አንደኛ ዜና መዋዕል
22 ከዚያም ዳዊት “የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ቤት በዚህ ይሆናል፤ ለእስራኤል የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያም በዚሁ ይቆማል” አለ።+
2 ዳዊት በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን የባዕድ አገር ሰዎች+ እንዲሰበስቡ አዘዘ፤ የእውነተኛውን አምላክ ቤት ለመገንባት የሚያስፈልጉትንም ድንጋዮች እንዲጠርቡ ድንጋይ ጠራቢዎች አድርጎ መደባቸው።+ 3 በተጨማሪም ዳዊት ለመግቢያዎቹ በሮች የሚያስፈልጉ ምስማሮችንና ማጠፊያዎችን ለመሥራት የሚያገለግል ከፍተኛ መጠን ያለው ብረት አዘጋጀ፤ ደግሞም ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የማይችል መዳብ አከማቸ፤+ 4 ከዚህም ሌላ ስፍር ቁጥር የሌለው ከአርዘ ሊባኖስ የተሠራ ሳንቃ+ አዘጋጀ፤ ሲዶናውያንና+ ጢሮሳውያን+ ከአርዘ ሊባኖስ የተዘጋጀ ብዛት ያለው ሳንቃ ለዳዊት አምጥተውለት ነበርና። 5 ዳዊትም እንዲህ አለ፦ “ልጄ ሰለሞን ገና ወጣት ነው፤ ተሞክሮም የለውም፤*+ ለይሖዋ የሚሠራው ቤት ደግሞ እጅግ የሚያምር+ ከመሆኑ የተነሳ ዝናውም ሆነ ውበቱ+ በመላው ምድር የታወቀ ይሆናል።+ ስለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር አዘጋጅለታለሁ።” በመሆኑም ዳዊት ከመሞቱ በፊት ለሥራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች በብዛት አዘጋጀ።
6 በተጨማሪም ልጁን ሰለሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ፣ ቤት እንዲሠራ አዘዘው። 7 ዳዊት ልጁን ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “እኔ በበኩሌ ለአምላኬ ለይሖዋ ስም፣ ቤት ለመሥራት ከልብ ተመኝቼ ነበር።+ 8 ሆኖም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ ‘አንተ እጅግ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ታላላቅ ጦርነቶችንም አድርገሃል። በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም ስላፈሰስክ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራልኝም።+ 9 እነሆ፣ የሰላም* ሰው የሚሆን ወንድ ልጅ ትወልዳለህ፤+ በዙሪያውም ካሉት ጠላቶቹ በሙሉ እረፍት እሰጠዋለሁ፤+ ስሙ ሰለሞን*+ ይባላልና፤ በእሱም ዘመን ለእስራኤል ሰላምና ጸጥታ እሰጣለሁ።+ 10 ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው።+ እሱ ልጄ ይሆናል፤ እኔም አባቱ እሆናለሁ።+ የንግሥናውን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።’+
11 “አሁንም ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም በተናገረው መሠረት ተሳክቶልህ የአምላክህን የይሖዋን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።+ 12 ብቻ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ሲሾምህ የአምላክህን የይሖዋን ሕግ እንድትጠብቅ+ የማመዛዘንና የማስተዋል ችሎታ ይስጥህ።+ 13 ደግሞም ይሖዋ እስራኤልን በተመለከተ ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና+ ድንጋጌ በጥንቃቄ ብትጠብቅ ይሳካልሃል።+ ደፋርና ብርቱ ሁን። አትፍራ ወይም አትሸበር።+ 14 እነሆ፣ እኔ ለይሖዋ ቤት 100,000 ታላንት* ወርቅና 1,000,000 ታላንት ብር እንዲሁም ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የማይችል መዳብና ብረት+ ለማዘጋጀት ብዙ ደክሜአለሁ፤ ደግሞም ሳንቃና ድንጋይ አዘጋጅቻለሁ፤+ አንተም በዚያ ላይ ትጨምርበታለህ። 15 ከአንተም ጋር ብዙ ሠራተኞች፣ ድንጋይ ጠራቢዎች፣ ግንበኞች፣+ አናጺዎችና በተለያዩ ሙያዎች የተካኑ ሠራተኞች አሉ።+ 16 ወርቁ፣ ብሩ፣ መዳቡና ብረቱ ስፍር ቁጥር የለውም።+ በል ሥራውን ጀምር፤ ይሖዋም ከአንተ ጋር ይሁን።”+
17 ከዚያም ዳዊት የእስራኤል መኳንንት ሁሉ ልጁን ሰለሞንን እንዲረዱት እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 18 “አምላካችሁ ይሖዋ ከእናንተ ጋር አይደለም? በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉስ እረፍት አልሰጣችሁም? የምድሪቱን ነዋሪዎች በእጄ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና፤ ምድሪቱም በይሖዋና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለች። 19 አሁንም በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* አምላካችሁን ይሖዋን ጠይቁ፤+ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦትና የእውነተኛውን አምላክ የተቀደሱ ዕቃዎች+ ለይሖዋ ስም+ ወደሚሠራው ቤት እንድታመጡ የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን መቅደስ መሥራት ጀምሩ።”+