕይወትህ መመሪያ እንድታደርገውና ለሌሎች እንድታካፍለው የሚያነሳሳህ ይሁን። አዎን፣ በየዕለቱ በእጅህ ያለውን እምነት የሚጣልበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ተጠቀምበት!—ኢሳይያስ 40:6-8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጥቅምት 15, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ላይ “ኮዴክስ ሳይናይቲከስን ከጥፋት ማዳን” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ያሳየው እድገት
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ብዛት
ቋንቋዎቹ
1 አይሁዳውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ግሪክኛ መተርጎም የጀመሩበት
280 ከዘአበ ገደማ
12 ጄሮም የላቲን ቩልጌትን ያጠናቀቀበት 400 እዘአ ገደማ
35 ጉተንበርግ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት ያጠናቀቀበት 1455 ገደማ
81 የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ምሥረታ 1804
በእነዚህ ዓመታት የነበረው የቋንቋዎቹ ግምታዊ አኃዝ
522
1900
600
700
800
900
1,049
1950
1,100
1,200
1,300
1,471
1970
2,123
1996
2,200
2,300
2,400
[ምንጭ]
ምንጭ:- Christianity Today, United Bible Society
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1995 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀድሰን ታስሮ እየተጎተተ ተወሰደ
[ምንጭ]
From the book Judson the Hero of Burma, by Jesse Page
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቲሸንዶርፍ ሲና ተራራ ሥር በሚገኘው በዚህ ገዳም የነበረውን ውድ የሆነ ጥንታዊ ጽሑፍ ከጥፋት አድኗል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.