ሕዝቅኤል
13 የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፣ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤+ የገዛ ራሳቸውን ትንቢት ፈጥረው የሚናገሩትንም*+ እንዲህ በላቸው፦ ‘የይሖዋን ቃል ስሙ። 3 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ምንም ያዩት ነገር ሳይኖር የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉት ሞኝ ነቢያት ወዮላቸው!+ 4 እስራኤል ሆይ፣ ነቢያትህ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ሆነዋል። 5 እስራኤል፣ በይሖዋ ቀን በሚኖረው ውጊያ+ ጸንቶ ይቆም ዘንድ በድንጋይ ቅጥሩ ላይ የሚገኙትን የፈረሱ ቦታዎች ለእስራኤል ቤት መልሳችሁ ለመገንባት ወደዚያ አትሄዱም።”+ 6 “ይሖዋ ሳይልካቸው ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል’ የሚሉ ሰዎች ያዩአቸው ራእዮች ውሸት ናቸው፤ ትንቢታቸውም ሐሰት ነው፤ ይሁንና ቃላቸው እንዲፈጸም ይጠብቃሉ።+ 7 እኔ የተናገርኩት ነገር ሳይኖር ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል’ ስትሉ ያያችሁት ራእይ ውሸት፣ የተናገራችሁትም ትንቢት ሐሰት መሆኑ አይደለም?”’
8 “‘ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ውሸት ስለተናገራችሁና ያያችኋቸው ራእዮች ሐሰት ስለሆኑ እኔ በእናንተ ላይ ተነስቻለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”+ 9 እጄ የውሸት ራእዮች በሚያዩና የሐሰት ትንቢት በሚናገሩ ነቢያት ላይ ተነስታለች።+ ሚስጥሬን ከማካፍላቸው ሰዎች መካከል አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብም ላይ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይመለሱም፤ እናንተም እኔ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።+ 10 ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰላም ሳይኖር “ሰላም አለ!” እያሉ ሕዝቤን በማሳታቸው ነው።+ ሕዝቡ ጥንካሬ የሌለው ግድግዳ ሲሠራ እነሱ በኖራ ይለስኑታል።’*+
11 “በኖራ የሚለስኑትን ሰዎች ’ግድግዳው ይፈርሳል’ በላቸው። ከባድ ዶፍ ይጥላል፤ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል፤ ኃይለኛ አውሎ ነፋስም ግድግዳውን ያፈርሰዋል።+ 12 ግድግዳው በሚወድቅበት ጊዜም ‘የለሰናችሁት ልስን የት አለ?’ ብለው ይጠይቋችኋል።+
13 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በታላቅ ቁጣዬ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እንዲነሳ አደርጋለሁ፤ በቁጣዬም ከባድ ዶፍ አዘንባለሁ፤ ደግሞም ጥፋት በሚያስከትል ታላቅ ንዴት የበረዶ ድንጋይ አወርዳለሁ። 14 እናንተ በኖራ የለሰናችሁትን ግድግዳ አፍርሼ ከመሬት እደባልቀዋለሁ፤ መሠረቱም ይታያል። ከተማዋ ስትወድቅ በውስጧ ትጠፋላችሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’
15 “‘ቁጣዬን ሁሉ በግድግዳውና ግድግዳውን በኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ በማወርድበት ጊዜ እንዲህ እላችኋለሁ፦ “ግድግዳው ፈርሷል፤ በኖራ የለሰኑት ሰዎችም የሉም።+ 16 ለኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእዮች የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል”’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
17 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ የገዛ ራሳቸውን ትንቢት ፈጥረው ወደሚናገሩት የሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን አዙር፤ በእነሱም ላይ ትንቢት ተናገር። 18 እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የሰዎችን ሕይወት* ለማደን፣ በክንድ* ሁሉ ላይ የሚታሰር ቀጭን ጨርቅ ለሚሰፉና ለሰው እንደየቁመቱ የራስ መሸፈኛ ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤን ሕይወት* እያደናችሁ የራሳችሁን ሕይወት* ለማዳን ትጥራላችሁ? 19 የእናንተን ውሸት ለሚያዳምጠው ሕዝቤ ውሸት እየተናገራችሁ+ መሞት የማይገባቸውን ሰዎች* በመግደልና መኖር የማይገባቸውን ሰዎች* በሕይወት በማቆየት፣ ለጥቂት እፍኝ ገብስና ለቁርስራሽ ዳቦ ብላችሁ+ በሕዝቤ መካከል ታረክሱኛላችሁ?”’
20 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ ሴቶች፣ እነሆ ሰዎችን* እንደ ወፎች ለማደን በምትጠቀሙበት ጨርቅ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ፤ ከክንዳችሁም ላይ እቀደዋለሁ፤ እንደ ወፎች ያደናችኋቸውንም ሰዎች ነፃ አወጣለሁ። 21 የራስ መሸፈኛችሁን እቀዳለሁ፤ ሕዝቤንም ከእጃችሁ እታደጋለሁ፤ ከእንግዲህ አድናችሁ አትይዟቸውም፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።+ 22 እኔ እንዲያዝን* ያላደረግኩትን ጻድቅ ሰው ሐሰት በመናገር+ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጋችኋልና፤ ደግሞም ክፉው ሰው ከክፋት መንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዳይኖር+ እጁን አበርትታችኋል።+ 23 ስለዚህ እናንተ ሴቶች፣ ከእንግዲህ የውሸት ራእዮች አታዩም፤ ሟርትም አታሟርቱም፤+ ሕዝቤንም ከእጃችሁ እታደጋለሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’”