ሁለተኛ ነገሥት
20 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር።+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህ ስለማይቀር ለቤተሰብህ መመሪያ ስጥ።’”+ 2 በዚህ ጊዜ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ፦ 3 “እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ እንዲሁም በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።”+ ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።
4 ኢሳይያስ ገና ወደ መካከለኛው ግቢ ሳይወጣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦+ 5 “ተመልሰህ ሂድና የሕዝቤ መሪ የሆነውን ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ። እንባህንም አይቻለሁ።+ ስለሆነም እፈውስሃለሁ።+ በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት ትወጣለህ።+ 6 እኔም በዕድሜህ* ላይ 15 ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ ደግሞም አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤+ ስለ ራሴና ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል ከተማዋን እጠብቃታለሁ።”’”+
7 ከዚያም ኢሳይያስ “የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡ” አለ። ጥፍጥፉንም አምጥተው እባጩ ላይ አደረጉለት፤ እሱም ቀስ በቀስ እየተሻለው ሄደ።+
8 ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “ይሖዋ እንደሚፈውሰኝና በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት እንደምወጣ ማወቅ የምችልበት ምልክት ምንድን ነው?”+ ሲል ጠየቀው። 9 ኢሳይያስም መልሶ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያሳየው ይሖዋ የሰጠህ ምልክት ይህ ነው፦ ጥላው በደረጃው* ላይ አሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ትፈልጋለህ ወይስ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” አለው።+ 10 ሕዝቅያስም “ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መመለሱ ግን ቀላል አይደለም” አለ። 11 ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ይሖዋ ጮኸ፤ እሱም በአካዝ ደረጃ ላይ ወደ ታች ወርዶ የነበረው ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ።+
12 በዚያን ጊዜ የባላዳን ልጅ የሆነው የባቢሎን ንጉሥ ቤሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ መታመሙን ሰምቶ ስለነበር ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።+ 13 ሕዝቅያስም ለመልእክተኞቹ ጥሩ አቀባበል አደረገላቸው፤* ከዚያም ግምጃ ቤቱን ሁሉ ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውንና በግምጃ ቤቶቹ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው።+ ሕዝቅያስ በቤቱም* ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።
14 ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።+ 15 ቀጥሎም “በቤትህ* ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ* ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።
16 በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ቃል ስማ፦+ 17 ‘እነሆ፣ በቤትህ* ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል።+ አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’ ይላል ይሖዋ። 18 ‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤+ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”+
19 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው”+ አለው። አክሎም “በእኔ የሕይወት ዘመን* ሰላምና መረጋጋት* መኖሩ መልካም ነው” አለ።+
20 የቀረው የሕዝቅያስ ታሪክ፣ ኃያልነቱ ሁሉ እንዲሁም ኩሬውንና+ ቦዩን ሠርቶ ውኃው ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ያደረገበት መንገድ+ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም? 21 በመጨረሻም ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ምናሴ+ ነገሠ።+