አንዳንዶች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ያገኙት እንዴት ነው?
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመጸለይ ልማድ አላቸው። አንዳንዶች ለጸሎታቸው መልስ እንዳገኙ ሆኖ ይሰማቸዋል። ሌሎች ጸሎታቸው ተሰሚነት ስለማግኘቱ ይጠራጠራሉ። ሌሎች ደግሞ መልስ የሚሹላቸው ጥያቄዎች ቢኖሯቸውም ጉዳዩን ለአምላክ በጸሎት ስለማቅረብ አስበው አያውቁም።
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው አምላክ ‘ጸሎት ሰሚ’ መሆኑን ይናገራል። (መዝሙር 65:2) የመጸለይ ልማድ ካለህ ጸሎትህን የምታቀርበው ለእውነተኛው አምላክ ነው? ጸሎቶችህ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉ ናቸው?
በምድር ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ አዎንታዊ ነው። ሆኖም ለጸሎታቸው መልስ ያገኙት እንዴት ነው? ከዚህስ ምን ትምህርት አግኝተዋል?
አምላክ ማን ነው?
በፖርቹጋል የምትኖር አንዲት መምህርት ቀሳውስትና ሴት መነኮሳት የሚሰጡትን ትምህርት የተከታተለች ከመሆኑም በላይ ሃይማኖቷን በቁም ነገር ትይዝ ነበር። ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እንደሆኑ ተነግሯት የነበሩት ልማዶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ሲቀየሩና ከናካቴው ሲተዉ ስትመለከት ግራ ተጋባች። ከቦታ ቦታ መጓዟ በሩቅ ምሥራቅ ያለውን የአምልኮ ሥርዓት የመመልከት አጋጣሚ ሰጣት። በዚህ ጊዜ አንድ እውነተኛ አምላክ ስለ መኖሩ በአእምሮዋ ጥያቄ ይጉላላ ጀመር። አምላክን ማምለክ ያለባት እንዴት ነው? የቤተ ክርስቲያኒቱ ቄስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስላነበበችው ነገር የምታቀርብላቸውን ጥያቄዎች ያጣጥሉባት ስለነበር በሁኔታው አልተደሰተችም።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህች መምህርት በምትኖርበት ከተማ ምእመናኑ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳይነጋገሩ የሚያስጠነቅቅ በራሪ ወረቀት አሰራጭታ ነበር። ሆኖም መምህርቷ አሁንም ለጥያቄዎቿ መልስ ትፈልግ ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ መጥተው ሲያነጋግሯት ያዳመጠቻቸው ሲሆን ጉዳዩም ትኩረቷን ሳበው። ከእነርሱ ጋር ስትወያይ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ይህች ሴት ለነበሯት ብዙ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። በየሳምንቱ በርካታ ጥያቄዎች አዘጋጅታ ትጠብቃቸው ነበር። ከጥያቄዎቿ መካከል እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ ነው? የአምላክ ስም ማን ነው? ለአምልኮ በምስሎች መጠቀምን አምላክ ይፈቅዳል? የሚሉትና ሌሎችም ይገኙበት ነበር። ምሥክሮቹ መልስ የሚሰጧት እንዲያው ከራሳቸው ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ መሆኑን አስተዋለች፤ በምትማረው ነገር ከመገረሟም በላይ በጣም ተደሰተች። የነበሯት በርካታ ጥያቄዎች ቀስ በቀስ ተመለሱላት። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ‘እውነተኛ አምላኪዎች’ እንደተናገረው ይሖዋን በእውነትና በመንፈስ በማምለክ ላይ ትገኛለች።—ዮሐንስ 4:23
በስሪ ላንካ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው በጋራ የሚያነብቡ ቢሆንም በጣም ያሳስቧቸው ለነበሩት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አልቻሉም። የቤተ ክርስቲያኑን ቄስ እንዲረዷቸው ቢጠይቁም ለጥያቄያቸው መልስ አላገኙም። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው አነጋገሯቸውና ጠቃሚ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ሰጧቸው። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ ስለሰጧቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ። ከጥናታቸው የሚማሩትን ነገር እየወደዱት መጡ።
ይሁንና ሚስትየዋ በልጅነቷ በቤተ ክርስቲያን የተማረቻቸው መሠረተ ትምህርቶች ‘ብቸኛው እውነተኛው አምላክ’ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት መሆኑን እንዳትቀበል እንቅፋት ሆኑባት። (ዮሐንስ 17:1, 3) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር እኩል እንደሆነና ይህ ፈጽሞ የማይመረመር “ምሥጢር” እንደሆነ ተነግሯት ነበር። የኢየሱስን ማንነት እንዲገልጽላት በመጠየቅ የይሖዋን ስም ጠቅሳ ከልቧ አምርራ ጸለየች። ከዚያም ከጉዳዩ ጋር የሚያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ዳግመኛ በጥንቃቄ መረመረች። (ዮሐንስ 14:28፤ 17:20, 21፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) በዚህ ጊዜ ልክ ዓይኗ እንደበራላት ያህል እውነተኛው አምላክ የሰማይና የምድር ፈጣሪና የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው ይሖዋ መሆኑን በግልጽ ተረዳች።—ኢሳይያስ 42:8፤ ኤርምያስ 10:10-12
መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው?
