ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
10 እኔም ደመና የተጎናጸፈ* ሌላ ብርቱ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበር፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ፣+ ቅልጥሞቹም* እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፤ 2 በእጁም የተከፈተች ትንሽ ጥቅልል ይዞ ነበር። እሱም ቀኝ እግሩን በባሕር ላይ፣ ግራ እግሩን ደግሞ በምድር ላይ አሳረፈ፤ 3 እንደሚያገሣ አንበሳም በታላቅ ድምፅ ጮኸ።+ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፆች+ ተናገሩ።
4 ሰባቱ ነጎድጓዶች በተናገሩም ጊዜ ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፤ ሆኖም ከሰማይ+ “ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሯቸውን ነገሮች በማኅተም አሽጋቸው* እንጂ አትጻፋቸው” የሚል ድምፅ ሰማሁ። 5 በባሕሩና በምድሩ ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሳ፤ 6 ሰማይንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች እንዲሁም ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በፈጠረውና+ ለዘላለም በሚኖረው+ በመማል እንዲህ አለ፦ “ከእንግዲህ ወዲህ መዘግየት አይኖርም። 7 ሆኖም ሰባተኛው መልአክ+ መለከቱን ሊነፋ+ በተዘጋጀባቸው ቀኖች አምላክ የገዛ ራሱ ባሪያዎች ለሆኑት ለነቢያት+ እንደ ምሥራች ያበሰረው ቅዱስ ሚስጥር+ በእርግጥ ይፈጸማል።”
8 ከሰማይ የመጣውም ድምፅ+ እንደገና ሲያናግረኝ ሰማሁ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ሂድ፣ በባሕሩና በምድሩ ላይ በቆመው መልአክ እጅ ያለችውን የተከፈተች ጥቅልል ውሰድ።”+ 9 እኔም ወደ መልአኩ ሄጄ ትንሿን ጥቅልል እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። እሱም “ውሰድና ብላት፤+ ሆድህን መራራ ታደርገዋለች፤ አፍህ ላይ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች” አለኝ። 10 ትንሿን ጥቅልል ከመልአኩ እጅ ወስጄ በላኋት፤+ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠች፤+ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ። 11 እነሱም “ሕዝቦችን፣ ብሔራትን፣ ቋንቋዎችንና ብዙ ነገሥታትን በተመለከተ እንደገና ትንቢት መናገር አለብህ” አሉኝ።