ኤርምያስ
21 ንጉሥ ሴዴቅያስ+ የማልኪያህን ልጅ ጳስኮርንና+ የማአሴያህን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን+ ወደ ኤርምያስ በላካቸው ጊዜ የይሖዋ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤ እነሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ 2 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ሊወጋን ስለሆነ+ እባክህ፣ ስለ እኛ ይሖዋን ጠይቅልን። ንጉሡ ከእኛ እንዲመለስ ይሖዋ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም ተአምር ይፈጽምልን ይሆናል።”+
3 ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፦ “ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ 4 ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎንን ንጉሥና ከቅጥሩ ውጭ የከበቧችሁን ከለዳውያንን ለመውጋት የምትጠቀሙባቸውን በገዛ እጃችሁ ላይ ያሉትን የጦር መሣሪያዎች በእናንተው ላይ አዞራለሁ።+ በዚህችም ከተማ መሃል እሰበስባቸዋለሁ። 5 እኔ ራሴ በተዘረጋች እጅና በኃያል ክንድ እንዲሁም በመዓትና በታላቅ ቁጣ እዋጋችኋለሁ።+ 6 የዚህችን ከተማ ነዋሪዎች፣ ሰውንም ሆነ እንስሳን እመታለሁ። እነሱም በታላቅ ቸነፈር* ይሞታሉ።”’+
7 “‘“ከዚያም በኋላ” ይላል ይሖዋ፣ “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፣ አገልጋዮቹን እንዲሁም ከቸነፈር፣ ከሰይፍና ከረሃብ ተርፎ በከተማዋ ውስጥ የሚቀረውን ሕዝብ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር* እጅ፣ በጠላቶቻቸው እጅና ሕይወታቸውን ለማጥፋት በሚሹ* ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።+ እሱም በሰይፍ ይመታቸዋል። አያዝንላቸውም፤ ርኅራኄም ሆነ ምሕረት አያሳያቸውም።”’+
8 “ደግሞም ይህን ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አድርጌአለሁ። 9 በዚህች ከተማ የሚቀሩ ሰዎች በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር ይሞታሉ። ይሁንና ከከተማዋ ወጥቶ፣ ለከበቧችሁ ከለዳውያን እጁን የሚሰጥ በሕይወት ይኖራል፤ ሕይወቱም* እንደ ምርኮ ትሆንለታለች።”’*+
10 “‘“መልካም ነገር ሳይሆን ጥፋት ለማምጣት ፊቴን ወደዚህች ከተማ አዙሬአለሁና”+ ይላል ይሖዋ። “ለባቢሎን ንጉሥ ትሰጣለች፤+ እሱም በእሳት ያቃጥላታል።”+
11 “‘የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ፦ የይሖዋን ቃል ስሙ። 12 የዳዊት ቤት ሆይ፣ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“ከክፉ ድርጊታችሁ የተነሳ
ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይቀጣጠልና+
ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል ድረስ እንዳይነድ
በየማለዳው ለፍትሕ ቁሙ፤
የተዘረፈውንም ሰው ከአጭበርባሪው እጅ ታደጉ።”’+
13 ‘አንቺ በሸለቆ ውስጥ* የምትኖሪ፣ በደልዳላው መሬት ላይ የተቀመጥሽ ዓለት ሆይ፣
እነሆ፣ እኔ በአንቺ ላይ እነሳለሁ’ ይላል ይሖዋ።
‘“በእኛ ላይ ማን ይወርዳል? ደግሞስ መኖሪያዎቻችንን ማን ይወራል?”
የምትሉ ይህን እወቁ፤
14 እንደ ሥራችሁ መጠን
ተጠያቂ አደርጋችኋለሁ’+ ይላል ይሖዋ።
‘ጫካዋን በእሳት አነዳለሁ፤
እሳቱም በዙሪያዋ ያለውን ነገር ሁሉ ይበላል።’”+