ከኢየሱስ ምን እንማራለን?
ስለ እውነተኛው አምልኮ
አምላክ ሁሉንም ሃይማኖት ይቀበላል?
▪ ኢየሱስ በሐሰት ሃይማኖት ለተታለሉ ሰዎች አዝኖላቸው ነበር። ‘በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ስለሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት’ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 7:15) አንዳንድ ሰዎች እኩይ ተግባራቸውን ለማስፈጸም ሃይማኖትን እንደ መሣሪያ እንደሚጠቀሙበት አስተውለህ ታውቃለህ?
ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው እውነት ጋር የሚጋጭ ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም ኢየሱስ “የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው” በማለት አምላክ የተናገረው ሐሳብ ግብዝ በሆኑ አንዳንድ የሃይማኖት ሰዎች ላይ እንደሚሠራ ገልጿል።—ማቴዎስ 15:9
እውነተኛ ሃይማኖት አለ?
▪ ኢየሱስ ሰማርያ ውስጥ በሐሰት ሃይማኖት ተታልላ የነበረች አንድ ሴት ባገኘ ጊዜ እንደሚከተለው ብሏታል፦ “እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ፤ . . . እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት እየመጣ ነው፤ . . . ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል።” (ዮሐንስ 4:22, 23) በእርግጥም እውነተኛ አምልኮ እንዳለ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል።
ኢየሱስ “በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ እሱ የሚያስተምረው ሃይማኖት ብቻ እውነተኛ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 8:28) በመሆኑም “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:6) የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች ወደ አብ የሚቀርቡበት መንገድ አንድ ዓይነት መሆን ስላለበት በአንድ እውነተኛ ሃይማኖት ሥር መታቀፍ ይኖርባቸዋል።
እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
▪ ክርስቲያን የሚባለው የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ የሚከተል ሰው ነው። የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉ ሰዎችን ያላንዳች ችግር ለይተህ እንድታውቅ የሚረዱህን አራት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ ‘ስምህን አሳውቄአለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 17:26) እውነተኛ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ።
2. ኢየሱስ ስለ ይሖዋ መንግሥት የሰበከ ከመሆኑም ባሻገር ደቀ መዛሙርቱ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ልኳቸው ነበር። “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር የሚገባው ማን እንደሆነ ፈልጉ” ብሏቸዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለተከታዮቹ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:7, 11፤ 28:19) በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ስላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችን በቀላሉ ለይተህ ማወቅ ትችላለህ።
3. ኢየሱስ በፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልነበረም። ስለዚህ ተከታዮቹን በሚመለከት “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል [አይደሉም]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:14) የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ገለልተኞች መሆን ይኖርባቸዋል።
4. ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ፍቅር የራሱን ጥቅም መሥዋዕት እንዲያደርግ አነሳስቶታል። “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ስለሚዋደዱ በጦርነት ውስጥ አይካፈሉም።
እውነተኛው ሃይማኖት ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
▪ እውነተኛው ሃይማኖት የሚጠይቃቸውን ነገሮች ለማድረግ በመጀመሪያ ይሖዋን በሚገባ ማወቅ ይኖርብሃል። ስለ አምላክ ያገኘኸው እውቀት ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንድትመራ የሚያስችልህ ከመሆኑም በላይ ልብህ በአምላክ ፍቅር እንዲሞላ ያደርጋል። ይሖዋ ደግሞ እሱን ለሚወዱ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ቃል ገብቷል። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተ . . . እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ይህን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ላይ ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።”—ማቴዎስ 7:15