ኢሳይያስ
6 ንጉሥ ዖዝያ በሞተበት ዓመት+ ይሖዋን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤+ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። 2 ሱራፌልም ከእሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፎች ነበሯቸው። እያንዳንዱ* በሁለቱ ክንፍ ፊቱን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ እግሩን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ ደግሞ ይበር ነበር።
3 አንዳቸውም ሌላውን እንዲህ ይሉ ነበር፦
“የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው።+
መላዋ ምድር በክብሩ ተሞልታለች።”
4 ከድምፁ ጩኸት* የተነሳ የበሩ መቃኖች ተናወጡ፤ ቤቱም በጭስ ተሞላ።+
5 በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ “ወዮልኝ!
ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና
የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ+ መካከል ስለሆነ
በቃ መሞቴ ነው፤*
ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!”
6 በዚህ ጊዜ ከሱራፌል አንዱ ወደ እኔ እየበረረ መጣ፤ እሱም ከመሠዊያው ላይ በጉጠት ያነሳውን ፍም+ በእጁ ይዞ ነበር።+ 7 አፌንም ነክቶ እንዲህ አለኝ፦
“እነሆ፣ ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል።
በደልህ ተወግዶልሃል፤
ኃጢአትህም ተሰርዮልሃል።”
8 ከዚያም የይሖዋ ድምፅ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?”+ ሲል ሰማሁ። እኔም “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” አልኩ።+
9 እሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፦ “ሄደህ ይህን ሕዝብ እንዲህ በለው፦
10 በዓይናቸው እንዳያዩ፣
በጆሯቸውም እንዳይሰሙ፣
ልባቸውም እንዳያስተውል፣
ተመልሰውም እንዳይፈወሱ
የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤+
ጆሯቸውንም ድፈን፤+
ዓይናቸውንም ሸፍን።”+
11 በዚህ ጊዜ “ይሖዋ ሆይ፣ እስከ መቼ ነው?” አልኩ። እሱም እንዲህ አለኝ፦
“ከተሞች እስኪፈራርሱና የሚኖርባቸው እስኪያጡ፣
ቤቶችም ሰው አልባ እስኪሆኑ፣
ምድሪቱም እስክትጠፋና ባድማ እስክትሆን ድረስ ነው፤+
12 ይሖዋም ሰዎችን ወደ ሩቅ ቦታ እስከሚሰድ፣+
የምድሪቱም በረሃነት በእጅጉ እስኪስፋፋ ድረስ ነው።
13 “ይሁንና በእሷ ውስጥ አንድ አሥረኛ ይቀራል፤ እሱም በድጋሚ ይቃጠላል፤ ከተቆረጡ በኋላ ጉቷቸው እንደሚቀር እንደ ትልቅ ዛፍና እንደ ባሉጥ ዛፍ ይሆናል፤ በምድሪቱ ላይ የቀረው ጉቶ የተቀደሰ ዘር ይሆናል።”