የሉቃስ ወንጌል
7 ኢየሱስ ለሕዝቡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2 በዚያም አንድ የጦር መኮንን* ነበር፤ በጣም የሚወደው ባሪያውም በጠና ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር።+ 3 እሱም ስለ ኢየሱስ ሲሰማ መጥቶ ባሪያውን እንዲፈውስለት ይለምኑለት ዘንድ የተወሰኑ አይሁዳውያን ሽማግሌዎችን ላከ። 4 እነሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ በማለት ተማጸኑት፦ “ይህን ሰው ልትረዳው ይገባል፤ 5 ምክንያቱም ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኩራባችንንም ያሠራልን እሱ ነው።” 6 ስለዚህ ኢየሱስ አብሯቸው ሄደ። ሆኖም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ መኮንኑ ወዳጆቹን እንዲህ ሲል ወደ ኢየሱስ ላከ፦ “ጌታዬ፣ በቤቴ ጣሪያ ሥር ልትገባ የሚገባኝ ሰው ስላልሆንኩ አትድከም።+ 7 ከዚህም የተነሳ አንተ ፊት መቅረብ የሚገባኝ ሰው እንደሆንኩ አልተሰማኝም። ስለዚህ አንተ አንድ ቃል ተናገርና አገልጋዬ ይፈወስ። 8 እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 9 ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ በሰውየው በጣም ተደንቆ ይከተለው ወደነበረው ሕዝብ ዞር በማለት “እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንኳ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት አላገኘሁም” አለ።+ 10 የተላኩትም ሰዎች ወደ ቤት ሲመለሱ ባሪያው ድኖ አገኙት።+
11 ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ናይን ወደምትባል ከተማ ተጓዘ፤ ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎችም አብረውት ይጓዙ ነበር። 12 ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረብ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው በመውጣት ላይ ነበሩ፤ ሟቹ ለእናቱ አንድ ልጇ ነበር።+ በተጨማሪም እናቱ መበለት ነበረች። ብዙ የከተማዋ ሕዝብም ከእሷ ጋር ነበር። 13 ጌታ ባያት ጊዜ በጣም አዘነላትና+ “በቃ፣ አታልቅሺ”+ አላት። 14 ከዚያም ቀረብ ብሎ ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙት ሰዎችም ባሉበት ቆሙ፤ ኢየሱስም “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” አለ።+ 15 የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት።+ 16 በዚህ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተውጠው “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነስቷል፤”+ እንዲሁም “አምላክ ሕዝቡን አሰበ” እያሉ አምላክን ያወድሱ ጀመር።+ 17 ኢየሱስ ያከናወነውም ነገር በይሁዳ ሁሉና በአካባቢው ባለ አገር ሁሉ ተሰማ።
18 በዚህ ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሁሉ አወሩለት።+ 19 ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ጠርቶ “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ+ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው እንዲጠይቁት ወደ ጌታ ላካቸው። 20 ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብለን እንድንጠይቅህ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። 21 ኢየሱስ በዚያኑ ሰዓት ብዙዎችን ከሕመምና ከከባድ በሽታ ፈወሳቸው፤+ እንዲሁም ያደሩባቸውን ክፉ መናፍስት አወጣ፤ የብዙ ዓይነ ስውራንንም ዓይን አበራ። 22 እሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የሰማችሁትንና ያያችሁትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፦ ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤+ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤+ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።+ 23 በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”+
24 የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?+ 25 ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ* የለበሰ ሰው ለማየት?+ የተንቆጠቆጠ ልብስ የሚለብሱና በቅንጦት የሚኖሩማ የሚገኙት በቤተ መንግሥት ነው። 26 ታዲያ ምን ለማየት ሄዳችሁ? ነቢይ? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።+ 27 ‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው።+ 28 እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ ሆኖም በአምላክ መንግሥት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።”+ 29 (ሕዝቡ ሁሉ እንዲሁም ቀራጮች ይህን በሰሙ ጊዜ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው ስለነበር አምላክ ጻድቅ መሆኑን አምነው ተቀበሉ።+ 30 ሆኖም ፈሪሳውያንና የሕጉ አዋቂዎች በዮሐንስ ባለመጠመቃቸው የአምላክን ምክር* አቃለሉ።)+
31 ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች ከማን ጋር ላነጻጽራቸው? ማንንስ ይመስላሉ?+ 32 በገበያ ስፍራ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን አላለቀሳችሁም’ ከሚባባሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላሉ። 33 በተመሳሳይም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና ወይን ጠጅ ሳይጠጣ መጣ፤+ እናንተ ግን ‘ጋኔን አለበት’ አላችሁ። 34 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ!’ አላችሁ።+ 35 የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ* መሆኗ በልጆቿ* ሁሉ ተረጋግጧል።”+
36 ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ደጋግሞ ለመነው። ስለሆነም ኢየሱስ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37 እነሆም፣ በከተማው ውስጥ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ አንዲት ሴት ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት እየበላ መሆኑን በሰማች ጊዜ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች።+ 38 እሷም ከበስተ ኋላ እግሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር፤ ከዚያም በፀጉሯ አበሰችው። በተጨማሪም እግሩን እየሳመች ዘይቱን ቀባችው። 39 የጋበዘው ፈሪሳዊም ይህን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ ቢሆን ኖሮ የምትነካው ማን መሆኗንና ምን ዓይነት ሴት እንደሆነች ይኸውም ኃጢአተኛ መሆኗን ባወቀ ነበር” ብሎ በልቡ አሰበ።+ 40 ኢየሱስ ግን መልሶ “ስምዖን፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እሱም “መምህር፣ እሺ ንገረኝ” አለው።
41 “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ 500 ሌላው ደግሞ 50 ዲናር* ተበድረው ነበር። 42 ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው ዕዳቸውን ሙሉ በሙሉ ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ ሰዎች አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?” 43 ስምዖንም መልሶ “ብዙ ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” አለው። እሱም “በትክክል ፈርደሃል” አለው። 44 ከዚያም ወደ ሴቲቱ ዞር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያታለህ? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ይሁንና አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም። ይህች ሴት ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ አበሰች። 45 አንተ አልሳምከኝም፤ ይህች ሴት ግን ከገባሁበት ሰዓት አንስቶ እግሬን መሳሟን አላቋረጠችም። 46 አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ ይህች ሴት ግን እግሬን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ቀባች። 47 ስለዚህ እልሃለሁ፣ ኃጢአቷ ብዙ* ቢሆንም ይቅር ተብሎላታል፤+ ምክንያቱም ታላቅ ፍቅር አሳይታለች። በትንሹ ይቅር የተባለ ግን የሚያሳየውም ፍቅር አነስተኛ ነው።” 48 ከዚያም ሴትየዋን “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” አላት።+ 49 በማዕድ አብረውት የተቀመጡት በልባቸው “ኃጢአትን እንኳ ይቅር የሚል ይህ ሰው ማን ነው?” ይሉ ጀመር።+ 50 ኢየሱስ ግን ሴትየዋን “እምነትሽ አድኖሻል፤+ በሰላም ሂጂ” አላት።