ሕዝቅኤል
46 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከምሥራቅ ትይዩ የሆነው የውስጠኛው ግቢ በር+ በስድስቱ የሥራ ቀናት+ ዝግ እንደሆነ ይቆይ፤+ ሆኖም በሰንበት ቀንና አዲስ ጨረቃ በምትወጣበት ቀን ይከፈት። 2 አለቃው ከውጭ በኩል በበሩ በረንዳ ገብቶ+ በበሩ መቃን አጠገብ ይቆማል። ካህናቱ የእሱን ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ እሱም በበሩ ደፍ ላይ ይሰግዳል፤ ከዚያም ይወጣል። በሩ ግን እስከ ምሽት ድረስ አይዘጋ። 3 የምድሪቱም ነዋሪዎች በየሰንበቱና አዲስ ጨረቃ በምትወጣበት ቀን+ በበሩ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት ይሰግዳሉ።
4 “‘አለቃው በሰንበት ቀን እንከን የሌለባቸው ስድስት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና እንከን የሌለበት አንድ አውራ በግ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርጎ ማቅረብ ይኖርበታል።+ 5 ለአውራ በጉ አንድ ኢፍ* የእህል መባ፣ ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹም መስጠት የሚችለውን ያህል የእህል መባ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ኢፍ አንድ ሂን* ዘይት ያቀርባል።+ 6 አዲስ ጨረቃ በምትወጣበት ቀን ከከብቶቹ መካከል እንከን የሌለበት አንድ ወይፈን፣ ስድስት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቀርባል፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።+ 7 ለወይፈኑ አንድ ኢፍ፣ ለአውራ በጉም አንድ ኢፍ፣ ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ ደግሞ መስጠት የሚችለውን ያህል እንደ እህል መባ አድርጎ ያቅርብ። እንዲሁም ለእያንዳንዱ ኢፍ አንድ ሂን ዘይት ያቅርብ።
8 “‘አለቃው ሲገባ፣ በበሩ በረንዳ በኩል ይግባ፤ ሲወጣም በዚያው በኩል ይውጣ።+ 9 የምድሪቱም ነዋሪዎች በበዓል ወቅቶች በይሖዋ ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ፣+ የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም በሰሜን በር+ የሚገቡ፣ በደቡብ በር ይውጡ፤ በደቡብ በር+ የሚገቡ ደግሞ በሰሜን በር ይውጡ። ማንም ሰው በገባበት በር ተመልሶ አይውጣ፤ ይልቁንም በተቃራኒ አቅጣጫ ባለው በር ይውጣ። 10 በመካከላቸው ያለው አለቃ እነሱ በሚገቡበት ጊዜ ይግባ፤ እነሱ በሚወጡበት ጊዜም ይውጣ። 11 በበዓላትና በተወሰኑት የበዓል ወቅቶች፣ ለወይፈኑ አንድ ኢፍ፣ ለአውራ በጉ አንድ ኢፍ፣ ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ ደግሞ መስጠት የሚችለውን ያህል የእህል መባ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ኢፍ አንድ ሂን ዘይት ያቅርብ።+
12 “‘አለቃው ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባን+ ወይም የኅብረት መሥዋዕትን የፈቃደኝነት መባ አድርጎ ለይሖዋ የሚያቀርብ ከሆነ በምሥራቅ ትይዩ ያለው በር ይከፈትለታል፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠለውን መባውንና የኅብረት መሥዋዕቱን ያቀርባል።+ ከወጣ በኋላ በሩ ይዘጋ።+
13 “‘በየዕለቱ፣ እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርገህ ለይሖዋ አቅርብ።+ ይህን በየማለዳው አድርግ። 14 ከዚህም ጋር በየማለዳው የኢፍ አንድ ስድስተኛ የእህል መባ እንዲሁም በላመው ዱቄት ላይ የሚፈስ የሂን አንድ ሦስተኛ ዘይት የዘወትር የእህል መባ አድርገህ ለይሖዋ አቅርብ። ይህ የዘላለም ደንብ ነው። 15 ተባዕቱን የበግ ጠቦት፣ የእህል መባውንና ዘይቱን ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል የዘወትር መባ አድርገው በየማለዳው ያቅርቡ።’
16 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አለቃው ለወንዶች ልጆቹ፣ ለእያንዳንዳቸው ውርስ አድርጎ ስጦታ ቢሰጣቸው፣ ስጦታው የልጆቹ ንብረት ይሆናል። ይህ በውርስ ያገኙት ንብረታቸው ነው። 17 ሆኖም ከአገልጋዮቹ ለአንዱ ከርስቱ ላይ ስጦታ ቢሰጥ፣ ነፃ እስከሚወጣበት ዓመት+ ድረስ ስጦታው የእሱ ይሆናል፤ ከዚያም ለአለቃው ይመለስለታል። ርስቱን ለዘለቄታው የራሳቸው አድርገው መያዝ የሚችሉት ወንዶች ልጆቹ ብቻ ናቸው። 18 አለቃው ሕዝቡን ከይዞታቸው በማፈናቀል የትኛውንም ርስት ሊወስድባቸው አይገባም። ከሕዝቤ መካከል አንዳቸውም ከይዞታቸው እንዳይፈናቀሉ ለወንዶች ልጆቹ ርስት መስጠት ያለበት ከራሱ ይዞታ ላይ ነው።’”
19 ከዚያም ከሰሜን ትይዩ ወደሚገኙት ቅዱስ ወደሆኑት የካህናቱ መመገቢያ ክፍሎች*+ ከሚወስደው በር አጠገብ ባለው መግቢያ+ በኩል አድርጎ አመጣኝ፤ በዚያም በምዕራብ በኩል ከበስተ ኋላ አንድ ቦታ አየሁ። 20 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ካህናቱ አንድም ነገር ወደ ውጨኛው ግቢ ይዘው በመውጣት ቅድስናን ወደ ሕዝቡ እንዳያስተላልፉ*+ ሲባል የበደል መባውንና የኃጢአት መባውን የሚቀቅሉት እንዲሁም የእህል መባውን የሚጋግሩት+ በዚህ ቦታ ነው።”
21 ከዚያም ወደ ውጨኛው ግቢ ከወሰደኝ በኋላ በአራቱ የግቢው ማዕዘኖች በኩል አዞረኝ፤ በውጨኛው ግቢ በአራቱም ማዕዘኖች በኩል ግቢ አየሁ። 22 በአራቱም የግቢው ማዕዘኖች፣ ርዝመታቸው 40 ክንድ፣* ወርዳቸው 30 ክንድ የሆኑ ትናንሽ ግቢዎች ነበሩ። አራቱም መጠናቸው እኩል ነበር።* 23 በአራቱም ዙሪያ እርከን* የነበረ ሲሆን ከእርከኑ ሥር መባዎቹ የሚቀቀሉባቸው ቦታዎች ተሠርተው ነበር። 24 ከዚያም “እነዚህ፣ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው+ ቦታዎች ናቸው” አለኝ።