147 ያህን አወድሱ!
ለአምላካችን የውዳሴ መዝሙር መዘመር ጥሩ ነው፤
እሱን ማወደስ ደስ ያሰኛል፤ ደግሞም ተገቢ ነው።+
2 ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ይገነባል፤+
የተበተኑትን የእስራኤል ነዋሪዎች ይሰበስባል።+
3 የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤
ቁስላቸውን ይፈውሳል።
4 የከዋክብትን ብዛት ይቆጥራል፤
ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።+
5 ጌታችን ታላቅ ነው፤ ደግሞም እጅግ ኃያል ነው፤+
ማስተዋሉም ወሰን የለውም።+
6 ይሖዋ የዋሆችን ያነሳል፤+
ክፉዎችን ግን መሬት ላይ ይጥላል።
7 ለይሖዋ በምስጋና ዘምሩ፤
ለአምላካችን በበገና የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ፤
8 እሱ ሰማያትን በደመናት ይሸፍናል፤
ለምድር ዝናብ ይሰጣል፤+
በተራሮች ላይ ሣር እንዲበቅል ያደርጋል።+
9 ለእንስሳት እንዲሁም የሚበሉትን ለማግኘት ለሚጮኹ የቁራ ጫጩቶች
ምግብ ይሰጣል።+
10 በፈረስ ጉልበት አይደሰትም፤+
የሰው እግር ጥንካሬም አያስደንቀውም።+
11 ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እሱን በሚፈሩ፣
ታማኝ ፍቅሩን በሚጠባበቁ ሰዎች ይደሰታል።+
12 ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ይሖዋን ከፍ ከፍ አድርጊ።
ጽዮን ሆይ፣ አምላክሽን አወድሺ።
13 እሱ የከተማሽን በሮች መወርወሪያዎች ያጠናክራል፤
በውስጥሽ ያሉትን ወንዶች ልጆች ይባርካል።
14 በክልልሽ ውስጥ ሰላም ያሰፍናል፤+
ምርጥ በሆነ ስንዴ ያጠግብሻል።+
15 ትእዛዙን ወደ ምድር ይልካል፤
ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል።
16 በረዶን እንደ ሱፍ ይልካል፤+
አመዳዩን እንደ አመድ ይበትናል።+
17 የበረዶውን ድንጋይ እንደ ዳቦ ፍርፋሪ ይወረውራል።+
እሱ የሚልከውን ቅዝቃዜ ማን ሊቋቋም ይችላል?+
18 ቃሉን ይልካል፤ እነሱም ይቀልጣሉ።
ነፋሱ እንዲነፍስ ያደርጋል፤+ ውኃውም ይፈስሳል።
19 ቃሉን ለያዕቆብ፣
ሥርዓቱንና ፍርዶቹን ለእስራኤል ያስታውቃል።+
20 ይህን ለሌላ ለማንም ብሔር አላደረገም፤+
እነሱ ስለ ፍርዶቹ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።
ያህን አወድሱ!+