የሐዋርያት ሥራ
11 በይሁዳ የነበሩት ሐዋርያትና ወንድሞች፣ አሕዛብም የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ ሰሙ። 2 ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ግርዘትን የሚደግፉ ሰዎች+ ይተቹት* ጀመር፤ 3 “ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ሄደህ ከእነሱ ጋር በልተሃል” አሉት። 4 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጉዳዩን በዝርዝር አብራራላቸው፦
5 “በኢዮጴ ከተማ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ሆኜ ራእይ አየሁ፤ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱም ጫፍ ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ።+ 6 ይህን ነገር ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸው የምድር እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና የሰማይ ወፎች አየሁ። 7 በተጨማሪም አንድ ድምፅ ‘ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!’ ሲለኝ ሰማሁ። 8 እኔ ግን ‘ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም ንጹሕ ያልሆነ ወይም የረከሰ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ። 9 ለሁለተኛ ጊዜ ከሰማይ የመጣው ድምፅ ‘አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው’ ሲል መለሰልኝ። 10 ይህም ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ፤ ከዚያም ሁሉም ነገር እንደገና ወደ ሰማይ ተወሰደ። 11 ልክ በዚያው ሰዓት ደግሞ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኛ ወደነበርንበት ቤት ደረሱ።+ 12 በዚህ ጊዜ መንፈስ፣ ምንም ሳልጠራጠር አብሬያቸው እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህ ስድስት ወንድሞችም አብረውኝ ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን።
13 “እሱም በቤቱ ውስጥ መልአክ ቆሞ እንዳየና እንዲህ እንዳለው ነገረን፦ ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራ፤+ 14 እሱም አንተና መላው ቤተሰብህ መዳን ልታገኙ የምትችሉበትን ነገር ሁሉ ይነግርሃል።’ 15 እኔም መናገር ስጀምር መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደወረደው ሁሉ በእነሱም ላይ ወረደ።+ 16 በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤+ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’+ እያለ ጌታ ይናገር የነበረውን ቃል አስታወስኩ። 17 እንግዲህ አምላክ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ የሰጠውን ያንኑ ነፃ ስጦታ ለእነሱም ከሰጠ፣ ታዲያ አምላክን መከልከል* የምችል እኔ ማን ነኝ?”+
18 እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ መቃወማቸውን ተዉ፤* ደግሞም “እንዲህ ከሆነማ አምላክ አሕዛብም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ንስሐ የሚገቡበት አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው” እያሉ አምላክን አከበሩ።+
19 ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተቀሰቀሰው ስደት የተነሳ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት+ እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄዱ፤ ቃሉን ይናገሩ የነበረው ግን ለአይሁዳውያን ብቻ ነበር።+ 20 ይሁን እንጂ ከእነሱ መካከል የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የሆኑ አንዳንዶች ወደ አንጾኪያ መጥተው ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን በማነጋገር የጌታ ኢየሱስን ምሥራች ይሰብኩላቸው ጀመር። 21 የይሖዋም* እጅ ከእነሱ ጋር ነበር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም አማኝ በመሆን ጌታን መከተል ጀመሩ።+
22 በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ ስለ እነሱ የሚገልጸው ወሬ ደረሰው፤ በዚህ ጊዜ በርናባስን+ ወደ አንጾኪያ ላኩት። 23 እሱም እዚያ ደርሶ አምላክ ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየውን ጸጋ ባስተዋለ ጊዜ በጣም ተደሰተ፤ ሁሉም በጽኑ ልብ ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉም አበረታታቸው፤+ 24 በርናባስ መንፈስ ቅዱስ የሞላበትና ጠንካራ እምነት ያለው ጥሩ ሰው ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም በጌታ አመኑ።+ 25 በመሆኑም ሳኦልን ፈልጎ ለማግኘት ወደ ጠርሴስ ሄደ።+ 26 ካገኘውም በኋላ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ከዚያም አንድ ዓመት ሙሉ ከእነሱ ጋር በጉባኤ አብረው እየተሰበሰቡ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት+ በአንጾኪያ ነበር።
27 በዚያን ጊዜ ነቢያት+ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። 28 ከእነሱም መካከል አጋቦስ+ የተባለው ተነስቶ በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት መንፈስ አነሳስቶት ትንቢት ተናገረ፤+ ይህም በቀላውዴዎስ ዘመን ተፈጸመ። 29 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን+ አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ፤+ 30 እርዳታውንም በበርናባስና በሳኦል እጅ ለሽማግሌዎቹ ላኩ።+