ዘኁልቁ
14 ከዚያም ማኅበረሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ ሕዝቡም ሌሊቱን ሙሉ ሲጮኽና ሲያለቅስ አደረ።+ 2 እስራኤላውያንም በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ ያጉረመርሙ ጀመር፤+ መላው ማኅበረሰብ እንዲህ አላቸው፦ “ምነው በግብፅ ምድር ሳለን ሞተን ባረፍነው፤ ወይም ምናለ በዚህ ምድረ በዳ በሞትን! 3 ይሖዋ በሰይፍ እንድንሞት ወደዚህ ምድር ያመጣን ለምንድን ነው?+ እንግዲህ ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ይማረካሉ።+ ታዲያ ወደ ግብፅ ብንመለስ አይሻለንም?”+ 4 እንዲያውም እርስ በርሳቸው “መሪ እንሹምና ወደ ግብፅ እንመለስ” ይባባሉ ጀመር።+
5 በዚህ ጊዜ ሙሴና አሮን በተሰበሰበው በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 6 ምድሩን ከሰለሉት ሰዎች መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና+ የየፎኒ ልጅ ካሌብ+ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7 ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብም እንዲህ አሉ፦ “ተዘዋውረን የሰለልናት ምድር እጅግ በጣም ጥሩ ምድር ናት።+ 8 ይሖዋ በእኛ ከተደሰተ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚህች ምድር+ በእርግጥ ያስገባናል፤ ደግሞም ይህችን ምድር ይሰጠናል። 9 ብቻ እናንተ በይሖዋ ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ስለምንጎርሳቸው የምድሪቱን ሕዝቦች አትፍሯቸው።+ ጥላቸው ተገፏል፤ ደግሞም ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው።+ ፈጽሞ አትፍሯቸው።”
10 ይሁን እንጂ መላው ማኅበረሰብ በድንጋይ ሊወግራቸው ተማከረ።+ ሆኖም የይሖዋ ክብር በመገናኛ ድንኳኑ ላይ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ተገለጠ።+
11 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ የሚንቀኝ እስከ መቼ ነው?+ በመካከላቸው ይህን ሁሉ ተአምራዊ ምልክት እያሳየሁ የማያምኑብኝስ እስከ መቼ ነው?+ 12 እንግዲህ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ ደግሞም እደመስሳቸዋለሁ፤ አንተን ግን ከእነሱ ይልቅ ታላቅና ኃያል ብሔር አደርግሃለሁ።”+
13 ሙሴ ግን ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንዲህ ካደረግክ ይህን ሕዝብ በኃይልህ ከመካከላቸው ስታወጣ ያዩ ግብፃውያን መስማታቸው አይቀርም፤+ 14 እነሱ ደግሞ የሰሙትን ነገር ለዚህ ምድር ነዋሪዎች ይናገራሉ። እነሱም ቢሆኑ አንተ ይሖዋ በዚህ ሕዝብ መካከል እንዳለህና+ ፊት ለፊት+ እንደተገለጥክላቸው ሰምተዋል። አንተ ይሖዋ ነህ፤ ደመናህም በላያቸው ላይ ቆሟል፤ ቀን ቀን በደመና ዓምድ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ከፊት ከፊታቸው ትሄዳለህ።+ 15 እንግዲህ ይህን ሕዝብ በሙሉ በአንዴ ብትፈጀው* የአንተን ዝና የሰሙ ብሔራት እንዲህ ማለታቸው አይቀርም፦ 16 ‘ይሖዋ ይህን ሕዝብ፣ ሊሰጠው ወደማለለት ምድር ሊያስገባው ስላልቻለ በምድረ በዳ ፈጀው።’+ 17 አሁንም እባክህ ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል በገባኸው መሠረት ኃይልህ ታላቅ ይሁን፦ 18 ‘ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩ* የበዛ፣+ ስህተትንና መተላለፍን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ ነው።’+ 19 ይህን ሕዝብ ከግብፅ አንስቶ እስካሁን ድረስ ይቅር ስትለው እንደቆየህ ሁሉ አሁንም እባክህ፣ የዚህን ሕዝብ ስህተት ታላቅ በሆነው ታማኝ ፍቅርህ ይቅር በል።”+
20 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “ባልከኝ መሠረት ይቅር እላቸዋለሁ።+ 21 በሌላ በኩል ግን በሕያውነቴ እምላለሁ፣ መላዋ ምድር በይሖዋ ክብር ትሞላለች።+ 22 ይሁን እንጂ ክብሬንና በግብፅም ሆነ በምድረ በዳ የፈጸምኳቸውን ተአምራዊ ምልክቶች+ የተመለከቱት ሆኖም አሥር ጊዜ የተፈታተኑኝና+ ቃሌን ያልሰሙት+ ሰዎች አንዳቸውም ቢሆኑ 23 ለአባቶቻቸው የማልኩላቸውን ምድር ፈጽሞ አያዩም። አዎ፣ የናቁኝ ሰዎች አንዳቸውም ቢሆኑ ያን ምድር አያዩም።+ 24 አገልጋዬ ካሌብ+ ግን የተለየ መንፈስ እንዳለው ስላሳየና በሙሉ ልቡ ስለተከተለኝ ሄዶባት ወደነበረው ምድር በእርግጥ አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ያቺን ምድር ይወርሳሉ።+ 25 አማሌቃውያንና ከነአናውያን+ በሸለቆው ውስጥ* ስለሚኖሩ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”+
