ኢያሱ
20 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በሙሴ አማካኝነት በነገርኳችሁ መሠረት ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን+ ምረጡ፤ 3 ሳያስበው ወይም በድንገት* ሰው የገደለ* ግለሰብ ወደነዚህ ከተሞች መሸሽ ይችላል። እነሱም ከደም ተበቃዩ+ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል። 4 ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ+ በከተማዋ በር ላይ ቆሞ+ ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይናገር። እነሱም ወደ ከተማቸው አስገብተው መኖሪያ ይስጡት፤ እሱም አብሯቸው ይኖራል። 5 ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት፤ ምክንያቱም ግለሰቡ ባልንጀራውን የገደለው የቆየ ጥላቻ ኖሮት ሳይሆን በድንገት* ነው።+ 6 ስለሆነም በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብ+ ድረስ በከተማዋ ውስጥ ይኑር፤ በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስም ከዚያ መውጣት የለበትም።+ ከዚያ በኋላ ገዳዩ ሸሽቶ ወደወጣባት ከተማ መመለስ እንዲሁም ወደ ከተማውና ወደ ቤቱ መግባት ይችላል።’”+
7 በመሆኑም በንፍታሌም ተራራማ አካባቢ በገሊላ የምትገኘውን ቃዴሽን፣+ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ሴኬምንና+ በይሁዳ ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ቂርያትአርባን+ ማለትም ኬብሮንን ለዚህ ዓላማ ቀደሱ።* 8 ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ ባለው የዮርዳኖስ ክልል ደግሞ ከሮቤል ነገድ ርስት በአምባው ላይ በሚገኘው ምድረ በዳ ላይ ያለችውን ቤጼርን፣+ ከጋድ ነገድ ርስት በጊልያድ የምትገኘውን ራሞትን+ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ ርስት በባሳን የምትገኘውን ጎላንን+ መረጡ።+
9 ሳያስበው ሰው* የገደለ ማንኛውም ግለሰብ በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ደም ተበቃዩ አግኝቶ እንዳይገድለው ሸሽቶ እንዲሸሸግባቸው+ ለእስራኤላውያን በሙሉ ወይም በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው የተለዩት ከተሞች እነዚህ ናቸው።+