ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 1
ዝም ለማለት ጊዜ አለው።—መክ. 3:7
ንግግራችንን ካልተቆጣጠርን ብዙ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። ለምሳሌ ሥራችን በታገደበት አገር ከሚኖር ወንድም ጋር ብንገናኝ በዚያ አገር ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ በተመለከተ ዝርዝር ነገሮችን እንዲነግረን ለመጠየቅ እንፈተን ይሆን? እንዲህ የምናደርገው በቅን ልቦና ተነሳስተን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ወንድሞቻችንን እንወዳቸዋለን እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ያሳስበናል። በተጨማሪም ስለ እነሱ ስንጸልይ አንዳንድ ነገሮችን ለይተን መጥቀስ እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና በዚህ ወቅት ከመናገር መታቀብ ይኖርብናል። ሚስጥራዊ መረጃ ያለው ወንድማችን መረጃውን እንዲነግረን ብንጎተጉተው ለእሱም ሆነ ሚስጥራቸውን እንደሚጠብቅላቸው ለሚተማመኑበት ወንድሞችና እህቶች ፍቅር እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግራቸው እንዲባባስ የሚያደርግ ነገር ማድረግ አንፈልግም። በተመሳሳይም እንዲህ ባለው አገር ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች በዚያ አገር የሚከናወነውን አገልግሎትና ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መናገራቸው ተገቢ አይሆንም። w20.03 21 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2
መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።—ዘፍ. 3:4
አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኖረው እንዲሞቱ አስቦ አልነበረም። አዳምና ሔዋን ለዘላለም መኖር ከፈለጉ ግን ይሖዋ የሰጣቸውን ቀላል መመሪያ መታዘዝ ነበረባቸው፤ መመሪያው የሚከተለው ነበር፦ “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍ. 2:16, 17) ይሁንና ሰይጣን ጣልቃ ገብቶ ችግር ፈጠረ። በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነገራት። የሚያሳዝነው፣ ሔዋን የተነገራትን ውሸት በማመን ፍሬውን በላች። በኋላ ላይ ባሏም ፍሬውን በላ። (ዘፍ. 3:6) በዚህ መልኩ ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ላይ ነገሡ። (ሮም 5:12) አምላክ በተናገረው መሠረት አዳምና ሔዋን ሞቱ። ሰይጣን ግን ስለ ሞት ውሸት መናገሩን አላቆመም። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ውሸቶችን ማስፋፋት ጀመረ። ከእነዚህ ውሸቶች መካከል አንዱ ‘ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ አለች’ የሚለው ትምህርት ነው። በተለያየ መልኩ የሚነገረው ይህ ውሸት እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ ሲሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች አሳስቷል።—1 ጢሞ. 4:1፤ w19.04 14-15 አን. 3-4
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3
ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ እናገር፣ እንደ ልጅ አስብ እንዲሁም እንደ ልጅ አመዛዝን ነበር።—1 ቆሮ. 13:11
ልጆች የማሰብ፣ የማመዛዘን ወይም አደጋ የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን አውቆ ከእነዚህ የመራቅ ችሎታቸው ሙሉ በሙሉ አልጎለበተም። በመሆኑም ሕፃናትን የሚያስነውሩ መሠሪ ሰዎች በቀላሉ ሊያታልሏቸው ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ለልጆቹ አደገኛ ውሸቶችን በመንገር ሊያታልሏቸው ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ ጥፋተኞቹ ልጆቹ ራሳቸው እንደሆኑ፣ የተፈጠረውን ነገር ለማንም መናገር እንደሌለባቸው፣ ቢናገሩም እንኳ የሚሰማቸው ወይም ግድ የሚሰጠው አንድም ሰው እንደማይኖር አሊያም በአንድ ልጅና በአንድ አዋቂ መካከል የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ድርጊት ምንም ስህተት እንደሌለውና ተገቢ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ ይነግሯቸው ይሆናል። ልጆቹ የተነገራቸው ነገር ውሸት እንደሆነ የሚያውቁት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ውሸቶች የተነገሯቸው ልጆች ንጽሕናቸው እንደጎደፈ፣ ምንም እንደማይጠቅሙ፣ የሚወዳቸው ሰው እንደሌለ ወይም ማጽናኛ ማግኘት እንደማይገባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር ፆታዊ ጥቃት ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ምንም አያስገርምም። የምንኖረው ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” በሆኑበት እንዲሁም “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” በሚሄዱበት በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1-5, 13፤ w19.05 15 አን. 7-8