የሐዋርያት ሥራ
6 በዚያን ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ።+ 2 ስለዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ ጠርተው እንዲህ አሏቸው፦ “በማዕድ ምግብ ለማከፋፈል ስንል የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራችንን ብንተው ተገቢ አይሆንም።+ 3 ስለዚህ ወንድሞች፣ ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ እንድንሾማቸው ከእናንተ መካከል መልካም ስም ያተረፉ፣*+ በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ+ ሰባት ወንዶች ምረጡ፤+ 4 እኛ ግን በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ* ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን።” 5 የተናገሩት ነገር ሁሉንም ደስ አሰኛቸው፤ ስለሆነም ጠንካራ እምነት የነበረውንና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣+ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞንን፣ ፓርሜናስንና ወደ ይሁዲነት ተለውጦ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። 6 ሐዋርያትም ፊት አቀረቧቸው፤ እነሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።+
7 ከዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤+ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤+ በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ።+
8 እስጢፋኖስም ጸጋና ኃይል ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ታላላቅ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ይፈጽም ነበር። 9 ይሁን እንጂ ‘ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ’ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከተወሰኑ የቀሬና፣ የእስክንድርያ፣ የኪልቅያና የእስያ ሰዎች ጋር መጥተው እስጢፋኖስን ተከራከሩት። 10 ይሁንና ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።+ 11 ስለዚህ “ይህ ሰው በሙሴና በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው እንዲናገሩ አንዳንድ ሰዎችን በድብቅ አግባቡ። 12 በተጨማሪም ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም ጸሐፍትን ቀሰቀሱ፤ ከዚያም ድንገት መጡና በኃይል ይዘው ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ ወሰዱት። 13 የሐሰት ምሥክሮችም አቀረቡ፤ እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ይህን ቅዱስ ስፍራና ሕጉን የሚቃወም ነገር ከመናገር ሊቆጠብ አልቻለም። 14 ለምሳሌ ያህል፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ እንደሚያፈርሰውና ሙሴ ያስተላለፈልንን ወግ እንደሚለውጥ ሲናገር ሰምተነዋል።”
15 በሳንሄድሪን ሸንጎ ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ ትኩር ብለው ሲያዩት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።