ኢዮብ ከባድ መከራ ደርሶበት ነበር። ልጆቹ በሙሉ በአውሎ ነፋስ ሳቢያ ሞቱ፤ እርሱም ለድህነት ተዳረገ። እንዲሁም በአሰቃቂ በሽታ ይሰቃይ የነበረ ከመሆኑም በላይ የሐሰት ወዳጆቹ ያሳደሩበትንም ጫና ለመቋቋም ተገዷል። ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስበት ማስተዋል የጎደለው ንግግር ተናገረ። (ኢዮብ 6:3) አምላክ ግን ኢዮብ የነበረበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቷል። (ኢዮብ 35:15) በኢዮብ ልብ ውስጥ የነበረውን ስለሚያውቅ የሚያስፈልገውን ምክር ሰጥቶታል። በዛሬው ጊዜም ለሰዎች እንዲሁ ያደርጋል።
በሞዛምቢክ የሚኖረው ካስትሮ እናቱ የሞተችበት ገና የአሥር ዓመት ልጅ እያለ ነበር። በሐዘን ቅስሙ ስለተሰበረ “እናታችን በትናን የሞተችው ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ተፈጠረበት። ያሳደጉት ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ወላጆች ቢሆኑም ሁኔታው ግራ እንዲጋባ አደረገው። መጽናኛ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? በቺቼዋ ቋንቋ የተዘጋጀ አንድ ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡና ያነበበውን ከታላላቅ ወንድሞቹ ጋር መወያየቱ መጽናኛ አስገኘለት።
ካስትሮ እናቱ የሞተችው አምላክ ስለፈረደባት ሳይሆን በወረሰችው አለፍጽምና ምክንያት መሆኑን እያደር ተገነዘበ። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) መጽሐፍ ቅዱስ በትንሣኤ አማካኝነት እናቱን እንደገና ማግኘት እንደሚችል እምነት ስላሳደረበት ይህ ተስፋ ትልቅ መጽናኛ ሆነለት። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) የሚያሳዝነው ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ አባቱ ሞተ። በዚህ ጊዜ ግን ሐዘኑን ለመቋቋም የተሻለ ጥንካሬ ነበረው። በዛሬው ጊዜ ካስትሮ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ያለው ሲሆን እርሱን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛል። የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ደስተኛ እንደሆነ ይመሰክሩለታል።
የሚያፈቅሩትን ሰው በሞት የተነጠቁ በርካታ ሰዎች ካስትሮን ካጽናኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መጽናኛ አግኝተዋል። በክፉ ሰዎች ድርጊት የተነሳ ከባድ መከራ የደረሰባቸው አንዳንዶች እንደ ኢዮብ “ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ?” በማለት ይጠይቃሉ። (ኢዮብ 21:7) አምላክ በቃሉ አማካኝነት ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ሰዎች ከልብ የሚያዳምጡ ከሆነ እርሱ ሁኔታዎችን የሚይዝበት መንገድ ለራሳቸው እንደሚጠቅም ይገነዘባሉ።—2 ጴጥሮስ 3:9
በዩናይትድ ስቴትስ ያደገችው ባርባራ የጦርነትን አስከፊነት በገዛ ዓይኗ ባትመለከትም በልጅነት ዕድሜዋ በዓለም ዙሪያ በርካታ አገሮች በጦርነት ላይ ነበሩ። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ዘግናኝ ድርጊቶች ዕለታዊ የዜና ዘገባ ሆነው ነበር። በትምህርት ቤት ሳለች ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ስለተፈጸሙ ታሪካዊ ክስተቶች ስትማር በጣም ግራ ትጋባ ነበር። እነዚህ ክስተቶች እንዲፈጸሙ ያደረገው ምንድን ነው? አምላክ በምድር ላይ ለሚፈጸሙት ነገሮች ግድ ይሰጠዋል? አምላክ መኖሩን ብታምንም ስለ እርሱ የነበራት ስሜት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነበር።
ይሁን እንጂ ባርባራ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመገናኘቷ ለሕይወት የነበራት አመለካከት ቀስ በቀስ ተለወጠ። ምሥራቹን ሲነግሯት ያዳመጠቻቸው ከመሆኑም በላይ ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረች ሲሆን በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይም ተገኘች። በተጨማሪም የተለያዩ ምሥክሮች ለምትጠይቃቸው ጥያቄዎች የሚሰጧት መልስ እርስ በእርሱ እንደማይጋጭ አስተዋለች። እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሚናገሩት እርስ በእርሱ ይስማማል።
ምሥክሮቹ ዓለም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንዳለና የእርሱን መንፈስ እንደሚያንጸባርቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እየጠቀሱ አሳዩአት። (ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 2:1-3፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እንቆቅልሽ ሆነውባት የነበሩት ታሪካዊ ክስተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት የተነገሩ መሆናቸውን ገለጹላት። (ዳንኤል ምዕራፍ 2, 7 እና 8) አምላክ ወደፊት የሚሆነውን የማወቅ ችሎታ ስላለው እነዚህን ክስተቶች በትንቢት አስነግሯል። ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ አንዳንዶቹ እንዲፈጸሙ ያደረገው አምላክ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ እንዲደርሱ ፈቅዷል። ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ስለሚፈጸሙት መልካምም ሆኑ መጥፎ ነገሮች በትንቢት እንደተናገረና ትርጉማቸውንም በግልጽ እንደሚያብራራ ነገሯት። (ማቴዎስ 24:3-14) መከራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አስረዷት።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4
