የሐዋርያት ሥራ
23 ጳውሎስ የሳንሄድሪንን ሸንጎ ትኩር ብሎ እየተመለከተ “ወንድሞች፣ እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በአምላክ ፊት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ይዤ ተመላልሻለሁ”+ አለ። 2 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጳውሎስ አጠገብ የቆሙት ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ። 3 ጳውሎስም “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! አምላክ አንተን ይመታሃል። በሕጉ መሠረት በእኔ ላይ ለመፍረድ ተቀምጠህ ሳለ አንተ ራስህ ሕጉን በመጣስ እንድመታ ታዛለህ?” አለው። 4 አጠገቡ የቆሙትም “የአምላክን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህ?” አሉት። 5 ጳውሎስም “ወንድሞች፣ እኔ እኮ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅኩም። ምክንያቱም ‘በሕዝብህ ገዢ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ ተብሎ ተጽፏል” አላቸው።+
6 ጳውሎስ ግማሾቹ ሰዱቃውያን ግማሾቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ በሳንሄድሪን ሸንጎ ውስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ።+ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው” ሲል ተናገረ። 7 ይህን በመናገሩ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ግጭት ተፈጥሮ ጉባኤው ለሁለት ተከፈለ። 8 ምክንያቱም ሰዱቃውያን ትንሣኤም፣ መልአክም፣ መንፈሳዊ ፍጥረታትም የሉም ይሉ የነበረ ሲሆን ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ነገሮች ያምኑ ነበር።+ 9 ስለዚህ ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ተነስተው እንዲህ ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፦ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ አናግሮት ከሆነ ግን+ . . . ።” 10 በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭት እየከረረ ሲሄድ የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው እንዲያመጡትና ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት አዘዘ።
11 ሆኖም በዚያኑ ዕለት ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለው፦ “አይዞህ፣ አትፍራ!+ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ* ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።”+
12 በነጋም ጊዜ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ ተማማሉ።* 13 ይህን ሴራ ለመፈጸም የተማማሉት ሰዎች ቁጥራቸው ከ40 በላይ ነበር። 14 እነሱም ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ሄደው እንዲህ አሉ፦ “ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ አንዳች እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ ተማምለናል። 15 ስለዚህ እናንተ ከሳንሄድሪን ሸንጎ ጋር ሆናችሁ የጳውሎስን ጉዳይ ይበልጥ ማጣራት የምትፈልጉ በማስመሰል እሱን ወደ እናንተ እንዲያመጣው ለሠራዊቱ ሻለቃ ንገሩት። ይሁንና እኛ እዚህ ከመድረሱ በፊት እሱን ለመግደል ተዘጋጅተን እንጠብቃለን።”
16 ይሁን እንጂ የጳውሎስ የእህቱ ልጅ አድብተው ጥቃት ለመሰንዘር እንዳሰቡ በመስማቱ ወደ ጦር ሰፈሩ ገብቶ ጉዳዩን ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመኮንኖቹ አንዱን ጠርቶ “ይህ ወጣት ለሠራዊቱ ሻለቃ የሚነግረው ነገር ስላለው ወደ እሱ ውሰደው” አለው። 18 እሱም ወደ ሻለቃው ይዞት ሄደና “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ ይህ ወጣት የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ጠየቀኝ” አለው። 19 ሻለቃውም እጁን ይዞ ለብቻው ገለል ካደረገው በኋላ “ልትነግረኝ የፈለግከው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 20 እሱም እንዲህ አለ፦ “አይሁዳውያን ስለ ጳውሎስ ጉዳይ በዝርዝር ማወቅ የፈለጉ በማስመሰል ነገ ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ እንድታመጣው ሊጠይቁህ ተስማምተዋል።+ 21 አንተ ግን በዚህ እንዳትታለል፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች አድብተው በእሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየጠበቁ ነው፤ ደግሞም እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህልም ሆነ ውኃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤+ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን ፈቃድ እየተጠባበቁ ነው።” 22 በዚህ ጊዜ የሠራዊቱ ሻለቃ “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም እንዳታወራ” ብሎ ካዘዘው በኋላ ወጣቱን አሰናበተው።
23 ከዚያም ከመኮንኖቹ መካከል ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ 200 ወታደሮች እንዲሁም 70 ፈረሰኞችና ጦር የያዙ 200 ሰዎች አዘጋጁ። 24 በተጨማሪም ጳውሎስን ወደ አገረ ገዢው ወደ ፊሊክስ በደህና ለማድረስ የሚጓዝባቸው ፈረሶች አዘጋጁ።” 25 እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፦
26 “ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ፤ ለክቡር አገረ ገዢ ለፊሊክስ፦ ሰላም ለአንተ ይሁን። 27 አይሁዳውያን ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ሆኖም የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅኩ+ ወዲያውኑ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አዳንኩት።+ 28 እሱን የከሰሱት ለምን እንደሆነ ለማወቅ ስለፈለግኩም ወደ ሳንሄድሪን ሸንጓቸው አቀረብኩት።+ 29 የተከሰሰውም ከሕጋቸው ጋር በተያያዘ በተነሳ ውዝግብ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤+ ሆኖም ለሞት ወይም ለእስር የሚያበቃ አንድም ክስ አላገኘሁም። 30 ይሁንና በዚህ ሰው ላይ የተሸረበ ሴራ እንዳለ ስለተነገረኝ+ ወዲያውኑ ወደ አንተ ልኬዋለሁ፤ ከሳሾቹም ክሳቸውን በአንተ ፊት እንዲያቀርቡ አዝዤአቸዋለሁ።”
31 ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ጳውሎስን ይዘው+ በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ ወሰዱት። 32 በማግስቱም ፈረሰኞቹ ከጳውሎስ ጋር ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ እነሱ ወደ ጦር ሰፈሩ ተመለሱ። 33 ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ ደብዳቤውን ለአገረ ገዢው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት። 34 እሱም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ የየትኛው አውራጃ ሰው እንደሆነ ጠየቀ፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ተረዳ።+ 35 ከዚያም “ከሳሾችህ ሲመጡ ጉዳይህን በደንብ አየዋለሁ” አለው።+ በሄሮድስም ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ አዘዘ።