ሁለተኛ ሳሙኤል
21 በዳዊት ዘመን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ረሃብ ሆነ፤+ ስለዚህ ዳዊት ይሖዋን ምክር ጠየቀ፤ ይሖዋም “ሳኦል ገባኦናውያንን ስለገደለ እሱም ሆነ ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ።+ 2 በመሆኑም ንጉሡ ገባኦናውያንን+ ጠርቶ አነጋገራቸው። (እርግጥ ገባኦናውያን ከአሞራውያን+ የተረፉ ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እስራኤላውያንም እንደማያጠፏቸው ምለውላቸው ነበር፤+ ይሁንና ሳኦል ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ባለው ቅንዓት ተነሳስቶ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር።) 3 ዳዊትም ገባኦናውያንን “የይሖዋን ርስት እንድትባርኩ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረይስ የምችለው እንዴት ነው?” አላቸው። 4 ገባኦናውያንም “ከሳኦልና ከእሱ ቤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በብርና በወርቅ የሚፈታ አይደለም፤+ ደግሞም በእስራኤል ውስጥ ማንንም ሰው የመግደል መብት የለንም” አሉት። በዚህ ጊዜ ዳዊት “ያላችሁትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” አላቸው። 5 እነሱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ለጥፋት ከዳረገንና በየትኛውም የእስራኤል ግዛት ውስጥ እንዳንኖር እኛን ለመደምሰስ ሴራ ከጠነሰሰብን ሰው+ 6 ወንዶች ልጆች መካከል ሰባቱ ይሰጡን። እኛም በይሖዋ የተመረጠው የሳኦል+ አገር በሆነችው በጊብዓ+ በድናቸውን በይሖዋ ፊት እንሰቅላለን።”*+ ከዚያም ንጉሡ “እሺ፣ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።
7 ሆኖም ንጉሡ እሱና የሳኦል ልጅ ዮናታን በይሖዋ ፊት በተማማሉት መሐላ የተነሳ የሳኦል ልጅ ለሆነው ለዮናታን+ ልጅ ለሜፊቦስቴ+ ራራለት። 8 በመሆኑም ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ+ ለሳኦል የወለደችለትን ሁለት ወንዶች ልጆች ማለትም አርሞኒንና ሜፊቦስቴን እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜልኮል*+ የመሆላታዊው የቤርዜሊ ልጅ ለሆነው ለአድሪዔል+ የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ወሰደ። 9 ከዚያም ለገባኦናውያኑ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም በድናቸውን በተራራው ላይ በይሖዋ ፊት ሰቀሉ።+ ሰባቱም አንድ ላይ ሞቱ፤ የተገደሉትም አዝመራ በሚሰበሰብባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት ይኸውም የገብስ አዝመራ መሰብሰብ በሚጀምርበት ጊዜ ነበር። 10 ከዚያም የአያ ልጅ ሪጽፋ+ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንስቶ በበድኖቹ ላይ ከሰማይ ዝናብ እስከሚወርድበት ጊዜ ድረስ ማቅ ወስዳ በዓለቱ ላይ አነጠፈች፤ ቀን የሰማይ አሞሮች እንዲያርፉባቸው፣ ሌሊት ደግሞ የዱር አራዊት እንዲጠጓቸው አልፈቀደችም።
11 በኋላም የሳኦል ቁባት የሆነችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችው ነገር ለዳዊት ተነገረው። 12 ስለዚህ ዳዊት ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከኢያቢስጊልያድ+ መሪዎች* ላይ ወሰደ፤ እነዚህ ሰዎች አፅሙን ፍልስጤማውያን ሳኦልን በጊልቦአ+ በገደሉበት ቀን እሱንና ዮናታንን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ ሰርቀው ወስደው ነበር። 13 እሱም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከዚያ አመጣ፤ በተጨማሪም የተገደሉትን* ሰዎች አፅም ሰበሰቡ።+ 14 ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም በቢንያም ምድር በጸላ+ በሚገኘው በሳኦል አባት በቂስ+ የመቃብር ስፍራ ቀበሩት። ንጉሡ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ከፈጸሙም በኋላ አምላክ ስለ ምድሪቱ ያቀረቡትን ልመና ሰማ።+
15 በፍልስጤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል እንደገና ጦርነት ተነሳ።+ በመሆኑም ዳዊትና አገልጋዮቹ ወርደው ፍልስጤማውያንን ወጉ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ዛለ። 16 ከረፋይም+ ዘር የሆነው እንዲሁም 300 ሰቅል*+ የሚመዝን የመዳብ ጦርና አዲስ ሰይፍ የታጠቀው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ለመግደል አሰበ። 17 የጽሩያ ልጅ አቢሳም+ ወዲያውኑ ደረሰለት፤+ ፍልስጤማዊውንም መትቶ ገደለው። በዚያን ጊዜ የዳዊት ሰዎች “ከአሁን በኋላ ከእኛ ጋር ወደ ውጊያ መውጣት የለብህም!+ የእስራኤልን መብራት አታጥፋ!”+ በማለት ማሉለት።
18 ከዚህም በኋላ እንደገና ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተከፈተ።+ በዚህ ጊዜ ሁሻዊው ሲበካይ+ የረፋይም+ ዘር የሆነውን ሳፍን ገደለው።
19 ዳግመኛም ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤+ የቤተልሔማዊው የያአሬዖርጊም ልጅ ኤልሃናን የሸማኔ መጠቅለያ የሚመስል ዘንግ ያለው ጦር ይዞ የነበረውን ጌታዊውን ጎልያድን ገደለው።+
20 እንደገናም በጌት ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ በዚያም በእጆቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች በእግሮቹም ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች፣ በድምሩ 24 ጣቶች ያሉት በጣም ግዙፍ የሆነ ሰው ነበር፤ እሱም የረፋይም ዘር ነበር።+ 21 ይህ ሰው እስራኤልን ይገዳደር+ ስለነበር የዳዊት ወንድም የሺምአይ+ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22 እነዚህ አራቱ በጌት የሚኖሩ የረፋይም ዘሮች ነበሩ፤ እነሱም በዳዊት እጅና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ።+