ዕዝራ
4 የይሁዳና የቢንያም ጠላቶች፣+ ከግዞት የተመለሱት ሰዎች+ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ እየገነቡ መሆናቸውን ሲሰሙ 2 ወዲያውኑ ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤት መሪዎች ቀርበው እንዲህ አሏቸው፦ “ከእናንተ ጋር እንገንባ፤ ልክ እንደ እናንተ እኛም አምላካችሁን እናመልካለን፤*+ ደግሞም ወደዚህ ካመጣን ከአሦር ንጉሥ ከኤሳርሃደን+ ዘመን ጀምሮ ለእሱ መሥዋዕት ስናቀርብ ኖረናል።”+ 3 ይሁንና ዘሩባቤል፣ የሆሹዋና የቀሩት የእስራኤል አባቶች ቤት መሪዎች እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላካችንን ቤት በመገንባቱ ሥራ ከእኛ ጋር ተካፋይ መሆን አትችሉም፤+ ምክንያቱም የፋርሱ ንጉሥ፣ ንጉሥ ቂሮስ ባዘዘን መሠረት እኛው ራሳችን የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤት እንገነባለን።”+
4 የምድሪቱም ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝቦች ተስፋ ለማስቆረጥና* ወኔ ከድቷቸው የግንባታ ሥራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ዘወትር ይጥሩ ነበር።+ 5 ከፋርሱ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመን አንስቶ እስከ ፋርሱ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ+ የግዛት ዘመን ድረስ እቅዶቻቸውን ለማጨናገፍ አማካሪዎችን ቀጠሩባቸው።+ 6 በተጨማሪም በአሐሽዌሮስ የግዛት ዘመን መጀመሪያ ላይ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ በጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው። 7 ከዚህም ሌላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትረዳት፣ ታብኤልና የቀሩት ግብረ አበሮቹ ለንጉሥ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ፤ ደብዳቤውንም ወደ አረማይክ ቋንቋ+ ተርጉመው በአረማይክ ፊደል ጻፉት።*
8 * ዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ረሁም እና ጸሐፊው ሺምሻይ ኢየሩሳሌምን በመክሰስ ለንጉሥ አርጤክስስ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉ፦ 9 (ደብዳቤውን የላኩት ዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ረሁም፣ ጸሐፊው ሺምሻይና የቀሩት ግብረ አበሮቻቸው እንዲሁም ዳኞቹ፣ የበታች ገዢዎቹ፣ ጸሐፊዎቹ፣ የኤሬክ+ ሕዝቦች፣ ባቢሎናውያን፣ የሱሳ+ ነዋሪዎች ማለትም ኤላማውያን፣+ 10 ታላቁና የተከበረው አስናፈር በግዞት ወስዶ በሰማርያ ከተሞች ያሰፈራቸው+ የቀሩት ብሔራትና ከወንዙ ባሻገር* ባለው ክልል የሚኖሩት የቀሩት ሰዎች ነበሩ፤ እንግዲህ 11 የላኩለት ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው።)
“ለንጉሥ አርጤክስስ፣ ከወንዙ ባሻገር ባለው ክልል ከሚኖሩት አገልጋዮችህ፦ እንግዲህ 12 ከአንተ ዘንድ ወደዚህ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም መድረሳቸውን ንጉሡ ይወቅ። እነዚህ ሰዎች ዓመፀኛና ክፉ የሆነችውን ከተማ መልሰው እየገነቡ ነው፤ ቅጥሮቿን ሠርተው እየጨረሱ+ ሲሆን መሠረቶቿንም እየጠገኑ ነው። 13 ከተማዋ ተመልሳ ከተገነባችና ቅጥሮቿም ተሠርተው ከተጠናቀቁ እነዚህ ሰዎች ቀረጥም ሆነ ግብር+ ወይም የኬላ ቀረጥ እንደማይከፍሉ፣ በዚህም የተነሳ ወደ ነገሥታቱ ግምጃ ቤት የሚገባው ገቢ እንደሚቀንስ ንጉሡ ይወቅ። 14 እኛ ደግሞ የቤተ መንግሥቱን ጨው እየበላን* የንጉሡ ጥቅም ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ መስሎ አልታየንም፤ በመሆኑም ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያውቀው ለማድረግ ይህን ደብዳቤ ልከናል፤ 15 ስለዚህ የቀድሞ አባቶችህ መዝገብ ይመርመር።+ ይህች ከተማ ዓመፀኛና ነገሥታትንም ሆነ አውራጃዎችን ጉዳት ላይ የምትጥል፣ ከጥንት ጀምሮም ዓመፅ ቆስቋሾችን ሸሽጋ የምታኖር መሆኗን ከእነዚህ መዛግብት መረዳት ትችላለህ። ከተማዋም የተደመሰሰችው በዚህ የተነሳ ነው።+ 16 ይህች ከተማ ተመልሳ ከተገነባችና ቅጥሮቿም ተሠርተው ከተጠናቀቁ ከወንዙ+ ባሻገር ያለውን ክልል መቆጣጠር እንደማትችል* ልናሳውቅህ እንፈልጋለን።”
17 ንጉሡም ለዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ለረሁም፣ ለጸሐፊው ለሺምሻይ፣ በሰማርያ ለሚኖሩት ለቀሩት ግብረ አበሮቻቸውና ከወንዙ ባሻገር ላለው ለቀረው ክልል እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦
“ሰላምታዬ ይድረሳችሁ! እንግዲህ 18 የላካችሁልን ደብዳቤ በፊቴ ግልጽ ሆኖ ተነቧል።* 19 በሰጠሁትም ትእዛዝ መሠረት ምርመራ ተደርጎ ከተማዋ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ረብሻ የምትቀሰቅስ እንዲሁም የዓመፅና የወንጀል መፍለቂያ እንደነበረች ተረጋግጧል።+ 20 ኢየሩሳሌም ከወንዙ ባሻገር ያሉትን አካባቢዎች በሙሉ የሚገዙ ኃያላን ነገሥታት ነበሯት፤ እነሱም ቀረጥ፣ ግብርና የኬላ ቀረጥ ይቀበሉ ነበር። 21 እንግዲህ እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ከተማዋ ተመልሳ እንዳትገነባ እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲያቆሙ ትእዛዝ አስተላልፉ። 22 የነገሥታቱን ጥቅም ይበልጥ የሚጎዳ ነገር እንዳይከሰት ይህን ጉዳይ በተመለከተ እርምጃ ከመውሰድ ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ።”+
23 ንጉሥ አርጤክስስ የላከው ደብዳቤ በረሁም፣ በጸሐፊው በሺምሻይና በተባባሪዎቻቸው ፊት ከተነበበ በኋላ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወዳሉት አይሁዳውያን በመሄድ አስገድደው ሥራውን አስቆሟቸው። 24 በኢየሩሳሌም የነበረውን የአምላክን ቤት የመገንባቱ ሥራ የተቋረጠው በዚህ ጊዜ ነበር፤ እስከ ፋርሱ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ የንግሥና ዘመን ሁለተኛ ዓመት ድረስም ሥራው ባለበት ቆመ።+