ኤርምያስ
19 ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ሄደህ፣ ከሸክላ ሠሪ ገንቦ ግዛ።+ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከካህናቱ ሽማግሌዎች መካከል የተወሰኑትን ይዘህ 2 በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሂኖም ልጅ ሸለቆ+ ውጣ። የምነግርህንም ቃል በዚያ አውጅ። 3 እንዲህ ትላለህ፦ ‘እናንተ የይሁዳ ነገሥታትና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የይሖዋን ቃል ስሙ። የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“‘“በዚህ ስፍራ ላይ ጥፋት ላመጣ ነው፤ ስለሚመጣው ጥፋት የሚሰማ ሰው ሁሉ ጆሮውን ይነዝረዋል። 4 ምክንያቱም እኔን ትተውኛል፤+ ይህን ስፍራም የማይታወቅ ቦታ አድርገውታል።+ በዚህ ስፍራ እነሱም ሆኑ አባቶቻቸው እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት ለማያውቋቸው ሌሎች አማልክት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ይህን ስፍራም በንጹሐን ደም ሞልተውታል።+ 5 እኔ ያላዘዝኩትን ወይም ያልተናገርኩትን፣ በልቤም እንኳ ፈጽሞ ያላሰብኩትን* ነገር ለማድረግ ይኸውም ወንዶች ልጆቻቸውን ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርገው ለባአል በእሳት ለማቃጠል ከፍ ያሉትን የባአል የማምለኪያ ቦታዎች ሠሩ።”’+
6 “‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ፣ እነሆ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ እንጂ ቶፌት ወይም የሂኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል።+ 7 በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አጨናግፋለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት በሰይፍ እንዲወድቁ፣ ሕይወታቸውንም* በሚሹ ሰዎች እጅ እንዲጠፉ አደርጋለሁ። አስከሬናቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል እንዲሆን እሰጣለሁ።+ 8 ይህችንም ከተማ አስፈሪ ቦታና ማፏጫ አደርጋታለሁ። በዚያ የሚያልፍ ሁሉ በደረሰባት መቅሰፍት የተነሳ በፍርሃት አፍጥጦ ይመለከታል፤ ደግሞም ያፏጫል።+ 9 ጠላቶቻቸውና ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚሹ* ሰዎች ሲከቧቸውና መፈናፈኛ አሳጥተው ሲያስጨንቋቸው የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤ እያንዳንዳቸው የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።”’+
10 “ከዚያም ገንቦውን ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ስበረው፤ 11 እንዲህም በላቸው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የሸክላ ሠሪን ዕቃ ሊጠገን በማይችል መንገድ እንደሚሰብረው፣ እኔም ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እንዲሁ እሰባብራለሁ፤ እነሱም የመቃብር ቦታ እስኪታጣ ድረስ የሞቱትን በቶፌት ይቀብራሉ።”’+
12 “‘ይህችን ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋት ዘንድ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ ይህን እፈጽማለሁ’ ይላል ይሖዋ። 13 ‘የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፣ አዎ በጣሪያዎቻቸው ላይ ለሰማያት ሠራዊት መሥዋዕቶች ያቀረቡባቸውና+ ለሌሎች አማልክት የመጠጥ መባዎች ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ+ እንደዚህ ስፍራ፣ እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ።’”+
14 ኤርምያስ፣ ይሖዋ ትንቢት እንዲናገር ልኮት ከነበረበት ከቶፌት ሲመለስ በይሖዋ ቤት ግቢ ቆሞ ለመላው ሕዝብ እንዲህ አለ፦ 15 “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ሁሉ ላይ አመጣዋለሁ ብዬ የተናገርኩትን ጥፋት ሁሉ አወርድባቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ቃሌን ለመታዘዝ በግትርነት አሻፈረን ብለዋል።’”*+