ሐሙስ፣ መስከረም 26
መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ።—ዕብ. 13:16
በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሙታን ይነሳሉ፤ እንዲሁም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። ይሖዋ ‘ጻድቃን ናቸው’ ብሎ የሚፈርድላቸው ሰዎች “ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝ. 37:10, 11, 29) በጣም ደስ የሚለው ደግሞ “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮ. 15:26) የዘላለም ሕይወት ተስፋችን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ተስፋ ነው። ይህ ተስፋ በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ይሁንና ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን፣ እሱን ለማገልገል የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ያለን ፍላጎት ሊሆን አይገባም። ለይሖዋና ለኢየሱስ ታማኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ለእነሱ ያለን ጥልቅ ፍቅር ነው። (2 ቆሮ. 5:14, 15) እንዲህ ያለው ፍቅር፣ እነሱን ለመምሰልና ስለ ተስፋችን ለሌሎች ለመናገር ያነሳሳናል። (ሮም 10:13-15) ከራስ ወዳድነት ነፃ ስንሆንና ልግስናን ስናዳብር ይሖዋ ለዘላለም ወዳጆቹ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች እንሆናለን። w22.12 6-7 አን. 15-16
ዓርብ፣ መስከረም 27
የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።—2 ጢሞ. 3:12
ስደት ሰላም የሚያስገኙልንን የተለያዩ ነገሮች ሊያሳጣን ይችላል። ‘ነገ ምን ይደርስብን ይሆን’ ብለን በመስጋት ልንጨነቅ እንችላለን። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ያም ቢሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ስደት ተከታዮቹን ሊያሰናክላቸው እንደሚችል ተናግሯል። (ዮሐ. 16:1, 2) ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን ቢናገርም ታማኝነታችንን መጠበቅ እንደምንችልም ዋስትና ሰጥቶናል። (ዮሐ. 15:20፤ 16:33) በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ከፍተኛ ገደብ በሚጣልበት ወቅት ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከሽማግሌዎች መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። የእነዚህ መመሪያዎች ዓላማ እኛን ከጉዳት መጠበቅ፣ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችንን እንድንቀጥል ማድረግ እንዲሁም ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን መስበካችንን እንድንቀጥል መርዳት ነው። የተሰጠህን መመሪያ ለመታዘዝ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። (ያዕ. 3:17) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማወቅ ለማይገባቸው ሰዎች እንዳትናገር ተጠንቀቅ።—መክ. 3:7፤ w22.12 20-21 አን. 14-16
ቅዳሜ፣ መስከረም 28
ያንኑ ትጋት [አሳዩ]።—ዕብ. 6:11
ኢየሱስ በመላው ምድር ላይ ስለ አምላክ መንግሥት ለሚሰብኩ ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። እሱ የበኩሉን አድርጓል። በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት እንዴት እንደምንሰብክ ያሠለጥነናል፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለማስፋፋት የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች ያቀርብልናል። (ማቴ. 28:18-20) እኛም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ትጉ በመሆን እንዲሁም ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ በንቃት በመጠባበቅ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። በዕብራውያን 6:11, 12 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ተስፋችንን “እስከ መጨረሻው” አጥብቀን እንይዛለን። ይሖዋ የሰይጣንን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት ወስኗል። ያ ጊዜ ሲመጣ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ትንቢቶች በሙሉ ያለአንዳች ጥርጥር እንዲፈጸሙ ያደርጋል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የሥርዓቱ ፍጻሜ እንደዘገየ ሊሰማን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ ቀን “አይዘገይም!” (ዕን. 2:3) እንግዲያው ‘የሚያድነንን አምላክ በትዕግሥት’ እንዲሁም ‘በጉጉት ለመጠባበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሚክ. 7:7፤ w23.02 19 አን. 15-16