20 የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣+ የሚያሰክር መጠጥም ሥርዓት አልበኛ ያደርጋል፤+
በዚህ ምክንያት ከትክክለኛው መንገድ የሚወጣ ሁሉ ጥበበኛ አይደለም።+
2 ንጉሥ የሚፈጥረው ሽብር እንደ አንበሳ ግሳት ነው፤+
የእሱን ቁጣ የሚያነሳሳ ሁሉ ሕይወቱን ለአደጋ ያጋልጣል።+
3 ሰው ከጠብ መራቁ ያስከብረዋል፤+
ሞኝ የሆነ ሁሉ ግን ጥል ውስጥ ይዘፈቃል።+
4 ሰነፍ ሰው በክረምት አያርስም፤
በመሆኑም በመከር ወራት ባዶውን ሲቀር ይለምናል።+
5 በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤
አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።
6 ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ታማኝ ፍቅር ያወራሉ፤
ይሁንና ታማኝ የሆነን ሰው ማን ሊያገኘው ይችላል?
7 ጻድቅ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ይመላለሳል።+
ከእሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቹ ደስተኞች ናቸው።+
8 ንጉሥ ለመፍረድ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ፣+
ክፋትን ሁሉ በዓይኖቹ ያበጥራል።+
9 “ልቤን አንጽቻለሁ፤+
ከኃጢአቴም ነጽቻለሁ” ሊል የሚችል ማን ነው?+
10 አባይ ሚዛንና የሐሰት መለኪያ፣
ሁለቱም በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ናቸው።+
11 ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ
በአድራጎቱ ይታወቃል።+
12 የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፣
ሁለቱንም የሠራው ይሖዋ ነው።+
13 እንቅልፍ አትውደድ፤ አለዚያ ድሃ ትሆናለህ።+
ዓይንህን ግለጥ፤ የተትረፈረፈ ምግብም ታገኛለህ።+
14 ዕቃ የሚገዛ ሰው “የማይረባ ነው፣ የማይረባ ነው!” ይላል፤
ከሄደ በኋላ ግን በራሱ ይኩራራል።+
15 ወርቅ አለ፤ ዛጎልም ተትረፍርፏል፤
እውቀትን የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ውድ ናቸው።+
16 አንድ ሰው ለማያውቀው ሰው ዋስ ከሆነ ልብሱን ውሰድበት፤+
ይህን ያደረገው ለባዕድ ሴት ብሎ ከሆነ መያዣውን ውሰድ።+
17 ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ያስደስተዋል፤
በኋላ ግን አፉን ኮረት ይሞላዋል።+
18 መመካከር ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል፤+
ለውጊያም ስትወጣ ጥበብ ያለበት አመራር ተቀበል።+
19 ስም የሚያጠፋ ሰው እየዞረ የሌሎችን ሚስጥር ይገልጣል፤+
ማማት ከሚወድ ሰው ጋር አትወዳጅ።
20 አባቱንና እናቱን የሚረግም ሁሉ
ጨለማ ሲሆን መብራቱ ይጠፋበታል።+
21 በመጀመሪያ በስግብግብነት የተገኘ ውርስ፣
የኋላ ኋላ በረከት አይሆንም።+
22 “ቆይ፣ ብድሬን ባልመልስ!” አትበል።+
ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤+ እሱም ያድንሃል።+
23 አባይ ሚዛን በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው፤
ለማጭበርበር የሚያገለግሉ መለኪያዎችንም መጠቀም ጥሩ አይደለም።
24 ይሖዋ የሰውን አካሄድ ይመራል፤+
ሰው የገዛ መንገዱን እንዴት ማስተዋል ይችላል?
25 ሰው ቸኩሎ “የተቀደሰ ነው!”+ ቢልና
ከተሳለ በኋላ ስእለቱን መልሶ ማጤን ቢጀምር ወጥመድ ይሆንበታል።+
26 ጥበበኛ ንጉሥ ክፉ ሰዎችን ያበጥራል፤+
የመውቂያ መንኮራኩርም በላያቸው ያስኬዳል።+
27 የሰው እስትንፋስ የይሖዋ መብራት ነው፤
ውስጣዊ ማንነቱን በሚገባ ይመረምራል።
28 ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቃሉ፤+
በታማኝ ፍቅርም ዙፋኑን ያጸናል።+
29 የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው፤+
የአረጋውያንም ግርማ ሽበታቸው ነው።+
30 ሰንበርና ቁስል ክፋትን ያስወግዳል፤+
ግርፋትም የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ያጠራል።