ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
4 እንዲህ ከሆነ ታዲያ በሥጋ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? 2 ለምሳሌ አብርሃም ጻድቅ የተባለው በሥራ ቢሆን ኖሮ የሚመካበት ነገር በኖረው ነበር፤ ሆኖም በአምላክ ፊት ሊመካ አይችልም። 3 የቅዱስ መጽሐፉስ ቃል ምን ይላል? “አብርሃም በይሖዋ* አመነ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”+ 4 ይሁንና ለሚሠራ ሰው ደሞዙ እንደ ሥራው ዋጋ* እንጂ እንደ ጸጋ ስጦታ ተደርጎ አይቆጠርለትም። 5 በሌላ በኩል ግን በራሱ ሥራ ከመመካት ይልቅ ኃጢአተኛውን ጻድቅ ነህ ብሎ በሚጠራው አምላክ የሚያምን እምነቱ እንደ ጽድቅ ይቆጠርለታል።+ 6 ይህም ዳዊት፣ አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ስለሚያገኘው ደስታ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ 7 “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው* ደስተኞች ናቸው፤ 8 ይሖዋ* ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።”+
9 ታዲያ ይህን ደስታ የሚያገኙት የተገረዙ ሰዎች ብቻ ናቸው ወይስ ያልተገረዙትም ጭምር?+ ምክንያቱም “አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ብለናል።+ 10 ታዲያ እምነቱ እንደ ጽድቅ የተቆጠረው በምን ዓይነት ሁኔታ እያለ ነው? ተገርዞ እያለ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? ተገርዞ እያለ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው። 11 ገና ከመገረዙ በፊት በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን+ ግርዘትን እንደ ማኅተም* ተቀበለ፤ ስለዚህ ባይገረዙም እንኳ በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት ሆኗል፤+ 12 ለተገረዙት ዘሮቹም አባት ነው፤ ይሁንና ግርዘትን አጥብቀው ለሚከተሉት ብቻ ሳይሆን አባታችን አብርሃም+ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት ተከትለው በሥርዓት ለሚመላለሱ ሰዎችም ሁሉ አባት ነው።
13 ምክንያቱም አብርሃም ወይም ዘሩ የዓለም ወራሽ+ እንደሚሆን ተስፋ የተሰጠው በሕግ አማካኝነት ሳይሆን በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ነው።+ 14 ወራሾች የሚሆኑት ሕጉን በጥብቅ የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ እምነት ከንቱ በሆነ ነበርና፤ የተስፋውም ቃል ባከተመ ነበር። 15 እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ቁጣ ያስከትላል፤+ ሆኖም ሕግ ከሌለ ሕግን መተላለፍ የሚባል ነገር አይኖርም።+
16 በመሆኑም ተስፋው በእምነት የተገኘ ነው፤ ይህም የሆነው ተስፋው በጸጋ+ ላይ የተመሠረተ እንዲሆንና ለዘሩ ሁሉ+ ይኸውም ሕጉን በጥብቅ ለሚከተል ብቻ ሳይሆን የሁላችንም አባት+ የሆነውን የአብርሃምን እምነት በጥብቅ ለሚከተል ጭምር የተረጋገጠ እንዲሆን ነው። 17 (ይህም “ለብዙ ብሔራት አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።)+ ይህ የሆነው እሱ ባመነበት ማለትም ሙታንን ሕያው በሚያደርገውና የሌለውን እንዳለ አድርጎ በሚጠራው* አምላክ ፊት ነው። 18 ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም መሠረት ባይኖርም እንኳ “የአንተም ዘር እጅግ ይበዛል”+ ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል። 19 እምነቱ ባይዳከምም እንኳ 100 ዓመት ገደማ+ ሆኖት ስለነበር የሞተ ያህል ስለሆነው የገዛ ራሱ አካል እንዲሁም ሙት* ስለሆነው የሣራ ማህፀን አሰበ።+ 20 ሆኖም አምላክ ከሰጠው የተስፋ ቃል የተነሳ ለአምላክ ክብር በመስጠት በእምነት በረታ እንጂ እምነት በማጣት አልወላወለም፤ 21 ደግሞም አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር።+ 22 በመሆኑም “ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”+
23 ሆኖም “ተቆጠረለት” ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ብቻ አይደለም፤+ 24 ከዚህ ይልቅ እንደ ጻድቃን ስለምንቆጠረው ስለ እኛም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስን ከሞት ባስነሳው በእሱ እናምናለን።+ 25 ኢየሱስ ስለ በደላችን ለሞት አልፎ ተሰጠ፤+ አምላክ ጻድቃን ናችሁ ብሎ እንዲያስታውቅልንም ከሞት ተነሳ።+