ዳንኤል
8 ንጉሥ ቤልሻዛር+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ቀደም ሲል ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ ለእኔ፣ ለዳንኤል ሌላ ራእይ ተገለጠልኝ።+ 2 እኔም ራእዩን ተመለከትኩ፤ በራእዩም ላይ ራሴን፣ በኤላም+ አውራጃ በሚገኘው በሹሻን*+ ግንብ* አየሁት፤ ደግሞም ራእዩን ተመለከትኩ፤ እኔም በኡላይ የውኃ መውረጃ አጠገብ ነበርኩ። 3 ዓይኔን አንስቼ ስመለከት፣ እነሆ በውኃ መውረጃው አጠገብ ሁለት ቀንዶች ያሉት+ አንድ አውራ በግ+ ቆሞ ነበር። ሁለቱ ቀንዶች ረጃጅም ነበሩ፤ ይሁንና አንደኛው ከሌላው ይረዝማል፤ ይበልጥ ረጅም የሆነው ቀንድ የበቀለው በኋላ ነው።+ 4 አውራ በጉ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲወጋ ተመለከትኩ፤ አንድም አውሬ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም መታደግ የሚችል ማንም አልነበረም።+ የፈለገውን ያደርግ ነበር፤ ራሱንም ከፍ ከፍ አደረገ።
5 እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ አንድ አውራ ፍየል+ ከምዕራብ* ተነስቶ መሬት ሳይነካ መላዋን ምድር እያቋረጠ መጣ። አውራውም ፍየል በዓይኖቹ መካከል ጎልቶ የሚታይ ቀንድ ነበረው።+ 6 እሱም በውኃ መውረጃው አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ አመራ፤ በታላቅ ቁጣም ተንደርድሮ መጣበት።
7 ወደ አውራው በግ ሲቀርብ አየሁት፤ በበጉም እጅግ ተመርሮ ነበር። በጉን መትቶ ሁለቱንም ቀንዶቹን ሰባበራቸው፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው የሚችልበት አቅም አልነበረውም። በጉን መሬት ላይ ጥሎ ረጋገጠው፤ አውራ በጉንም ከእጁ የሚያስጥለው አልነበረም።
8 ከዚያም አውራው ፍየል እጅግ ታበየ፤ ሆኖም ኃያል በሆነ ጊዜ ትልቁ ቀንድ ተሰበረ፤ በምትኩም ጎልተው የሚታዩ አራት ቀንዶች ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በቀሉ።+
9 ከእነሱ መካከል ከአንደኛው፣ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና* ውብ ወደሆነችው ምድር*+ በጣም እያደገ ሄደ። 10 ወደ ሰማይ ሠራዊት እስከሚደርስ ድረስ እያደገ ሄደ፤ ከሠራዊቱና ከከዋክብቱ መካከልም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም። 11 በሠራዊቱ አለቃ ላይ እንኳ ሳይቀር ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የዘወትሩም መሥዋዕት ከአለቃው ተወሰደ፤ ጽኑ የሆነው የመቅደሱ ስፍራም ፈረሰ።+ 12 ከተፈጸመው በደል የተነሳ ሠራዊቱ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለቀንዱ አልፎ ተሰጠ፤ እውነትን ወደ ምድር ጣለ፤ እንደ ፈቃዱ አደረገ፤ ደግሞም ተሳካለት።
13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እየተናገረ ለነበረው ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕትና ጥፋት ስለሚያመጣው በደል+ እንዲሁም ቅዱሱ ስፍራና ሠራዊቱ እንዲረገጡ ስለመተዋቸው በሚገልጸው ራእይ ላይ የታየው ነገር የሚቆየው እስከ መቼ ነው?” 14 እሱም “2,300 ምሽቶችና ንጋቶች እስኪያልፉ ድረስ ነው፤ ቅዱሱም ስፍራ ወደ ትክክለኛው ሁኔታ በእርግጥ ይመለሳል” አለኝ።
15 እኔ ዳንኤል ራእዩን እየተመለከትኩና ለመረዳት እየጣርኩ ሳለ፣ ሰው የሚመስል ድንገት ከፊት ለፊቴ ቆሞ አየሁ። 16 ከዚያም ከኡላይ+ መካከል የሰው ድምፅ ሰማሁ፤ እሱም ጮክ ብሎ “ገብርኤል፣+ ለዚህ ሰው ያየውን ነገር አስረዳው” አለ።+ 17 በመሆኑም እኔ ወደቆምኩበት ስፍራ ቀረበ፤ ሆኖም ወደ እኔ ሲመጣ፣ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ በግንባሬ ተደፋሁ። እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ ራእዩ የሚፈጸመው በዘመኑ ፍጻሜ መሆኑን ተረዳ” አለኝ።+ 18 እኔ ግን እያናገረኝ ሳለ መሬት ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከባድ እንቅልፍም ወሰደኝ። ስለዚህ ዳሰሰኝና ቆሜበት በነበረው ቦታ እንድቆም አደረገኝ።+ 19 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ፣ በቁጣው ዘመን ማብቂያ ላይ የሚሆነውን ነገር አሳውቅሃለሁ፤ ምክንያቱም ራእዩ በተወሰነው የፍጻሜ ዘመን ይፈጸማል።+
20 “ያየኸው ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ የሜዶንንና የፋርስን ነገሥታት ያመለክታል።+ 21 ፀጉራሙ አውራ ፍየል የግሪክን ንጉሥ ያመለክታል፤+ በዓይኖቹ መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያውን ንጉሥ ያመለክታል።+ 22 ቀንዱ ተሰብሮ በምትኩ አራት ቀንዶች እንደወጡ ሁሉ+ ከእሱ ብሔር የሚነሱ አራት መንግሥታት ይኖራሉ፤ ሆኖም የእሱን ያህል ኃይል አይኖራቸውም።
23 “በዘመነ መንግሥታቸውም መገባደጃ ላይ በደለኞቹ እስከ መጨረሻ* በደል ሲፈጽሙ፣ ግራ የሚያጋቡ አባባሎችን የሚረዳ* አስፈሪ መልክ ያለው ንጉሥ ይነሳል። 24 ኃይሉ እጅግ ታላቅ ይሆናል፤ በገዛ ኃይሉ ግን አይደለም። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት* ያደርሳል፤ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለታል። በኃያላን ሰዎችና በቅዱሳኑ ሕዝብ ላይ ጥፋት ያደርሳል።+ 25 መሠሪ ዘዴ ተጠቅሞ ብዙዎችን በማታለል ረገድ ይሳካለታል፤ በልቡም ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜም* በብዙዎች ላይ ጥፋት ያደርሳል። አልፎ ተርፎም የልዑላን ልዑል በሆነው ላይ ይነሳል፤ ሆኖም የሰው እጅ ሳይነካው ይሰበራል።
26 “ምሽቶቹንና ንጋቶቹን በተመለከተ በራእይ የተነገረው ነገር እውነት ነው፤ አንተ ግን ራእዩን በሚስጥር ያዝ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ* የሚሆነውን ነገር የሚያመለክት ነውና።”+
27 እኔም ዳንኤል ኃይሌ ተሟጠጠ፤ ለተወሰኑ ቀናትም ታመምኩ።+ ከዚያም ተነስቼ ለንጉሡ የማከናውነውን ሥራ መሥራት ጀመርኩ፤+ ሆኖም ባየሁት ነገር የተነሳ ደንዝዤ ነበር፤ ራእዩንም ማንም ሰው ሊረዳው አልቻለም።+