ኤርምያስ
52 ሴዴቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እናቱ ሀሙጣል+ ትባል ነበር፤ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2 ሴዴቅያስም ኢዮዓቄም እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 3 እነዚህ ነገሮች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የተፈጸሙት ከይሖዋ ቁጣ የተነሳ ነው፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።+ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዓመፀ።+ 4 ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ሠራዊቱን ሁሉ አስከትሎ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። በዙሪያዋም ሰፈሩ፤ ደግሞም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ቆለሉ።+ 5 ከተማዋም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ 11ኛ ዓመት ድረስ ተከበበች።
6 በአራተኛው ወር፣ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን+ በከተማዋ ውስጥ ረሃቡ እጅግ ከፋ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትም ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጡ።+ 7 በመጨረሻም የከተማዋ ቅጥር ተነደለ፤ ከለዳውያን ከተማዋን ከበው ሳለም ወታደሮቹ ሁሉ በንጉሡ የአትክልት ቦታ አቅራቢያ ባለው መንገድ፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር በኩል በሌሊት ከከተማዋ ወጥተው ሸሹ፤ ወደ አረባ የሚወስደውንም አቅጣጫ ይዘው ሄዱ።+ 8 ይሁንና የከለዳውያን ሠራዊት ንጉሡን አሳደደ፤ ሴዴቅያስንም+ በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ጥለውት ተበታተኑ። 9 ከዚያም ንጉሡን ይዘው በሃማት ምድር በምትገኘው በሪብላ ወደነበረው የባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ እሱም ፈረደበት። 10 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አረዳቸው፤ በተጨማሪም የይሁዳን መኳንንት ሁሉ በዚያው በሪብላ አረዳቸው። 11 ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ዓይን አሳወረ፤+ በመዳብ የእግር ብረት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ በእስር ቤት አቆየው።
12 በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ናቡከደነጾር* በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ የዘቦች አለቃና የባቢሎን ንጉሥ አገልጋይ የሆነው ናቡዛራዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።+ 13 እሱም የይሖዋን ቤት፣ የንጉሡን ቤትና* በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ አቃጠለ፤+ ትላልቅ ቤቶችንም ሁሉ በእሳት አጋየ። 14 ከዘቦቹ አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሰ።+
15 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን ችግረኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል የተወሰኑትንና በከተማዋ የቀሩትን በሕይወት የተረፉ ሰዎች አጋዘ። በተጨማሪም ከድተው ለባቢሎን ንጉሥ እጃቸውን የሰጡትን ሰዎችና የቀሩትን የተካኑ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ወሰደ።+ 16 ሆኖም የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን፣ በምድሪቱ ከነበሩት ያጡ የነጡ ድሆች መካከል አንዳንዶቹ የወይን አትክልት ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉና የግዳጅ አገልግሎት እንዲሰጡ በዚያው ተዋቸው።+
17 ከለዳውያን የይሖዋን ቤት የመዳብ ዓምዶች+ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትን የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችና+ የመዳብ ባሕር+ ሰባብረው መዳቡን በሙሉ ወደ ባቢሎን አጋዙ።+ 18 በተጨማሪም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ የእሳት ማጥፊያዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹን፣+ ጽዋዎቹንና+ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የመዳብ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። 19 የዘቦቹ አለቃ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ዕቃዎች+ ይኸውም ሳህኖቹን፣+ መኮስተሪያዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹን፣ አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ መቅረዞቹን፣+ ጽዋዎቹንና ሌሎቹን ጎድጓዳ ሳህኖች ወሰደ። 20 ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ ቤት ያሠራቸው ሁለቱ ዓምዶች፣ ባሕሩ፣ ከባሕሩ ሥር ያሉት 12 የመዳብ በሬዎችና+ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹ የተሠሩበት መዳብ ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የሚችል አልነበረም።
21 ዓምዶቹ እያንዳንዳቸው 18 ክንድ* ቁመት ነበራቸው፤ የዙሪያቸው መጠን በመለኪያ ገመድ 12 ክንድ፣+ ውፍረታቸውም አራት ጣት* ሲሆን ውስጣቸው ክፍት ነበር። 22 በዓምዱም አናት ላይ ያለው ጌጥ ከመዳብ የተሠራ ነበር፤ የአንዱ ጌጥ ርዝማኔ አምስት ክንድ+ ሲሆን በዙሪያው ያሉት ሮማኖችና መረቡ በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። ሁለተኛው ዓምድ፣ ሮማኖቹን ጨምሮ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር። 23 በጎኖቹ ላይ* 96 ሮማኖች የነበሩ ሲሆን በመረቡ ዙሪያ ያሉት ሮማኖች በጠቅላላ 100 ነበሩ።+
24 በተጨማሪም የዘቦቹ አለቃ የካህናት አለቃ የሆነውን ሰራያህን፣+ ሁለተኛውን ካህን ሶፎንያስንና+ ሦስቱን የበር ጠባቂዎች ወሰዳቸው።+ 25 ደግሞም ከከተማዋ የወታደሮቹ ኃላፊ የሆነን አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን፣ በከተማዋ ውስጥ የነበሩትን ሰባቱን የንጉሡ የቅርብ ሰዎች፣ የምድሪቱን ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ እንዲሁም ከተማዋ ውስጥ የተገኙትን በምድሪቱ የሚኖሩ 60 ተራ ሰዎች ወሰደ። 26 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን እነዚህን ሰዎች ይዞ፣ በሪብላ ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው። 27 የባቢሎን ንጉሥ በሃማት ምድር ባለችው በሪብላ+ ሰዎቹን መትቶ ገደላቸው። በዚህ መንገድ ይሁዳ ከምድሩ በግዞት ተወሰደ።+
28 ናቡከደነጾር* በግዞት የወሰዳቸው ሰዎች እነዚህ ናቸው፦ በሰባተኛው ዓመት 3,023 አይሁዳውያንን ወሰደ።+
29 በናቡከደነጾር* 18ኛ ዓመት+ ከኢየሩሳሌም 832 ሰዎች* ተጋዙ።
30 ናቡከደነጾር* በነገሠ በ23ኛው ዓመት፣ የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን ከአይሁዳውያን መካከል 745 ሰዎችን* በግዞት ወሰደ።+
በአጠቃላይ 4,600 ሰዎች* በግዞት ተወሰዱ።
31 ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ ኤዊልሜሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን+ ፈታው፤* ከእስር ቤትም አወጣው፤+ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በግዞት በተወሰደ በ37ኛው ዓመት፣ በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በ25ኛው ቀን ነበር። 32 በርኅራኄም አናገረው፤ ዙፋኑንም በባቢሎን ከእሱ ጋር ከነበሩት ከሌሎች ነገሥታት ዙፋን ይበልጥ ከፍ ከፍ አደረገለት። 33 በመሆኑም ዮአኪን የእስር ቤት ልብሱን አወለቀ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ በቋሚነት ከንጉሡ ማዕድ ይመገብ ነበር። 34 የባቢሎን ንጉሥ፣ ዮአኪን እስከሞተበት ጊዜ ድረስ፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ ቀለቡን በየዕለቱ ይሰጠው ነበር።