ዘዳግም
1 ሙሴ በዮርዳኖስ ክልል በሚገኘው ምድረ በዳ ይኸውም በፋራን፣ በጦፌል፣ በላባ፣ በሃጼሮት እና በዲዛሃብ መካከል ከሚገኘው ከሱፈ ፊት ለፊት ባለው በረሃማ ሜዳ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 ወደ ሴይር ተራራ በሚወስደው መንገድ በኩል ከኮሬብ እስከ ቃዴስበርኔ+ የ11 ቀን መንገድ ነው። 3 በ40ኛው ዓመት፣+ በ11ኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሙሴ ለእስራኤላውያን* እንዲነግራቸው ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ነገራቸው። 4 ይህን ያደረገው በሃሽቦን ይኖር የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን+ ድል ካደረገና በአስታሮት ይኖር የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ኦግን+ ኤድራይ+ ላይ* ካሸነፈ በኋላ ነው። 5 በዮርዳኖስ ክልል፣ በሞዓብ ምድር ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ በማለት ያብራራ ጀመር፦+
6 “ይሖዋ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ አለን፦ ‘በዚህ ተራራማ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል።+ 7 ተነስታችሁ ወደ አሞራውያን+ ተራራማ አካባቢ እንዲሁም በአረባ፣+ በተራራማው አካባቢ፣ በሸፌላ፣ በኔጌብ እና በባሕሩ ዳርቻ+ ወደሚገኙት ጎረቤቶቻቸው ሁሉ ብሎም ወደ ከነአናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ*+ በመጓዝ እስከ ታላቁ ወንዝ ማለትም እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ+ ድረስ ሂዱ። 8 እነሆ በፊታችሁ ይህችን ምድር አስቀምጫለሁ። ይሖዋ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና+ ለያዕቆብ+ እንዲሁም ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቻቸው ሊሰጣቸው የማለላቸውን ምድር+ ገብታችሁ ውረሱ።’
9 “እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘እኔ ብቻዬን እናንተን ልሸከማችሁ አልችልም።+ 10 ይሖዋ አምላካችሁ ቁጥራችሁን አብዝቶታል፤ ይኸው ዛሬ ከብዛታችሁ የተነሳ በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት ሆናችኋል።+ 11 የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ ሺህ ጊዜ ያብዛችሁ፤+ ደግሞም በገባላችሁ ቃል መሠረት ይባርካችሁ።+ 12 ይሁንና እኔ ብቻዬን የእናንተን ሸክምና ጫና እንዲሁም ጠብ እንዴት መሸከም እችላለሁ?+ 13 ከየነገዶቻችሁ ጥበበኛና አስተዋይ የሆኑ እንዲሁም ተሞክሮ ያካበቱ ወንዶችን ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ መሪ አድርጌ እሾማቸዋለሁ።’+ 14 እናንተም ‘አድርጉ ያልከን ነገር መልካም ነው’ በማለት መለሳችሁልኝ። 15 እኔም ጥበበኛ የሆኑትንና ተሞክሮ ያካበቱትን የየነገዳችሁን መሪዎች ወስጄ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዶቻችሁ ሹማምንት አድርጌ በእናንተ ላይ ሾምኳቸው።+
16 “በዚያን ጊዜ ለዳኞቻችሁ ይህን መመሪያ ሰጠኋቸው፦ ‘በወንድሞቻችሁ መካከል የተፈጠረን አንድ ጉዳይ በምትሰሙበት ጊዜ በሰውየውና በወንድሙ ወይም በባዕድ አገሩ ሰው መካከል+ በጽድቅ ፍረዱ።+ 17 በምትፈርዱበት ጊዜ አታዳሉ።+ ትንሹንም ሆነ ትልቁን እኩል ስሙ።+ ፍርድ የአምላክ ስለሆነ+ ሰውን አትፍሩ፤+ አንድ ጉዳይ ከከበዳችሁ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም እሰማዋለሁ።’+ 18 በዚያን ጊዜ ማድረግ ስላለባችሁ ነገር ሁሉ መመሪያ ሰጠኋችሁ።
19 “ከዚያም ይሖዋ አምላካችን ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ በመነሳት ያን ያያችሁትን ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ ምድረ በዳ+ አቋርጠን ወደ አሞራውያን ተራራማ አካባቢዎች+ በሚወስደው መንገድ ተጓዝን፤ በመጨረሻም ቃዴስበርኔ+ ደረስን። 20 እኔም እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘አምላካችን ይሖዋ ወደሚሰጠን ወደ አሞራውያን ተራራማ አካባቢዎች ደርሳችኋል። 21 ይኸው አምላካችሁ ይሖዋ ምድሪቱን ለእናንተ ሰጥቷችኋል። የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ በነገራችሁ መሠረት ተነሱና ውረሷት።+ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።’
