ኢዮብ
42 ከዚያም ኢዮብ ለይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦
3 አንተ ‘ያለእውቀት ሐሳቤን የሚሰውር ይህ ማን ነው?’ አልክ።+
በመሆኑም ስለማላውቃቸው እጅግ ድንቅ የሆኑ ነገሮች+
ማስተዋል በጎደለው መንገድ ተናግሬአለሁ።
4 ‘እባክህ ስማኝ፤ እኔም እናገራለሁ።
እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ትነግረኛለህ’ አልከኝ።+
5 ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤
አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ።
7 ይሖዋ ከኢዮብ ጋር ተነጋግሮ ካበቃ በኋላ፣ ቴማናዊውን ኤሊፋዝን ይሖዋ እንዲህ አለው፦
“አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን ስላልተናገራችሁ+ በአንተና በሁለቱ ጓደኞችህ+ ላይ ቁጣዬ ነዷል። 8 አሁን ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ ለራሳችሁም የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። አገልጋዬ ኢዮብም ለእናንተ ይጸልያል።+ እንደ ሞኝነታችሁ እንዳላደርግባችሁ የእሱን ልመና እቀበላለሁ፤* አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን አልተናገራችሁምና።”
9 በመሆኑም ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣ ሹሃዊው በልዳዶስና ናአማታዊው ሶፋር ሄደው ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። ይሖዋም የኢዮብን ጸሎት ሰማ።
10 ኢዮብ ለጓደኞቹ ከጸለየ+ በኋላ ይሖዋ በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ+ እንዲያበቃ አደረገ፤ ደግሞም ብልጽግናውን መለሰለት።* ይሖዋ ለኢዮብ ቀድሞ የነበረውን እጥፍ አድርጎ ሰጠው።+ 11 ወንድሞቹና እህቶቹ ሁሉ እንዲሁም የቀድሞ ወዳጆቹ ሁሉ+ ወደ እሱ መጡ፤ በቤቱም ከእሱ ጋር ምግብ በሉ። ሐዘናቸውን ገለጹለት፤ እንዲሁም ይሖዋ በእሱ ላይ እንዲደርስበት ከፈቀደው መከራ ሁሉ አጽናኑት። እያንዳንዳቸውም የገንዘብ ስጦታና የወርቅ ጌጥ ሰጡት።
12 በመሆኑም ይሖዋ ከፊተኛው የኢዮብ ሕይወት ይልቅ የኋለኛውን አብዝቶ ባረከ፤+ ኢዮብም 14,000 በጎች፣ 6,000 ግመሎች፣ 1,000 ጥማድ ከብቶችና 1,000 እንስት አህዮች አገኘ።+ 13 ደግሞም ሌሎች ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ወለደ።+ 14 የመጀመሪያዋን ሴት ልጁን ይሚማ፣ ሁለተኛዋን ቃስያ፣ ሦስተኛዋን ደግሞ ቄሬንሃጱክ ብሎ ስም አወጣላቸው። 15 በምድሪቱ ሁሉ የኢዮብን ሴቶች ልጆች ያህል የተዋቡ ሴቶች አልነበሩም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው።
16 ከዚህ በኋላ ኢዮብ 140 ዓመት ኖረ፤ እስከ አራት ትውልድም ድረስ ልጆችንና የልጅ ልጆችን አየ። 17 በመጨረሻም ኢዮብ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።