ዘኁልቁ
1 ይሖዋም እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት ሁለተኛ ወር፣ የመጀመሪያ ቀን+ ላይ በሲና ምድረ በዳ+ በመገናኛ ድንኳኑ+ ውስጥ ሙሴን አነጋገረው። እንዲህም አለው፦ 2 “የእስራኤልን ማኅበረሰብ* በሙሉ በየቤተሰባቸው፣ በየአባቶቻቸው ቤትና በስም በተዘረዘሩት ወንዶች ሁሉ ቁጥር መሠረት በግለሰብ ደረጃ ቁጠር።+ 3 አንተና አሮን ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን+ በእስራኤል ውስጥ ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉትን ሁሉ በየምድባቸው* መዝግቡ።
4 “ከየነገዱ አንድ ሰው ውሰድ፤ እያንዳንዳቸውም ለየአባቶቻቸው ቤት መሪ ይሆናሉ።+ 5 ከአንተ ጋር የሚቆሙትም ወንዶች ስም የሚከተለው ነው፦ ከሮቤል ነገድ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር፣+ 6 ከስምዖን ነገድ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል፣+ 7 ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፣+ 8 ከይሳኮር ነገድ የጹአር ልጅ ናትናኤል፣+ 9 ከዛብሎን ነገድ የሄሎን ልጅ ኤልያብ፣+ 10 ከዮሴፍ ወንዶች ልጆች ይኸውም ከኤፍሬም+ ነገድ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ፣ ከምናሴ ነገድ ደግሞ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል፣ 11 ከቢንያም ነገድ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን፣+ 12 ከዳን ነገድ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር፣+ 13 ከአሴር ነገድ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል፣+ 14 ከጋድ ነገድ የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ 15 እንዲሁም ከንፍታሌም ነገድ የኤናን ልጅ አሂራ።+ 16 እነዚህ ከማኅበረሰቡ የተመረጡ ናቸው። እነሱም የአባቶቻቸው ነገዶች መሪዎች+ ማለትም የእስራኤል የሺህ አለቆች+ ናቸው።”
17 በመሆኑም ሙሴና አሮን በስም የተጠቀሱትን እነዚህን ወንዶች ወሰዱ። 18 እነሱም ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ+ የሆኑት በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በግለሰብ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለማድረግ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ላይ መላውን ማኅበረሰብ ሰበሰቡ፤ 19 ይህን ያደረጉት ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ነው። እሱም በሲና ምድረ በዳ መዘገባቸው።+
20 የእስራኤል የበኩር ልጅ+ ዝርያዎች የሆኑት የሮቤል ልጆች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተቆጠሩ፤ 21 ከሮቤል ነገድ የተመዘገቡት 46,500 ነበሩ።
22 የስምዖን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተቆጠሩ፤ 23 ከስምዖን ነገድ የተመዘገቡት 59,300 ነበሩ።
24 የጋድ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 25 ከጋድ ነገድ የተመዘገቡት 45,650 ነበሩ።
26 የይሁዳ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 27 ከይሁዳ ነገድ የተመዘገቡት 74,600 ነበሩ።
28 የይሳኮር+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 29 ከይሳኮር ነገድ የተመዘገቡት 54,400 ነበሩ።
30 የዛብሎን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 31 ከዛብሎን ነገድ የተመዘገቡት 57,400 ነበሩ።
32 በኤፍሬም+ በኩል ያሉት የዮሴፍ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 33 ከኤፍሬም ነገድ የተመዘገቡት 40,500 ነበሩ።
34 የምናሴ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 35 ከምናሴ ነገድ የተመዘገቡት 32,200 ነበሩ።
36 የቢንያም+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 37 ከቢንያም ነገድ የተመዘገቡት 35,400 ነበሩ።
38 የዳን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 39 ከዳን ነገድ የተመዘገቡት 62,700 ነበሩ።
40 የአሴር+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 41 ከአሴር ነገድ የተመዘገቡት 41,500 ነበሩ።
42 የንፍታሌም+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 43 ከንፍታሌም ነገድ የተመዘገቡት 53,400 ነበሩ።
44 ሙሴ ከአሮንና እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ቤት ከሚወክሉት ከ12 የእስራኤል አለቆች ጋር በመሆን የመዘገባቸው እነዚህ ናቸው። 45 በእስራኤል ውስጥ ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት እስራኤላውያን ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 46 የተመዘገቡትም ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 603,550 ነበር።+
47 ይሁን እንጂ ሌዋውያኑ+ ሌሎቹ እንደተመዘገቡት በየአባቶቻቸው ነገድ መሠረት አልተመዘገቡም።+ 48 ስለዚህ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 49 “የሌዊን ነገድ ብቻ አትመዝግብ፤ ቁጥራቸውም በሌሎቹ እስራኤላውያን ቁጥር ውስጥ እንዲካተት አታድርግ።+ 50 ሌዋውያኑን በምሥክሩ+ የማደሪያ ድንኳን፣ በዕቃዎቹ ሁሉና ከዚያ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ሹማቸው።+ እነሱም የማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን በሙሉ ይሸከማሉ፤+ በዚያም ያገለግላሉ፤+ በማደሪያ ድንኳኑም ዙሪያ ይሰፍራሉ።+ 51 የማደሪያ ድንኳኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ ሌዋውያኑ ይንቀሉት፤+ የማደሪያ ድንኳኑ በሚተከልበት ጊዜም ሌዋውያኑ ይትከሉት። ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ወደዚያ ቢቀርብ ይገደል።+
52 “እያንዳንዱ እስራኤላዊ በየተመደበበት ሰፈር ድንኳኑን ይትከል፤ እያንዳንዱም ሰው ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ቡድኑ*+ ውስጥ በየምድቡ* ይስፈር። 53 በእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ሌዋውያኑ በምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን ዙሪያ ይስፈሩ፤+ ሌዋውያኑም የምሥክሩን የማደሪያ ድንኳን የመንከባከብ* ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።”+
54 እስራኤላውያንም ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ልክ እንደዚያው አደረጉ።