ዘፀአት
9 ስለሆነም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።+ 2 እነሱን ለመልቀቅ እንቢተኛ የምትሆንና እንዳይሄዱ የምትከለክላቸው ከሆነ 3 የይሖዋ እጅ+ በመስክ ያሉትን ከብቶችህን ይመታል። በፈረሶች፣ በአህዮች፣ በግመሎች፣ በበሬዎች፣ በላሞችና በመንጎች ላይ አጥፊ መቅሰፍት ይወርዳል።+ 4 ይሖዋም በእስራኤል ከብቶችና በግብፅ ከብቶች መካከል ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል፤ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አይሞትም።”’”+ 5 ከዚህም በላይ ይሖዋ “በነገው ዕለት እኔ ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ይህን አደርጋለሁ” በማለት ቀን ቆርጧል።
6 ይሖዋም በማግስቱ ይህን አደረገ፤ የግብፅ ከብት ሁሉ ይሞት ጀመር፤+ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል ግን አንድ እንኳ አልሞተም። 7 ፈርዖንም ሁኔታውን ሲያጣራ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ግን የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡንም አለቀቀም።+
8 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ እፍኝ ሙሉ ጥቀርሻ ውሰዱ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9 ጥቀርሻውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ አቧራ ይሆናል፤ ከዚያም በመላው የግብፅ ምድር ባለ ሰውና እንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ይወጣል።”
10 እነሱም ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ ጥቀርሻ ወስደው ፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን ወደ ሰማይ በተነው፤ ጥቀርሻውም በሰውና በእንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ወጣ። 11 አስማተኞቹ ካህናት በእባጩ የተነሳ ሙሴ ፊት ሊቆሙ አልቻሉም፤ ምክንያቱም እባጩ በአስማተኞቹ ካህናትና በሁሉም ግብፃውያን ላይ ወጥቶ ነበር።+ 12 ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ ፈርዖንም ልክ ይሖዋ ለሙሴ እንደነገረው እነሱን አልሰማቸውም።+
13 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም፤ እንዲህም በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14 ምክንያቱም በመላው ምድር ላይ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ እንድታውቅ+ ልብህን፣ አገልጋዮችህንና ሕዝብህን ለመምታት መቅሰፍቴን በሙሉ አሁን አወርዳለሁ። 15 እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር። 16 ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።+ 17 ሕዝቤን አለቅም በማለት አሁንም በእነሱ ላይ እንደታበይክ ነህ? 18 እንግዲህ በነገው ዕለት በዚህ ሰዓት ገደማ ግብፅ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ እጅግ ታላቅ የበረዶ ውርጅብኝ አዘንባለሁ። 19 ስለዚህ አሁን መልእክት ልከህ በመስክ ላይ የተሰማሩትን ከብቶችህንና የአንተ የሆኑትን ሁሉ ወደ መጠለያ እንዲገቡ አድርግ። በመስክ የተገኘና ወደ ቤት ያልገባ ማንኛውም ሰውና እንስሳ በረዶው ይወርድበትና ይሞታል።”’”
20 ከፈርዖን አገልጋዮች መካከል የይሖዋን ቃል የፈሩ ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ቤት አስገቡ፤ 21 ሆኖም የይሖዋን ቃል ከቁም ነገር ያልቆጠሩት ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን እዚያው መስክ ላይ እንዳሉ ተዉአቸው።
22 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “በመላው የግብፅ ምድር ላይ ይኸውም በሰው፣ በእንስሳና በግብፅ ምድር ላይ በበቀለው ተክል ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ+ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።+ 23 በመሆኑም ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ አነሳ፤ ይሖዋም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፤ እሳትም* በምድር ላይ ወረደ፤ ይሖዋ በግብፅ ምድር ላይ ያለማቋረጥ በረዶ እንዲወርድ አደረገ። 24 በረዶም ወረደ፤ በበረዶውም መካከል የእሳት ብልጭታ ነበር። በረዶውም እጅግ ከባድ ነበር፤ ግብፅ እንደ አገር ሆና ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በዚያች ምድር ላይ እንዲህ ያለ በረዶ ተከስቶ አያውቅም።+ 25 በረዶው ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር በመስክ ላይ የነበረውን ማንኛውንም ነገር መታ፤ ዕፀዋቱን ሁሉና በሜዳ ላይ ያለውን ዛፍ በሙሉ አወደመ።+ 26 በረዶ ያልወረደው እስራኤላውያን በሚኖሩበት በጎሸን ምድር ብቻ ነበር።+
27 ስለሆነም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንስ በድያለሁ። ይሖዋ ጻድቅ ነው፤ ጥፋተኞቹ እኔና ሕዝቤ ነን። 28 አምላክ ያመጣው ነጎድጓድና በረዶ እንዲቆም ይሖዋን ለምኑልኝ። እኔም እናንተን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እሆናለሁ፤ ከአሁን በኋላ እዚህ አትቆዩም።” 29 በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “ልክ ከከተማዋ እንደወጣሁ እጆቼን በይሖዋ ፊት እዘረጋለሁ። ምድር የይሖዋ እንደሆነች እንድታውቅም ነጎድጓዱ ይቆማል፤ በረዶውም ከዚያ በኋላ አይወርድም።+ 30 ሆኖም አንተም ሆንክ አገልጋዮችህ ይህ ከሆነ በኋላም እንኳ ይሖዋ አምላክን እንደማትፈሩ አውቃለሁ።”
31 በዚህ ጊዜ ገብሱ አሽቶ፣ ተልባውም አብቦ ስለነበር ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። 32 ስንዴውና አጃው ግን ወቅታቸው ገና ስለነበር ጉዳት አልደረሰባቸውም። 33 ሙሴም ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማዋ ወጣ፤ እጆቹንም በይሖዋ ፊት ዘረጋ፤ ነጎድጓዱና በረዶውም ቆመ፤ ዝናቡም በምድር ላይ መዝነቡን አቆመ።+ 34 ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጎድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደገና ኃጢአት ሠራ፤ እሱም ሆነ አገልጋዮቹ ልባቸውን አደነደኑ።+ 35 የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት እንደተናገረውም እስራኤላውያንን አለቀቀም።+