ዕዝራ
6 በዚያን ጊዜ ንጉሥ ዳርዮስ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነሱም በባቢሎን የሚገኘውን ውድ ነገሮች የሚቀመጡበትን ግምጃ ቤት* መረመሩ። 2 በሜዶን አውራጃ፣ በኤክባታና* ውስጥ በሚገኘው የተመሸገ ስፍራ አንድ ጥቅልል ተገኘ፤ በላዩም ላይ የሚከተለው መልእክት ተጽፎ ነበር፦
3 “ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ ንጉሥ ቂሮስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የአምላክ ቤት አስመልክቶ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፦+ ‘መሥዋዕቶችን በዚያ ማቅረብ እንዲችሉ ቤቱ ተመልሶ ይገንባ፤ መሠረቶቹም ይጣሉ፤ ቁመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 60 ክንድ+ ሆኖ 4 ትላልቅ ድንጋዮችን በሦስት ዙር በመደራረብና በላዩ ላይ አንድ ዙር ሳንቃ በማድረግ ይሠራ፤+ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይከፈል።+ 5 በተጨማሪም ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የወርቅና የብር ዕቃዎች ይመለሱ፤+ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ተወስደው በቀድሞ ቦታቸው ላይ ይደረጉ፤ በአምላክም ቤት ውስጥ ይቀመጡ።’+
6 “አሁንም ከወንዙ ባሻገር* ያለው ክልል ገዢ የሆንከው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና ከወንዙ ባሻገር የሚገኙ የበታች ገዢዎች የሆኑት ግብረ አበሮቻችሁ ከዚያ ራቁ።+ 7 በአምላክ ቤት ሥራ ጣልቃ አትግቡ። የአይሁዳውያን ገዢዎችና የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ያንን የአምላክ ቤት በቀድሞ ቦታው ላይ መልሰው ይገንቡት። 8 በተጨማሪም እነዚህ የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ያን የአምላክ ቤት መልሰው ሲገነቡ ልታደርጉላቸው የሚገባውን ነገር በተመለከተ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፦ ሥራው እንዳይስተጓጎል ከንጉሡ ግምጃ ቤት+ ይኸውም ከወንዙ ባሻገር ካለው ክልል ከተሰበሰበው ቀረጥ ላይ ተወስዶ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በአፋጣኝ ይሸፈንላቸው።+ 9 ለሰማይ አምላክ ለሚቀርቡት የሚቃጠሉ መባዎች የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ይኸውም ወይፈኖች፣+ አውራ በጎች፣+ የበግ ጠቦቶች፣+ ስንዴ፣+ ጨው፣+ የወይን ጠጅና+ ዘይት+ በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚጠይቁት መሠረት በየቀኑ ያለማቋረጥ ይሰጣቸው፤ 10 ይህም የሚደረገው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኙ መባዎችን ዘወትር እንዲያቀርቡ እንዲሁም ለንጉሡና ለልጆቹ ደህንነት እንዲጸልዩ ነው።+ 11 ከዚህ በተጨማሪ ይህን አዋጅ የጣሰ ማንኛውም ሰው ለዚህ ጥፋቱ ከቤቱ ምሰሶ እንዲነቀልና ወደ ላይ ከፍ ተደርጎ ላዩ ላይ እንዲቸነከር* እንዲሁም ቤቱ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት* እንዲሆን አዝዣለሁ። 12 ስሙ በዚያ እንዲኖር ያደረገው አምላክ+ ይህን ትእዛዝ ለመቃወምና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ያንን የአምላክ ቤት ለማጥፋት እጁን የሚያነሳን ማንኛውንም ንጉሥም ሆነ ሕዝብ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። ይህም በአስቸኳይ ተግባራዊ ይደረግ።”
13 ከዚያም ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና+ ግብረ አበሮቻቸው ንጉሥ ዳርዮስ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ተግባራዊ አደረጉ። 14 የአይሁዳውያን ሽማግሌዎችም ነቢዩ ሐጌና+ የኢዶ የልጅ ልጅ ዘካርያስ+ በተናገሩት ትንቢት ተበረታተው ግንባታውን ማከናወናቸውንና ሥራውን ማፋጠናቸውን ቀጠሉ፤+ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ መሠረት+ እንዲሁም በቂሮስ፣+ በዳርዮስና+ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ+ ትእዛዝ መሠረት ቤቱን ገንብተው አጠናቀቁ። 15 ቤቱንም በአዳር* ወር በሦስተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ሠርተው አጠናቀቁ።
16 ከዚያም እስራኤላውያን፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና+ በግዞት ተወስደው የነበሩት የቀሩት ሰዎች የአምላክን ቤት ምርቃት* በደስታ አከበሩ። 17 ለአምላክ ቤት ምርቃትም 100 በሬዎችን፣ 200 አውራ በጎችንና 400 የበግ ጠቦቶችን እንዲሁም ለመላው እስራኤል የኃጢአት መባ እንዲሆኑ በእስራኤል ነገዶች ቁጥር ልክ 12 አውራ ፍየሎችን አቀረቡ።+ 18 እንዲሁም በሙሴ መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት+ በኢየሩሳሌም ለሚቀርበው የአምላክ አገልግሎት ካህናቱን በየክፍላቸው፣ ሌዋውያኑንም በየምድባቸው ሾሙ።+
19 በግዞት ተወስደው የነበሩት ሰዎች በመጀመሪያው ወር በ14ኛው ቀን ላይ ፋሲካን* አከበሩ።+ 20 ካህናቱና ሌዋውያኑ በሙሉ ራሳቸውን ስላነጹ+ ሁሉም ንጹሕ ሆነው ነበር፤ እነሱም በግዞት ተወስደው ለነበሩት ሰዎች በሙሉ፣ አብረዋቸው ለሚያገለግሉት ካህናትና ለራሳቸው የፋሲካውን እርድ አረዱ። 21 ከዚያም ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን በምድሪቱ ከነበሩት ብሔራት ርኩሰት ራሳቸውን በመለየት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለማምለክ* ከእነሱ ጋር ከተቀላቀሉት ሁሉ ጋር ሆነው በሉት።+ 22 በተጨማሪም ይሖዋ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸውና የእስራኤል አምላክ የሆነውን የእውነተኛውን አምላክ ቤት ይሠሩ ዘንድ እንዲረዳቸው* የአሦርን ንጉሥ ልብ ስላራራላቸው+ የቂጣን* በዓል+ ለሰባት ቀን በደስታ አከበሩ።