-
ማቴዎስ 12:1-8አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
12 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል አለፈ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ።+ 2 ፈሪሳውያን ይህን ባዩ ጊዜ “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት።+ 3 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁም?+ 4 ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር+ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እንዲበሉ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ አልበሉም? 5 ደግሞስ ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም?+ 6 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 7 ይሁንና ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን+ እንጂ መሥዋዕትን+ አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። 8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”+
-
-
ማርቆስ 2:23-28አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
23 በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ አብረውት ይሄዱ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።+ 24 በመሆኑም ፈሪሳውያን “ተመልከት! በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?” አሉት። 25 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት የሚበላው ባጣ ጊዜ እንዲሁም እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?+ 26 ሊቀ ካህናት ስለሆነው ስለ አብያታር+ በሚናገረው ታሪክ ላይ ዳዊት ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ማንም እንዲበላ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩትም እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?” 27 ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሰጠ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም።+ 28 በመሆኑም የሰው ልጅ የሰንበትም እንኳ ጌታ ነው።”+
-