ዘፍጥረት
12 ይሖዋም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።+ 2 አንተን ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፤ አንተም በረከት ትሆናለህ።+ 3 የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግምህንም እረግማለሁ፤+ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ።”*+
4 ስለዚህ አብራም ልክ ይሖዋ በነገረው መሠረት ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን በወጣበት ጊዜ ዕድሜው 75 ዓመት ነበር።+ 5 አብራም ሚስቱን ሦራን፣+ የወንድሙን ልጅ ሎጥን+ እንዲሁም ያፈሩትን ንብረት ሁሉና+ በካራን አብረዋቸው የነበሩትን ሰዎች* በሙሉ ይዞ ተነሳ፤ እነሱም ወደ ከነአን ምድር አቀኑ።+ ከነአን ምድር በደረሱም ጊዜ 6 አብራም በሞሬ ትላልቅ ዛፎች+ አቅራቢያ እስከሚገኘው ሴኬም+ እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ወደ ምድሪቱ ዘልቆ ገባ። በዚያን ጊዜ ከነአናውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር። 7 ይሖዋም ለአብራም ተገለጠለትና “ይህችን ምድር ለዘርህ+ እሰጣለሁ”+ አለው። ስለዚህ አብራም ተገልጦለት ለነበረው ለይሖዋ በዚያ መሠዊያ ሠራ። 8 በኋላም ከዚያ ተነስቶ ከቤቴል+ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ ተጓዘ፤ እሱም ቤቴልን በስተ ምዕራብ፣ ጋይን+ ደግሞ በስተ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤+ የይሖዋንም ስም ጠራ።+ 9 ከዚያ በኋላ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በየቦታው እየሰፈረ ወደ ኔጌብ+ ተጓዘ።
10 በምድሪቱም ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ በጣም አስከፊ ስለነበር+ አብራም ለተወሰነ ጊዜ* በግብፅ ለመኖር ወደዚያ ወረደ።+ 11 ወደ ግብፅ ለመግባት ሲቃረብም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ ስሚኝ፤ አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ።+ 12 ስለሆነም ግብፃውያን አንቺን ሲያዩ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ማለታቸው አይቀርም። ከዚያም እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13 በአንቺ የተነሳ መልካም እንዲሆንልኝ እባክሽ፣ እህቴ እንደሆንሽ አድርገሽ ተናገሪ፤ እንዲህ ካደረግሽ ሕይወቴ ይተርፋል።”*+
14 አብራምም ግብፅ እንደደረሰ ግብፃውያኑ ሴቲቱ እጅግ ውብ እንደሆነች ተመለከቱ። 15 የፈርዖንም መኳንንት ሴቲቱን አዩአት፤ ስለ እሷም ለፈርዖን በአድናቆት ነገሩት። በመሆኑም ሴቲቱ ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። 16 ፈርዖንም በእሷ ምክንያት አብራምን ተንከባከበው፤ በጎችን፣ ከብቶችን፣ ተባዕትና እንስት አህዮችን፣ ግመሎችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ሰጠው።+ 17 ከዚያም ይሖዋ በአብራም ሚስት በሦራ+ የተነሳ ፈርዖንንና ቤተሰቡን በታላቅ መቅሰፍት መታ። 18 በመሆኑም ፈርዖን አብራምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ሚስትህ እንደሆነች ያልነገርከኝ ለምንድን ነው? 19 ‘እህቴ ናት’+ ያልከውስ ለምንድን ነው? እኔ እኮ ወስጄ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል፣ ሚስትህ ይችውልህ፤ ይዘሃት ሂድ!” 20 ስለዚህ ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።+