ሁለተኛ ዜና መዋዕል
15 የአምላክ መንፈስ በኦዴድ ልጅ በአዛርያስ ላይ ወረደ። 2 እሱም ከአሳ ጋር ለመገናኘት ወጥቶ እንዲህ አለው፦ “አሳ ሆይ፣ ይሁዳና ቢንያም ሁሉ ስሙኝ! እናንተ ከእሱ ጋር እስከሆናችሁ ድረስ ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤+ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤+ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።+ 3 እስራኤል ያለእውነተኛው አምላክ፣ ያለአስተማሪ ካህንና ያለሕግ ብዙ ዘመን* አሳልፏል።+ 4 በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ተመልሰው ፈለጉት፤ እሱም ተገኘላቸው።+ 5 በዚያ ዘመን በሰላም መጓዝ የሚችል ሰው አልነበረም፤* ምክንያቱም በየክልሉ በሚኖሩት ሰዎች ሁሉ መካከል ከፍተኛ ሁከት ነበር። 6 አምላክ በተለያየ ችግር ያውካቸው ስለነበር አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር፣ አንዱ ከተማም ሌላውን ከተማ ያደቅ ነበር።+ 7 እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ ተስፋም አትቁረጡ።”*+
8 አሳ ይህን ቃልና ነቢዩ ኦዴድ የተናገረውን ትንቢት ሲሰማ ተበረታታ፤ አስጸያፊ የሆኑትን ጣዖቶችም ከይሁዳና ከቢንያም ምድር ሁሉ እንዲሁም በተራራማው የኤፍሬም ክልል ከያዛቸው ከተሞች አስወገደ፤+ ከይሖዋ ቤት በረንዳ ፊት ለፊት የነበረውን የይሖዋን መሠዊያም አደሰ።+ 9 እሱም ይሁዳንና ቢንያምን ሁሉ እንዲሁም ከኤፍሬም፣ ከምናሴና ከስምዖን መጥተው ከእነሱ ጋር የተቀመጡትን የባዕድ አገር ሰዎች ሰበሰበ፤+ አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሆነ ባዩ ጊዜ በርካታ የባዕድ አገር ሰዎች እስራኤልን ትተው ወደ እሱ መጥተው ነበር። 10 በመሆኑም አሳ በነገሠ በ15ኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11 በዚያም ቀን፣ ካመጡት ምርኮ ላይ 700 ከብቶችንና 7,000 በጎችን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 12 በተጨማሪም የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው* ለመፈለግ ቃል ኪዳን ገቡ።+ 13 የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን የማይፈልግ ማንኛውም ሰው ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንድም ሆነ ሴት እንዲገደል ተስማሙ።+ 14 በታላቅ ድምፅ፣ በእልልታ፣ በመለከትና በቀንደ መለከት ለይሖዋ ማሉ። 15 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በሙሉ ልባቸው ስለማሉ በመሐላው ሐሴት አደረጉ፤ አምላክንም ከልባቸው ፈለጉት፤ እሱም ተገኘላቸው፤+ ይሖዋም በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው እረፍት ሰጣቸው።+
16 ሌላው ቀርቶ ንጉሥ አሳ አያቱ ማአካ+ ለማምለኪያ ግንዱ* አምልኮ ጸያፍ ጣዖት ሠርታ ስለነበር ከእመቤትነቷ* ሻራት።+ ከዚያም አሳ፣ አያቱ የሠራችውን ጸያፍ ጣዖት ቆርጦ በማድቀቅ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።+ 17 ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ግን ከእስራኤል አልተወገዱም ነበር።+ ይሁንና አሳ በሕይወት ዘመኑ* ሁሉ በሙሉ ልቡ ተመላልሷል።*+ 18 እሱና አባቱ የቀደሷቸውን ነገሮች ይኸውም ብሩን፣ ወርቁንና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት አስገባ።+ 19 እስከ 35ኛው የአሳ ዘመነ መንግሥት ድረስ ጦርነት አልነበረም።+