የማቴዎስ ወንጌል
22 በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል በምሳሌ ነገራቸው፦ 2 “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ+ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 3 ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።+ 4 በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። 5 እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤+ 6 ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።
7 “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።+ 8 ከዚያም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም።+ 9 ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’+ 10 በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።
11 “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። 12 በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። 13 ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው።
14 “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
15 ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው በንግግሩ ሊያጠምዱት ሴራ ጠነሰሱ።+ 16 ስለዚህ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር ወደ እሱ በመላክ እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር እንዲሁም ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ እናውቃለን። 17 እስቲ ንገረን፣ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”* 18 ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? 19 እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ።” እነሱም አንድ ዲናር* አመጡለት። 20 እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። 21 እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።+ 22 ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ከዚያም ትተውት ሄዱ።
23 በዚያኑ ዕለት፣ በትንሣኤ የማያምኑት+ ሰዱቃውያን መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦+ 24 “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል።+ 25 በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። 26 ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ። 27 በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 28 እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
29 ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ተሳስታችኋል፤+ 30 ምክንያቱም በትንሣኤ ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማይ እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።+ 31 የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ አምላክ እንዲህ ሲል ለእናንተ የተናገረውን አላነበባችሁም? 32 ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ብሏል።+ እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”+ 33 ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ በትምህርቱ ተደነቁ።+
34 ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሲሰሙ ተሰብስበው መጡ። 35 ከእነሱም መካከል አንድ ሕግ አዋቂ እሱን ለመፈተን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 36 “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?”+ 37 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “‘አምላክህን ይሖዋን* በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና* በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’+ 38 ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። 39 ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።+ 40 መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።”+
41 ፈሪሳውያን አንድ ላይ ተሰብስበው እንዳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦+ 42 “ስለ መሲሑ* ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” እነሱም “የዳዊት” አሉት።+ 43 እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ+ እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል? 44 ምክንያቱም ዳዊት ‘ይሖዋ* ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ሲል ተናግሯል።+ 45 ታዲያ ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”+ 46 ከዚህ በኋላ አንዲት ቃል ሊመልስለት የቻለም ሆነ ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ አንድም ሰው አልነበረም።