ሁለተኛ ዜና መዋዕል
32 እነዚህ ነገሮች ከተከናወኑና ሕዝቅያስ በታማኝነት ሲመላለስ+ ከቆየ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ቅጥራቸውን አፍርሶ ለመያዝ ስላሰበ የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።+
2 ሕዝቅያስ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመውጋት አስቦ እንደመጣ ባየ ጊዜ፣ 3 ከመኳንንቱና ከተዋጊዎቹ ጋር ተማክሮ ከከተማዋ ውጭ ያሉትን የውኃ ምንጮች ለመድፈን ወሰነ፤+ እነሱም ረዱት። 4 ብዙ ሰዎች ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ለምን ብዙ ውኃ ያግኙ?” በማለት ምንጮቹንና በምድሪቱ መካከል የሚፈሰውን ጅረት በሙሉ ደፈኑ።
5 በተጨማሪም ሕዝቅያስ በትጋት በመሥራት የፈረሰውን ቅጥር በሙሉ ገነባ፤ በላዩም ላይ ማማዎችን ሠራ፤ ከውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር ገነባ። ደግሞም የዳዊትን ከተማ ጉብታ*+ ጠገነ፤ እንዲሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችና* ጋሻዎች ሠራ። 6 ከዚያም በሕዝቡ ላይ የጦር አለቆችን ሾሞ በከተማዋ በር በሚገኘው አደባባይ ሰበሰባቸው፤ እንዲህም በማለት አበረታታቸው፦* 7 “ደፋርና ብርቱዎች ሁኑ። ከአሦር ንጉሥና ከእሱ ጋር ካለው ብዙ ሠራዊት የተነሳ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ፤+ ከእሱ ጋር ካሉት ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ።+ 8 ከእሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ* ሲሆን ከእኛ ጋር ያለው ግን አምላካችን ይሖዋ ነው፤ እሱ ይረዳናል፤ ደግሞም ይዋጋልናል።”+ ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።+
9 ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ* ጋር በለኪሶ+ ሳለ አገልጋዮቹን ወደ ኢየሩሳሌም ይኸውም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደሚኖሩት አይሁዳውያን+ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦
10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ ‘ኢየሩሳሌም ተከባ ሳለ ከከተማዋ ሳትወጡ የቀራችሁት በምን ተማምናችሁ ነው?+ 11 ሕዝቅያስ “አምላካችን ይሖዋ ከአሦር ንጉሥ እጅ ይታደገናል” እያለ እናንተን በማታለል በረሃብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ሊሰጣችሁ አይደለም?+ 12 የአምላካችሁን* ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና+ መሠዊያዎች+ ካስወገደ በኋላ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን “በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በዚያም ላይ የሚጨስ መሥዋዕት አቅርቡ” ያለው ሕዝቅያስ ራሱ አይደለም?+ 13 እኔም ሆንኩ አባቶቼ በተለያዩ አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁም?+ የእነዚህ አገሮች ሕዝቦች አማልክት ምድራቸውን ከእጄ መታደግ ችለዋል?+ 14 አባቶቼ ፈጽመው ካጠፏቸው ከእነዚህ ብሔራት አማልክት ሁሉ መካከል ሕዝቡን ከእጄ መታደግ የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ የእናንተስ አምላክ ቢሆን ከእጄ ሊታደጋችሁ ይችላል?+ 15 አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ መንገድ አያታላችሁ ወይም አያሳስታችሁ!+ አትመኑት፤ የየትኛውም ብሔርም ሆነ መንግሥት አምላክ ከእኔና ከአባቶቼ እጅ ሕዝቡን መታደግ አልቻለም። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ይታደጋችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!’”+
