ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
22 መልአኩም ከአምላክና ከበጉ+ ዙፋን ወጥቶ የሚፈሰውን እንደ ክሪስታል የጠራ የሕይወት ውኃ ወንዝ አሳየኝ፤+ 2 ወንዙም በከተማዋ አውራ ጎዳና መካከል ቁልቁል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈሩ በዓመት 12 ጊዜ ፍሬ የሚሰጡ የሕይወት ዛፎች ነበሩ። የዛፎቹም ቅጠሎች ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ ነበሩ።+
3 በዚያም ከእንግዲህ እርግማን አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የአምላክና የበጉ ዙፋን+ በከተማዋ ውስጥ ይሆናል፤ ባሪያዎቹም ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡለታል፤ 4 ፊቱንም ያያሉ፤+ ስሙም በግንባራቸው ላይ ይሆናል።+ 5 በተጨማሪም ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤+ ይሖዋ* አምላክ በእነሱ ላይ ብርሃን ስለሚፈነጥቅ የመብራት ብርሃንም ሆነ የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤+ ደግሞም ለዘላለም ይነግሣሉ።+
6 መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና* እውነት ናቸው፤+ አዎ፣ ነቢያት በመንፈስ መሪነት እንዲናገሩ የሚያደርገው ይሖዋ* አምላክ፣+ በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፈጸም ያለባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ ለማሳየት መልአኩን ልኳል። 7 እነሆ፣ እኔ ቶሎ እመጣለሁ።+ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሚገኙትን የትንቢት ቃላት የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው ደስተኛ ነው።”+
8 እነዚህን ነገሮች ስሰማና ስመለከት የነበርኩት እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ እያሳየኝ ለነበረው መልአክ ልሰግድ እግሩ ሥር ተደፋሁ። 9 እሱ ግን “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! እኔ ከአንተም ሆነ ነቢያት ከሆኑት ወንድሞችህና በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሰፈሩትን ቃላት ከሚጠብቁት ሁሉ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ። ለአምላክ ስገድ” አለኝ።+
10 ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ “የተወሰነው ጊዜ ስለቀረበ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሰፈሩትን የትንቢት ቃላት በማኅተም አታሽጋቸው። 11 ጻድቅ ያልሆነ፣ በዓመፅ ጎዳናው ይቀጥል፤ ርኩስ የሆነውም በርኩሰቱ ይቀጥል፤ ጻድቅ የሆነው ግን በጽድቅ ጎዳና መመላለሱን ይቀጥል፤ ቅዱስ የሆነውም በቅድስና ይቀጥል።
12 “‘እነሆ፣ እኔ ቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምከፍለው ብድራት ከእኔ ጋር ነው።+ 13 እኔ አልፋና ኦሜጋ፣*+ ፊተኛውና ኋለኛው፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ። 14 ከሕይወት ዛፎች ፍሬ የመብላት መብት እንዲያገኙና+ በበሮቿ+ በኩል ወደ ከተማዋ መግባት እንዲፈቀድላቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ+ ደስተኞች ናቸው። 15 ውሾች፣* መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ ሴሰኞች፣* ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች እንዲሁም ውሸትን የሚወዱና የሚዋሹ ሁሉ ከከተማዋ ውጭ አሉ።’+
16 “‘እኔ ኢየሱስ ለጉባኤዎቹ ጥቅም ስል ስለ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ለመመሥከር መልአኬን ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር+ እንዲሁም ደማቅ አጥቢያ ኮከብ+ ነኝ።’”
17 መንፈሱና ሙሽራይቱም+ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም ሁሉ “ና!” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤+ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።+
18 “በዚህ ጥቅልል ላይ የሰፈሩትን የትንቢት ቃላት ለሚሰማ ሁሉ እመሠክራለሁ፦ ማንም በእነዚህ ነገሮች ላይ አንዲት ነገር ቢጨምር+ አምላክ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የተጻፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፤+ 19 ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ ከሰፈሩት ቃላት አንዲት ነገር ቢያጎድል አምላክ በዚህ ጥቅልል ላይ ከተጠቀሱት የሕይወት ዛፎችና+ ከቅድስቲቱ ከተማ+ ዕጣ ፋንታውን ይወስድበታል።
20 “ስለ እነዚህ ነገሮች የሚመሠክረው ‘አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ’+ ይላል።”
“አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና።”
21 የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከቅዱሳኑ ጋር ይሁን።