ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ በጊቲት። የዳዊት ማህሌት።
8 ጌታችን ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ በመላው ምድር ላይ ምንኛ የከበረ ነው፤
ግርማህ ከሰማያትም በላይ ከፍ ከፍ እንዲል አድርገሃል!+
2 ከባላጋራዎችህ የተነሳ፣
ከልጆችና ከሕፃናት አፍ በሚወጡ ቃላት+ ብርታትህን አሳየህ፤
ይህም ጠላትንና ተበቃይን ዝም ለማሰኘት ነው።
3 የጣቶችህን ሥራ ሰማያትን፣
አንተ የሠራሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን ስመለከት፣+
4 ታስበው ዘንድ ሟች ሰው ምንድን ነው?
ትንከባከበውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?+
5 ከመላእክት በጥቂቱ አሳነስከው፤
የክብርና የግርማ ዘውድም ደፋህለት።
6 በእጆችህ ሥራዎች ላይ ሥልጣን ሰጠኸው፤+
ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አደረግክለት፦
7 መንጎቹንና ከብቶቹን ሁሉ፣
እንዲሁም የዱር አራዊትን፣+
8 የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሣዎችን፣
በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትን ሁሉ ከእግሩ በታች አደረግክለት።
9 ጌታችን ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ በመላው ምድር ላይ ምንኛ የከበረ ነው!