ባርባራ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው ይሖዋ አምላክ ባይሆንም ሰዎች ሕጉን እንዲታዘዙ በማስገደድ ይህ መከራ እንዳይደርስባቸው እንደማያደርግ ተገነዘበች። (ዘዳግም 30:19, 20) አምላክ ለዘላለም በደስታ መኖር የምንችልበትን ዝግጅት አድርጎልናል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ከእርሱ የጽድቅ ጎዳና ጋር ተስማምተን እንኖር እንደሆነና እንዳልሆነ የምናሳይበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። (ራእይ 14:6, 7) ባርባራ አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች ለመማርና ከእነርሱ ጋር ተስማምታ ለመኖር ወሰነች። እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የእውነተኛ ተከታዮቹ መለያ እንደሆነ የተናገረለትን ፍቅር እንደሚያሳዩ ተመለከተች።—ዮሐንስ 13:34, 35
አንተም እርሷ እርዳታ ካገኘችበት ዝግጅት መጠቀም ትችላለህ።
ዓላማ ያለው ሕይወት
በኑሮ የተሳካላቸው የሚመስሉ ሰዎችም ጭምር ግራ ለሚያጋቧቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በብሪታኒያ የሚኖር ማቲው የተባለ ወጣት እውነተኛውን አምላክና የሕይወትን ዓላማ የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። አባቱ የሞተበት የ17 ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ከዚያ በኋላም ማቲው በሙዚቃ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያዘ። ከዚያም ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረው አኗኗሩ ትርጉም የለሽ ሆነበት። መኖሪያ ቦታ ቀይሮ ወደ ለንደን ከመጣ በኋላ እርካታ የሞላበት የሕይወት ጎዳና ለማግኘት ባደረገው ጥረት አደገኛ ዕፅ መውሰድና የምሽት ጭፈራ ቤቶች መሄድ የጀመረ ሲሆን በኮከብ ቆጠራና በመናፍስታዊ ሥራዎች ተጠላለፈ። ከዚህም በላይ ዜን ቡድሂዝምንና ሌሎች ፍልስፍናዎችን ይከተል ጀመር። ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት እውነትን ለማግኘት እንዲረዳው አምላክን ተማጸነ።
ከሁለት ቀናት በኋላ ማቲው የድሮ ጓደኛውን አግኝቶ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ነገረው። ጓደኛው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና የነበረ ሲሆን 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን ባነበበለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የዓለምን ሁኔታ በትክክል የገለጸበት መንገድ አስገረመው። የተራራውን ስብከት ሲያነብ መልእክቱ ልቡን ነካው። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) የይሖዋ ምሥክሮችን የሚነቅፍ ጽሑፍ አንብቦ ስለነበር በመጀመሪያ በስብሰባ ላይ ለመገኘት ቢያመነታም በኋላ ግን በአቅራቢያው ወደሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ለመሄድ ወሰነ።
ማቲው በስብሰባው ላይ በሰማው ትምህርት ስለተደሰተ ከአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። እየተማረ ያለው ነገር ቀደም ሲል ወደ አምላክ ላቀረበው ጸሎት የተሰጠው መልስ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ይሖዋን የማያስደስቱ ልማዶቹን በመተዉም ተጠቀመ። ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት እያዳበረ ሲሄድ ከአምላክ መመሪያ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ጥረት ያደርግ ጀመር። ማቲው እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ዓላማ እንዳለው ተገንዝቧል።—መክብብ 12:13
ማቲውም ሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሌሎች ሰዎች ደስታ የሞላበት ሕይወት ማግኘታቸው አስቀድሞ የተወሰነ ነገር አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ አምላክ መመሪያዎቹን በደስታ ለመታዘዝ የሚመርጡ ሰዎችን በሙሉ የሚያቅፍ ፍቅራዊ ዓላማ እንዳለው ተገንዝበዋል። (ሥራ 10:34, 35) ይህ ዓላማ ጦርነት፣ በሽታ፣ ረሃብ፣ አልፎ ተርፎም ሞት በሌለበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖርን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 2:4፤ 25:6-8፤ 33:24፤ ዮሐንስ 3:16) ይህን ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥበት ስብሰባ ላይ በመገኘት አስደሳች ሕይወት ስለሚገኝበት መንገድ ተጨማሪ እውቀት መቅሰም ትችላለህ። በዚያ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስሙን በመጥራት ለአምላክ ልባዊ ጸሎት አቅርብ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቃሉን በትክክል ከሚያስተምሩ ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥና
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ተገኝ
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ተራራ ወጪ፦ Chad Ehlers/Index Stock Photography