ዕዝራ
1 በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦+
2 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤+ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።+ 3 ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ ቤቱ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን* የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤትም መልሶ ይገንባ፤ እሱ እውነተኛ አምላክ ነው። 4 በየትኛውም ስፍራ የባዕድ አገር ሰው ሆኖ የሚኖረውን+ ማንኛውንም ሰው፣ ጎረቤቶቹ* በኢየሩሳሌም ለነበረው ለእውነተኛው አምላክ ቤት ከሚቀርበው የፈቃደኝነት መባ+ በተጨማሪ ብር፣ ወርቅ፣ የተለያዩ ዕቃዎችና የቤት እንስሳት በመስጠት ይርዱት።’”
5 ከዚያም የይሁዳና የቢንያም የአባቶች ቤት መሪዎች፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ፣ እውነተኛው አምላክ መንፈሳቸውን ያነሳሳው ሰዎች ሁሉ ወጥተው በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ቤት መልሰው ለመገንባት ተዘጋጁ። 6 በዙሪያቸው ያሉትም ሁሉ በፈቃደኝነት ከተሰጠው መባ በተጨማሪ የብርና የወርቅ ዕቃዎችን፣ የተለያዩ ዕቃዎችን፣ የቤት እንስሳትን እንዲሁም ውድ የሆኑ ነገሮችን በመስጠት ረዷቸው።*
7 በተጨማሪም ንጉሥ ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአምላኩ ቤት ያስቀመጣቸውን የይሖዋን ቤት ዕቃዎች አወጣ።+ 8 የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኃላፊ በሚትረዳት ተቆጣጣሪነት ዕቃዎቹ እንዲወጡ አደረገ፤ ሚትረዳትም ለይሁዳው አለቃ ለሸሽባጻር*+ ቆጥሮ አስረከበው።
9 የተቆጠሩት ዕቃዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ በቅርጫት ቅርጽ የተሠሩ 30 የወርቅ ዕቃዎች፣ በቅርጫት ቅርጽ የተሠሩ 1,000 የብር ዕቃዎችና 29 ምትክ ዕቃዎች 10 እንዲሁም 30 ትናንሽ ጎድጓዳ የወርቅ ሳህኖች፣ 410 አነስተኛ ጎድጓዳ የብር ሳህኖችና 1,000 ሌሎች ዕቃዎች። 11 የወርቅና የብር ዕቃዎቹ በአጠቃላይ 5,400 ነበሩ። ሸሽባጻርም ግዞተኞቹ+ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ይዞ ወጣ።