26 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 27 “ይህ ክፉ ማኅበረሰብ በእኔ ላይ እንዲህ የሚያጉረመርመው እስከ መቼ ነው?+ እስራኤላውያን በእኔ ላይ የሚያጉረመርሙትን ሰምቻለሁ።+ 28 እንዲህ በሏቸው፦ ‘“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ይሖዋ፤ “እናንተው ራሳችሁ ስትናገሩ የሰማሁትን ነገር አደርግባችኋለሁ!+ 29 ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗችሁ የተመዘገባችሁትና የተቆጠራችሁት ሁሉ አዎ፣ በእኔ ላይ ያጉረመረማችሁት+ ሁሉ ሬሳችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል።+ 30 ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር+ አንዳችሁም ብትሆኑ በዚያ እንደማኖራችሁ ወደማልኩላችሁ* ምድር አትገቡም።+
31 “‘“ለምርኮ ይዳረጋሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን+ ግን አስገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትንም ምድር+ በሚገባ ያውቋታል። 32 የእናንተ ሬሳ ግን በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። 33 እንግዲህ ልጆቻችሁ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት እረኞች ይሆናሉ፤+ እነሱም የእናንተ የመጨረሻው ሬሳ በምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ+ እናንተ ለፈጸማችሁት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት* መልስ ይሰጣሉ። 34 እኔን መቃወም* ምን ማለት እንደሆነ እንድታውቁ ምድሪቱን በሰለላችሁባቸው 40 ቀናት+ ልክ ይኸውም አንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት ተቆጥሮ፣ ለሠራችኋቸው ስህተቶች ለ40 ዓመት+ መልስ ትሰጣላችሁ።
35 “‘“እኔ ይሖዋ ተናግሬአለሁ። በእኔ ላይ ተባብሮ በተነሳው በዚህ ክፉ ማኅበረሰብ ላይ በእርግጥ ይህን አደርጋለሁ፦ መጨረሻቸው በዚህ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።+ 36 ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸውና ስለ ምድሪቱ መጥፎ ወሬ ይዘው በመምጣት መላው ማኅበረሰብ በእሱ ላይ እንዲያጉረመርም ያደረጉት ሰዎች+ 37 አዎ፣ ስለ ምድሪቱ መጥፎ ወሬ ይዘው የመጡት ሰዎች በይሖዋ ፊት ተቀስፈው ይሞታሉ።+ 38 ምድሪቱን ለመሰለል ከሄዱት ሰዎች መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የየፎኒ ልጅ ካሌብ ግን በሕይወት ይኖራሉ።”’”+
39 ሙሴም ለእስራኤላውያን በሙሉ ይህን ሲነግራቸው ሕዝቡ እጅግ አዘነ። 40 ከዚያም በጠዋት ወደ ተራራው አናት ለመውጣት ተነሱ፤ እነሱም “ኃጢአት ስለሠራን ይሖዋ ወደተናገረለት ቦታ ለመውጣት ይኸው ዝግጁ ነን” አሉ።+ 41 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፦ “የይሖዋን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው? ይህ አይሳካላችሁም። 42 ይሖዋ ከእናንተ ጋር ስላልሆነ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትመታላችሁ።+ 43 ምክንያቱም አማሌቃውያንና ከነአናውያን በዚያ ይገጥሟችኋል፤+ እናንተም በሰይፍ ትወድቃላችሁ። ምክንያቱም ይሖዋን ከመከተል ዞር ስላላችሁ ይሖዋ ከእናንተ ጋር አይሆንም።”+
44 እነሱ ግን በትዕቢት ወደ ተራራው አናት ወጡ፤+ ሆኖም የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ መካከል ንቅንቅ አላሉም።+ 45 ከዚያም በዚያ ተራራ የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነአናውያን ወርደው መቷቸው፤ እስከ ሆርማም ድረስ በታተኗቸው።+