ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ
2 አንተ ግን ምንጊዜም ከትክክለኛ* ትምህርት ጋር የሚስማማ ነገር ተናገር።+ 2 አረጋውያን ወንዶች በልማዶቻቸው ረገድ ልከኞች፣ ቁም ነገረኞች፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው እንዲሁም በእምነት፣ በፍቅርና በጽናት ጤናሞች ይሁኑ። 3 በተመሳሳይም አረጋውያን ሴቶች ለቅዱሳን ሰዎች የሚገባ ባሕርይ ያላቸው፣ ስም የማያጠፉ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ እንዲሁም ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ 4 ይህም ወጣት ሴቶችን በመምከር* ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ 5 ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ንጹሐን፣ በቤት ውስጥ የሚሠሩ፣* ጥሩዎችና ለባሎቻቸው የሚገዙ+ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላቸዋል፤ ይህም የአምላክ ቃል እንዳይሰደብ ነው።
6 በተመሳሳይም ወጣት ወንዶች ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው አሳስባቸው፤+ 7 በማንኛውም ሁኔታ መልካም ሥራ በመሥራት አርዓያ መሆንህን አሳይ። ንጹሕ የሆነውን ነገር* በቁም ነገር አስተምር፤+ 8 ደግሞም ሊነቀፍ የማይችል ጤናማ* አነጋገር በመጠቀም አስተምር፤+ ይኸውም ተቃዋሚዎች ስለ እኛ የሚናገሩት መጥፎ ነገር አጥተው እንዲያፍሩ ነው።+ 9 ባሪያዎች ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ጥረት በማድረግ በሁሉም ነገር ይገዙላቸው፤+ የአጸፋ ቃልም አይመልሱላቸው፤ 10 ደግሞም ሊሰርቋቸው አይገባም፤+ ከዚህ ይልቅ አዳኛችን የሆነው አምላክ ትምህርት በሁሉም መንገድ ውበት እንዲጎናጸፍ ያደርጉ ዘንድ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው ይሁኑ።+
11 የአምላክ ጸጋ ተገልጧልና፤ ጸጋው ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን ያስገኛል።+ 12 ይህም ጸጋ ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን+ መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት* ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር ያሠለጥነናል፤+ 13 በዚህ ሁኔታ አስደሳች የሆነውን ተስፋ+ እንዲሁም የታላቁን አምላክና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በክብር መገለጥ እንጠባበቃለን፤ 14 ክርስቶስ ከማንኛውም ዓይነት የዓመፅ ሕይወት እኛን ነፃ ለማውጣትና*+ ለመልካም ሥራ የሚቀና+ ልዩ ንብረቱ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል።+
15 እነዚህን ነገሮች፣ በሙሉ ሥልጣን መናገርህን፣ አጥብቀህ መምከርህንና* መውቀስህን ቀጥል።+ ማንም ሰው ፈጽሞ አይናቅህ።