55 እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ+ ኑ፤ ወደ ውኃው ኑ!+
እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ!
አዎ፣ ኑና ያለገንዘብ፣ ያለዋጋም የወይን ጠጅና ወተት+ ግዙ።+
2 ምግብ ላልሆነ ነገር ለምን ገንዘባችሁን ታወጣላችሁ?
እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን ታባክናላችሁ?
እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤+
ምርጥ ምግብ በመብላትም ሐሴት ታደርጋላችሁ።+
3 ጆሯችሁን አዘንብሉ፤ ወደ እኔም ኑ።+
አዳምጡ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤
ለዳዊት ካሳየሁት የማይከስም ታማኝ ፍቅር+ ጋር በሚስማማ ሁኔታ
ከእናንተ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።+
4 እነሆ፣ ለብሔራት ምሥክር፣+
መሪና+ አዛዥ+ አድርጌዋለሁ።
5 እነሆ፣ የማታውቀውን ብሔር ትጠራለህ፤
የማያውቅህ ብሔርም ለአምላክህ ለይሖዋና ለእስራኤል ቅዱስ ሲል
ወደ አንተ ሮጦ ይመጣል፤+
ምክንያቱም እሱ ክብር ያጎናጽፍሃል።+
6 ይሖዋን በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት።+
በቅርብም ሳለ ጥሩት።+
7 ክፉ ሰው መንገዱን፣
መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤+
ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤+
ይቅርታው ብዙ ነውና።+
8 “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣
መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና”+ ይላል ይሖዋ።
9 “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ
መንገዴ ከመንገዳችሁ፣
ሐሳቤም ከሐሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።+
10 ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣
ምድርን በማራስ እንድታበቅልና እንድታፈራ፣
ለዘሪው ዘርን፣ ለበላተኛውም ምግብን እንድትሰጥ ሳያደርግ ወደመጣበት እንደማይመለስ ሁሉ፣
11 ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ እንዲሁ ይሆናል።+
ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ያደርጋል፣+
የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ
ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም።+
12 በታላቅ ደስታ ትወጣላችሁና፤+
በሰላምም ትመለሳላችሁ።+
ተራሮቹና ኮረብቶቹ በደስታ በፊታችሁ እልል ይላሉ፤+
የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ።+
13 በቁጥቋጦ ፋንታ የጥድ ዛፍ ይበቅላል፤+
በሳማም ፋንታ የአደስ ዛፍ ይበቅላል።
የይሖዋ ስም እንዲገን ያደርጋል፤+
እንዲሁም ፈጽሞ የማይጠፋ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”