የዳዊት ጸሎት።
86 ይሖዋ ሆይ፣ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ደግሞም መልስልኝ፤
ጎስቋላና ድሃ ነኝና።+
2 እኔ ታማኝ ስለሆንኩ ሕይወቴን ጠብቃት።+
በአንተ የሚታመነውን አገልጋይህን አድነው፤
አንተ አምላኬ ነህና።+
3 ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየኝ፤+
ቀኑን ሙሉ አንተን እጣራለሁና።+
4 አገልጋይህን ደስ አሰኘው፤
ይሖዋ ሆይ፣ የአንተን እርዳታ እሻለሁና።
5 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤+ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤+
አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።+
6 ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን አዳምጥ፤
እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውንም ልመና በትኩረት ስማ።+
7 አንተ መልስ ስለምትሰጠኝ፣+
በተጨነቅኩ ቀን አንተን እጣራለሁ።+
8 ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤+
ከአንተ ሥራ ጋር የሚወዳደር አንድም ሥራ የለም።+
9 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ የሠራሃቸው ብሔራት ሁሉ ይመጣሉ፤
በፊትህም ይሰግዳሉ፤+
ለስምህም ክብር ይሰጣሉ።+
10 አንተ ታላቅ ነህና፤ ድንቅ ነገሮችም ትሠራለህ፤+
አንተ አምላክ ነህ፤ ከአንተ ሌላ የለም።+
11 ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ።+
በእውነትህ እሄዳለሁ።+
ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ።+
12 ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ፤+
ስምህንም ለዘላለም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤
13 ለእኔ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ታላቅ ነውና፤
ሕይወቴንም ጥልቅ ከሆነው መቃብር አድነሃል።+
14 አምላክ ሆይ፣ እብሪተኛ ሰዎች በእኔ ላይ ተነስተዋል፤+
የጨካኞች ቡድን ሕይወቴን ይሻታል፤
አንተንም ከምንም አልቆጠሩም።+
15 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን መሐሪና ሩኅሩኅ፣
ለቁጣ የዘገየህ እንዲሁም ታማኝ ፍቅርህና ታማኝነትህ የበዛ አምላክ ነህ።+
16 ወደ እኔ ተመልከት፤ ሞገስም አሳየኝ።+
ለአገልጋይህ ብርታትህን ስጠው፤+
የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17 እኔን የሚጠሉ አይተው እንዲያፍሩ፣
የጥሩነትህን ምልክት አሳየኝ።
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ረዳቴና አጽናኜ ነህና።