ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት ማህሌት። መዝሙር።
65 አምላክ ሆይ፣ በጽዮን+ ውዳሴ ይቀርብልሃል፤
የተሳልነውን ለአንተ እንሰጣለን።+
2 ጸሎት ሰሚ የሆንከው አምላክ ሆይ፣ ሁሉም ዓይነት ሰው ወደ አንተ ይመጣል።+
3 የፈጸምኳቸው በደሎች አሸንፈውኛል፤+
አንተ ግን መተላለፋችንን ይቅር አልክ።+
4 በቅጥር ግቢዎችህ ይኖር ዘንድ
የመረጥከውና ያቀረብከው ሰው ደስተኛ ነው።+
እኛም በቤትህ፣
ቅዱስ በሆነው ቤተ መቅደስህ+ ውስጥ ባሉ ጥሩ ነገሮች እንረካለን።+
5 የመዳናችን አምላክ ሆይ፣
ፍርሃት በሚያሳድሩ የጽድቅ ተግባሮች ትመልስልናለህ፤+
በምድር ዳርቻዎች ሁሉና
ከባሕሩ ማዶ ርቀው ላሉት መታመኛቸው ነህ።+
6 አንተ በኃይልህ ተራሮችን አጽንተህ መሥርተሃል፤
ኃይልንም ለብሰሃል።+
7 አንተ የሚናወጡትን ባሕሮች፣ የሞገዶቻቸውን ድምፅ፣
የብሔራትንም ነውጥ ጸጥ ታሰኛለህ።+
8 ርቀው በሚገኙ ስፍራዎች የሚኖሩ ሰዎች ምልክቶችህን አይተው በታላቅ አድናቆት ይዋጣሉ፤+
ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ያሉ በደስታ እልል እንዲሉ ታደርጋለህ።
9 ምድርን እጅግ ፍሬያማ በማድረግና
በማበልጸግ ትንከባከባታለህ።+
የአምላክ ጅረት በውኃ የተሞላ ነው፤
ለሰዎች እህል ትሰጣለህ፤+
ምድርን ያዘጋጀኸው በዚህ መንገድ ነውና።
10 ትልሞቿን በውኃ ታረሰርሳለህ፤ የታረሰውንም መሬት ትደለድላለህ፤
በካፊያ ታለሰልሳታለህ፤ ቡቃያዋንም ትባርካለህ።+
11 ዘመኑ ጥሩነትህን እንደ ዘውድ እንዲጎናጸፍ ታደርጋለህ፤
በጎዳናዎችህም ላይ የተትረፈረፉ ነገሮች ይፈስሳሉ።+
12 የምድረ በዳው የግጦሽ መሬቶች ሁልጊዜ እንደረሰረሱ ናቸው፤+
ኮረብቶቹም ደስታን ተጎናጽፈዋል።+
13 የግጦሽ መሬቶቹ በመንጎች ተሞሉ፤
ሸለቆዎቹም በእህል ተሸፈኑ።+
በድል አድራጊነት እልል ይላሉ፤ አዎ፣ ይዘምራሉ።+