22 “ሆኖም እናንተ ሁላችሁም ወደ እኔ መጥታችሁ እንዲህ አላችሁኝ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልን እንዲሁም በየትኛው መንገድ መሄድ እንደሚኖርብንና ምን ዓይነት ከተሞች እንደሚያጋጥሙን አይተው እንዲነግሩን ሰዎችን አስቀድመን እንላክ።’+ 23 ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ በመሆኑም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ይኸውም ከመካከላችሁ 12 ሰዎችን መረጥኩ።+ 24 እነሱም ተነስተው ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዱ፤+ እስከ ኤሽኮል ሸለቆ* ድረስ በመዝለቅም ምድሪቱን ሰለሉ። 25 ምድሪቱ ከምታፈራው ፍሬም የተወሰነ ይዘው ወደ እኛ መጡ፤ እንዲሁም ‘አምላካችን ይሖዋ የሚሰጠን ምድር መልካም ናት’ ብለው ነገሩን።+ 26 እናንተ ግን ወደዚያ ለመውጣት ፈቃደኞች አልሆናችሁም፤ በአምላካችሁ በይሖዋ ትእዛዝም ላይ ዓመፃችሁ።+ 27 በየድንኳኖቻችሁ ውስጥ ሆናችሁ እንዲህ በማለት አጉተመተማችሁ፦ ‘ይሖዋ ስለጠላን አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነሱ አሳልፎ ሊሰጠን ከግብፅ ምድር አወጣን። 28 ታዲያ የምንሄደው ወዴት ነው? ወንድሞቻችን “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱና ረጃጅሞች ናቸው፤ ከተሞቻቸውም ቢሆኑ ታላላቅና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤+ እንዲያውም በዚያ የኤናቅን+ ልጆች አይተናል” በማለት ልባችን እንዲቀልጥ አድርገዋል።’+
29 “በመሆኑም እኔ እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘በእነሱ የተነሳ በፍርሃት አትራዱ ወይም አትሸበሩ።+ 30 አምላካችሁ ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የገዛ ዓይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ይዋጋላችኋል።+ 31 በምድረ በዳም ተጉዛችሁ እዚህ እስክትደርሱ ድረስ አንድ አባት ልጁን እንደሚሸከም አምላካችሁ ይሖዋም በሄዳችሁበት ሁሉ እንዴት እንደተሸከማችሁ አይታችኋል።’ 32 እናንተ ግን ይህ ሁሉ ተደርጎላችሁም በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ እምነት አላሳደራችሁም፤+ 33 እሱ የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግ ከፊት ከፊታችሁ ይሄድ ነበር። በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ ለማሳየትም ሌሊት ሌሊት በእሳት፣ ቀን ቀን ደግሞ በደመና ይመራችሁ ነበር።+
34 “በዚህ ጊዜ ይሖዋ ያላችሁትን ሰማ፤ ተቆጥቶም እንዲህ ሲል ማለ፦+ 35 ‘ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የማልኩላቸውን መልካሚቱን ምድር ከዚህ ክፉ ትውልድ መካከል አንድም ሰው አያያትም፤+ 36 ከየፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር ማንም አያያትም። እሱ ያያታል፤ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ስለተከተለም የረገጣትን ምድር ለእሱና ለልጆቹ እሰጣታለሁ።+ 37 (ይሖዋ በእናንተ የተነሳ በእኔም ላይ እንኳ ተቆጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “አንተም ብትሆን ወደዚያ አትገባም።+ 38 ወደ ምድሪቱ የሚገባው+ በፊትህ የሚቆመው የነዌ ልጅ ኢያሱ ነው።+ እስራኤላውያን ምድሪቱን እንዲወርሱ የሚያደርገው እሱ ስለሆነ አበርታው።”)*+ 39 በተጨማሪም ለምርኮ ይዳረጋሉ+ ያላችኋቸው ልጆቻችሁ እንዲሁም ዛሬ ክፉና ደጉን የማያውቁት ወንዶች ልጆቻችሁ ወደዚያ ይገባሉ፤ እኔም ምድሪቱን እንዲወርሷት ለእነሱ እሰጣታለሁ።+ 40 እናንተ ግን አቅጣጫ በመቀየር ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ አድርጋችሁ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።’+
41 “እናንተም በዚህ ጊዜ እንዲህ አላችሁኝ፦ ‘በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል። በቃ፣ አምላካችን ይሖዋ ባዘዘን መሠረት ወጥተን እንዋጋለን!’ በመሆኑም እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያዎቻችሁን ታጠቃችሁ፤ ወደ ተራራው መውጣት ቀላል መስሎ ታይቷችሁ ነበር።+ 42 ይሁንና ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘እንዲህ በላቸው፦ “እኔ አብሬያችሁ ስለማልሆን ወጥታችሁ ውጊያ እንዳትገጥሙ።+ እንዲህ ብታደርጉ ግን ጠላቶቻችሁ ድል ያደርጓችኋል።”’ 43 እኔም ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ትእዛዝ ላይ በማመፅ በእብሪት ወደ ተራራው ለመውጣት ሞከራችሁ። 44 ከዚያም በተራራው ላይ ይኖሩ የነበሩት አሞራውያን እናንተን ለመግጠም ወጡ፤ እነሱም ልክ እንደ ንብ እየተከታተሉ አሳደዷችሁ፤ ከሴይር አንስቶ እስከ ሆርማ ድረስም በታተኗችሁ። 45 ስለሆነም ተመልሳችሁ በይሖዋ ፊት ማልቀስ ጀመራችሁ፤ ሆኖም ይሖዋ ጩኸታችሁን አልሰማም፤ ጆሮውንም አልሰጣችሁም። 46 እነዚያን ሁሉ ቀናት በቃዴስ የተቀመጣችሁትም ለዚህ ነው።