ዘፍጥረት
16 የአብራም ሚስት ሦራ ለአብራም ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤+ ይሁንና አጋር+ የምትባል አንዲት ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት። 2 በመሆኑም ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እንደምታየው ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል። እባክህ ከአገልጋዬ ጋር ግንኙነት ፈጽም። ምናልባትም በእሷ አማካኝነት ልጆች ላገኝ እችላለሁ።”+ ስለሆነም አብራም የሦራን ቃል ሰማ። 3 አብራም በከነአን ምድር ለአሥር ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወስዳ ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ለአብራም ሰጠችው። 4 በመሆኑም አብራም ከአጋር ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች። መፀነሷን ባወቀች ጊዜም እመቤቷን መናቅ ጀመረች።
5 በዚህ ጊዜ ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ። አገልጋዬን በእቅፍህ ያደረግኩልህ እኔው ራሴ ነበርኩ፤ እሷ ግን መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ትንቀኝ ጀመር። ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ።” 6 በመሆኑም አብራም ሦራን “እንግዲህ አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ናት። መልካም መስሎ የታየሽን ነገር አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ አገልጋይዋን አዋረደቻት፤ ስለዚህም ጥላት ኮበለለች።
7 በኋላም የይሖዋ መልአክ አጋርን በምድረ በዳ በሚገኝ አንድ የውኃ ምንጭ አጠገብ ማለትም ወደ ሹር+ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው ምንጭ አጠገብ አገኛት። 8 እሱም “የሦራ አገልጋይ አጋር፣ ለመሆኑ የመጣሽው ከየት ነው? ወዴትስ እየሄድሽ ነው?” አላት። እሷም መልሳ “ከእመቤቴ ከሦራ ኮብልዬ እየሄድኩ ነው” አለች። 9 የይሖዋም መልአክ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእሷም በትሕትና ተገዢላት” አላት። 10 ከዚያም የይሖዋ መልአክ “ከብዛቱ የተነሳ የማይቆጠር እስኪሆን ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛዋለሁ”+ አላት። 11 በተጨማሪም የይሖዋ መልአክ እንዲህ አላት፦ “እንግዲህ ይኸው ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ስሙንም እስማኤል* ትይዋለሽ፤ ምክንያቱም ይሖዋ የሥቃይ ጩኸትሽን ሰምቷል። 12 እሱም እንደ ዱር አህያ* ይሆናል። ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል፤ ከወንድሞቹም ሁሉ ፊት ለፊት ይኖራል።”*
13 ከዚያም አጋር “የሚያየኝን አሁን በእርግጥ አየሁት ማለት ነው?” ብላ ስላሰበች እያነጋገራት የነበረውን ይሖዋን ስሙን ጠርታ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ”+ አለች። 14 የውኃ ጉድጓዱ ብኤርላሃይሮዒ* ተብሎ የተጠራው በዚህ የተነሳ ነው። (ጉድጓዱም በቃዴስና በቤሬድ መካከል ይገኛል።) 15 ስለዚህ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን ልጅ እስማኤል+ ብሎ ስም አወጣለት። 16 አጋር ለአብራም እስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የ86 ዓመት ሰው ነበር።