ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ “ጥፋት አታምጣ” በተባለው ቅኝት። የዳዊት መዝሙር። ሚክታም። ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው እንዲጠብቁና እንዲገድሉት ሰዎችን በላከ ጊዜ።+
59 አምላኬ ሆይ፣ ከጠላቶቼ ታደገኝ፤+
በእኔ ላይ ከተነሱት ሰዎች ጠብቀኝ።+
2 ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤
ከጨካኝ ሰዎችም አድነኝ።
3 እነሆ፣ እኔን ለማጥቃት አድፍጠው ይጠብቃሉ፤+
ይሖዋ ሆይ፣ ምንም ዓይነት ዓመፅም ሆነ ኃጢአት ሳይገኝብኝ
ብርቱ የሆኑ ሰዎች ያጠቁኛል።+
4 የሠራሁት ጥፋት ባይኖርም እኔን ለማጥቃት ተጣደፉ፤ ደግሞም ተዘጋጁ።
ወደ አንተ ስጣራ ተነስ፤ ተመልከተኝም።
5 የሠራዊት አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ ነህና።+
ብሔራትን ሁሉ ለመመርመር ተነስ።
ተንኮለኛ ለሆኑ ከሃዲዎች ሁሉ ምሕረት አታድርግ።+ (ሴላ)
6 በየምሽቱ ተመልሰው ይመጣሉ፤+
እንደ ውሾች እያጉረመረሙ በከተማዋ ዙሪያ ያደባሉ።+
7 ከአፋቸው የሚዥጎደጎደውን ተመልከት፤
ከንፈሮቻቸው እንደ ሰይፍ ናቸው፤+
“ማን ይሰማል?” ይላሉና።+
8 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ትስቅባቸዋለህ፤+
ብሔራትን ሁሉ ታላግጥባቸዋለህ።+
9 ብርታቴ ሆይ፣ አንተን እጠባበቃለሁ፤+
አምላክ አስተማማኝ መጠጊያዬ ነውና።+
10 ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላክ ይረዳኛል፤+
አምላክ ጠላቶቼን በድል አድራጊነት ስሜት እንዳያቸው ያደርገኛል።+
11 ሕዝቤ ይህን እንዳይረሳ አትግደላቸው።
በኃይልህ እንዲቅበዘበዙ አድርጋቸው፤
ጋሻችን ይሖዋ ሆይ፣ ለውድቀት ዳርጋቸው።+
12 ከአፋቸው ኃጢአትና ከከንፈራቸው ቃል፣
ከሚናገሩት እርግማንና የማታለያ ቃል የተነሳ
በኩራታቸው ይጠመዱ።+
13 በቁጣህ አጥፋቸው፤+
ከሕልውና ውጭ እንዲሆኑ ደምስሳቸው፤
አምላክ ያዕቆብንና መላውን ምድር በመግዛት ላይ እንደሆነ አሳውቃቸው።+ (ሴላ)
14 ምሽት ላይ ተመልሰው ይምጡ፤
እንደ ውሾች እያጉረመረሙ በከተማዋ ዙሪያ ያድቡ።+
15 ምግብ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ይንከራተቱ፤+
በልተውም አይጥገቡ፤ የሚያርፉበት ቦታም ይጡ።
16 እኔ ግን ስለ ብርታትህ እዘምራለሁ፤+
በማለዳ ስለ ታማኝ ፍቅርህ በደስታ እናገራለሁ።
አንተ አስተማማኝ መጠጊያዬ፣
ደግሞም በጭንቀቴ ቀን መሸሸጊያዬ ነህና።+
17 ብርታቴ ሆይ፣ ለአንተ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፤+
ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላክ አስተማማኝ መጠጊያዬ ነውና።+