ሁለተኛ ሳሙኤል
3 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የሚደረገው ውጊያ ለረጅም ጊዜ ዘለቀ፤ ዳዊት እየበረታ+ ሲሄድ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ+ መጣ።
2 በዚህ መሃል ዳዊት በኬብሮን ወንዶች ልጆች ተወለዱለት።+ የበኩር ልጁ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ የወለደው አምኖን+ ነበር። 3 ሁለተኛው ልጁ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል+ የወለደው ኪልአብ ሲሆን ሦስተኛው ልጁ ደግሞ የገሹር ንጉሥ የታልማይ+ ልጅ የሆነችው የማአካ ልጅ አቢሴሎም+ ነበር። 4 አራተኛው ልጁ የሃጊት ልጅ አዶንያስ፣+ አምስተኛው ልጁ ደግሞ የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያህ ነበር። 5 ስድስተኛው ልጁ ኤግላ ከተባለችው ሚስቱ የወለደው ይትረአም ነበር። እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።
6 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የነበረው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት አበኔር+ በሳኦል ቤት ውስጥ የነበረውን ቦታ እያጠናከረ ሄደ። 7 ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ+ የተባለች ቁባት ነበረችው። በኋላም ኢያቡስቴ+ አበኔርን “ከአባቴ ቁባት ጋር ግንኙነት የፈጸምከው ለምንድን ነው?” አለው።+ 8 አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ተቆጥቶ እንዲህ አለ፦ “እኔ ከይሁዳ ወገን የሆንኩ የውሻ ጭንቅላት ነኝ? እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፣ ለወንድሞቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላልኩም፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ይኸው አንተ ግን ዛሬ በአንዲት ሴት የተነሳ ጥፋተኛ አድርገህ ትከሰኛለህ። 9 ይሖዋ ለዳዊት እንደማለለት+ ሳላደርግለት ብቀር አምላክ በአበኔር ላይ ይህን ያድርግበት፤ ከዚህ የከፋም ያምጣበት፤ 10 አምላክ መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ እንዲሁም የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ እንደሚያጸና ምሏል።” 11 ኢያቡስቴም አበኔርን ስለፈራው አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።+
12 አበኔርም ወዲያውኑ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን ልኮ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን ግባ፤ መላው እስራኤል ከአንተ ጎን እንዲቆም የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ”* አለው።+ 13 እሱም እንዲህ አለው፦ “መልካም! ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ። ብቻ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እጠይቅሃለሁ፤ ወደ እኔ ስትመጣ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን+ ይዘህ ካልመጣህ በቀር ፊቴን እንደማታይ እወቅ” አለው። 14 ከዚያም ዳዊት ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ+ “በ100 የፍልስጤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ላከ።+ 15 በመሆኑም ኢያቡስቴ መልእክተኛ ልኮ ሜልኮልን የላይሽ ልጅ ከሆነው ከባሏ ከፓልጢኤል+ ወሰዳት። 16 ባሏ ግን እስከ ባሁሪም+ ድረስ እያለቀሰ ተከትሏት ሄደ። ከዚያም አበኔር “በቃ ሂድ፣ ተመለስ!” አለው። እሱም ተመለሰ።
17 ይህ በእንዲህ እንዳለ አበኔር ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “ቀድሞውንም ቢሆን ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ትፈልጉ ነበር። 18 ይሖዋ ዳዊትን ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጤማውያንና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ የምታደገው በአገልጋዬ በዳዊት እጅ ነው’+ ስላለው በሉ አሁን እርምጃ ውሰዱ።” 19 ከዚያም አበኔር ቢንያማውያንን+ አነጋገራቸው። በተጨማሪም አበኔር እስራኤልና መላው የቢንያም ቤት ለማድረግ የተስማሙትን ነገር በኬብሮን ላለው ለዳዊት በግል ሊነግረው ወደ እሱ ሄደ።