16 የሰናክሬም አገልጋዮች በእውነተኛው አምላክ በይሖዋና በአገልጋዩ በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17 በተጨማሪም ንጉሡ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለመስደብና+ እሱን ለማቃለል እንዲህ ሲል ደብዳቤ ጻፈ፦+ “የሌሎች ብሔራት አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ መታደግ እንዳልቻሉ ሁሉ+ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም።” 18 በቅጥሩ ላይ ያሉትን የኢየሩሳሌም ሰዎች በማስፈራራትና በማሸበር ከተማዋን ለመያዝ ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአይሁዳውያን ቋንቋ ለሰዎቹ መናገራቸውን ቀጠሉ።+ 19 የሰው እጅ ሥራ በሆኑት በሌሎች የምድር ሕዝቦች አማልክት ላይ እንደተናገሩ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ። 20 ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ ግን ይህን ጉዳይ በተመለከተ አጥብቀው ጸለዩ፤ እርዳታ ለማግኘትም ወደ ሰማይ ጮኹ።+
21 ከዚያም ይሖዋ አንድ መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር የነበሩትን ኃያላን ተዋጊዎች+ እንዲሁም መሪዎችና አለቆች ሁሉ ጠራርጎ አጠፋ፤ ንጉሡም ኀፍረት ተከናንቦ ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። በኋላም ወደ አምላኩ ቤት ገባ፤* በዚያም ሳለ የገዛ ወንዶች ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።+ 22 በዚህ መንገድ ይሖዋ ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅና ከሌሎች ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካሉ ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት ሰጣቸው። 23 ብዙዎችም ለይሖዋ ስጦታ፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ምርጥ የሆኑ ነገሮች ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤+ እሱም ከዚያ በኋላ በብሔራት ሁሉ ዘንድ ታላቅ አክብሮት አተረፈ።
24 በዚያን ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር፤ ወደ ይሖዋም ጸለየ፤+ እሱም መለሰለት፤ ምልክትም* ሰጠው።+ 25 ይሁንና ሕዝቅያስ ልቡ ታብዮ ስለነበር ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ ቀረ፤ የአምላክም ቁጣ በእሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። 26 ይሁን እንጂ ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን ዝቅ አደረገ፤+ እሱና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ትሕትና አሳዩ፤ የይሖዋም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።+
27 ሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብት አገኘ፤ ታላቅ ክብርም ተጎናጸፈ፤+ ብሩን፣ ወርቁን፣ የከበሩ ድንጋዮቹን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ጋሻዎቹንና ውድ የሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ የሚያስቀምጥባቸው ግምጃ ቤቶች ሠራ።+ 28 በተጨማሪም ለእህሉ፣ ለአዲሱ የወይን ጠጅና ለዘይቱ የማከማቻ ቦታዎች አዘጋጀ፤ እንዲሁም ለተለያዩ እንስሳት በረት፣ ለበጎችና ለፍየሎች ደግሞ ጉረኖ ሠራ። 29 ለራሱም ከተሞችን ገነባ፤ እጅግ ብዙ ከብቶች፣ መንጎችና እንስሳት ነበሩት፤ አምላክ ብዙ ንብረት ሰጥቶት ነበር። 30 የግዮንን+ ውኃ የላይኛውን መውጫ ደፍኖ+ ውኃው በምዕራብ በኩል በቀጥታ ወደ ዳዊት ከተማ+ እንዲወርድ ያደረገው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተሳካለት። 31 ይሁንና የባቢሎን መኳንንት ቃል አቀባዮች በምድሪቱ ላይ ስለተከሰተው+ ምልክት* እንዲጠይቁት+ ወደ እሱ በተላኩ ጊዜ እውነተኛው አምላክ እሱን ለመፈተንና+ በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ+ ሲል ተወው።
32 የቀረው የሕዝቅያስ ታሪክና ያሳየው ታማኝ ፍቅር+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ባየው ራእይ ላይ፣+ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።+ 33 በመጨረሻም ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ወደ ዳዊት ልጆች የመቃብር ስፍራ በሚወስድ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቀበሩት፤+ በሞተበት ጊዜም መላው ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አከበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ ምናሴ ነገሠ።