ኢሳይያስ
39 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ፣ የባላዳን ልጅ ሜሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ ታሞ እንደነበረና ከሕመሙ እንዳገገመ በመስማቱ ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።+ 2 ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ ከዚያም ግምጃ ቤቱን ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውን ሁሉና በግምጃ ቤቶቹ+ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው። ሕዝቅያስ በቤቱም* ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።
3 ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።+ 4 ቀጥሎም “በቤትህ* ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ* ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።
5 በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋን ቃል ስማ፤ 6 ‘እነሆ፣ በቤትህ* ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል። አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’+ ይላል ይሖዋ።+ 7 ‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”+
8 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው” አለው። አክሎም እንዲህ አለ፦ “ምክንያቱም በእኔ የሕይወት ዘመን* ሰላምና መረጋጋት* ይኖራል።”+