20 አበኔር ከ20 ሰዎች ጋር ሆኖ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት ሲመጣ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21 ከዚያም አበኔር ዳዊትን “እስራኤላውያን ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ ተነስቼ ልሂድና ሁሉንም ወደ ጌታዬ ወደ ንጉሡ ልሰብስባቸው፤ አንተም በፈለግከው* ሁሉ ላይ ንጉሥ ትሆናለህ” አለው። በመሆኑም ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ።
22 በዚህ ጊዜ የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮዓብ በጣም ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ በኬብሮን ከእሱ ጋር አልነበረም። 23 ኢዮዓብና+ አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ ሲደርስ “የኔር+ ልጅ አበኔር+ ወደ ንጉሡ መጥቶ ነበር፤ ንጉሡም አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮዓብ ነገሩት። 24 በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለው፦ “ምን ማድረግህ ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ነበር። ታዲያ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትከው ለምንድን ነው? 25 የኔርን ልጅ አበኔርን በሚገባ ታውቀዋለህ! ወደዚህ የመጣው አንተን ለማታለል እንዲሁም መውጫ መግቢያህን ለማወቅና የምታደርገውን ነገር ሁሉ ለመሰለል ነው።”
26 በመሆኑም ኢዮዓብ ከዳዊት ዘንድ ወጥቶ መልእክተኞችን ወደ አበኔር ላከ፤ እነሱም ሲራ ከተባለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ጋ መለሱት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። 27 አበኔር ወደ ኬብሮን+ በተመለሰ ጊዜ ኢዮዓብ ከእሱ ጋር በግል ለመነጋገር ነጠል አድርጎ ወደ ቅጥሩ በር ይዞት ገባ። ሆኖም በዚያ ሳሉ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው፤+ ይህን ያደረገው የወንድሙን የአሳሄልን ደም ለመበቀል ነው።+ 28 ዳዊትም ይህን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “እኔም ሆንኩ መንግሥቴ በኔር ልጅ በአበኔር ደም በይሖዋ ፊት ለዘላለም ተጠያቂ አይደለንም።+ 29 ደሙ በኢዮዓብ ራስና በመላው የአባቱ ቤት ራስ ላይ ይሁን።+ ከኢዮዓብም ቤት ፈሳሽ የሚወጣው+ ሰው ወይም የሥጋ ደዌ+ ያለበት አሊያም እንዝርት የሚያሾር ወንድ* ወይም በሰይፍ የሚወድቅ አሊያም የሚበላው ያጣ ረሃብተኛ አይጥፋ!”+ 30 በመሆኑም ኢዮዓብና ወንድሙ አቢሳ+ በገባኦን በተደረገው ውጊያ ላይ ወንድማቸውን አሳሄልን ስለገደለባቸው+ አበኔርን+ ገደሉት።
31 ከዚያም ዳዊት ኢዮዓብንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች በሙሉ “ልብሳችሁን ቀድዳችሁና ማቅ አሸርጣችሁ ለአበኔር አልቅሱለት” አላቸው። ንጉሥ ዳዊትም ራሱ ከቃሬዛው ኋላ ይሄድ ነበር። 32 አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሰ። 33 ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፦
“አበኔርም እንደማይረባ ሰው ይሙት?
34 እጆችህ አልታሰሩም፤
እግሮችህም እግር ብረት* ውስጥ አልገቡም።
በወንጀለኞች* ፊት እንደሚወድቅ ሰው ወደቅክ።”+
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ለእሱ እንደገና አለቀሱ።
35 በኋላም ሕዝቡ ሁሉ ገና ቀን ሳለ፣ ዳዊትን ለማጽናናት ምግብ* ይዞ መጣ፤ ሆኖም ዳዊት “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ምግብ ወይም ማንኛውንም ነገር ብቀምስ አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ!” በማለት ማለ።+ 36 ሕዝቡም ሁሉ የሆነውን ነገር ተመለከተ፤ ይህም ደስ አሰኛቸው። ንጉሡ ያደረገው ማንኛውም ነገር እንዳስደሰታቸው ሁሉ ይህም ደስ አሰኛቸው። 37 በመሆኑም ሰዎቹ ሁሉና መላው እስራኤል ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንደሌለበት በዚያ ቀን አወቁ።+ 38 ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “በዛሬው ዕለት በእስራኤል ውስጥ አለቃና ታላቅ ሰው እንደወደቀ አታውቁም?+ 39 ምንም እንኳ ንጉሥ ሆኜ የተቀባሁ+ ብሆንም እኔ ዛሬ ደካማ ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ+ ልጆች እጅግ ጨካኝ ሆነውብኛል።+ ይሖዋ ለክፉ አድራጊው እንደ ክፋቱ ይመልስለት።”+